ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 17
17
ኢዮሣፍጥ የይሁዳ ንጉሥ መሆኑ
1ኢዮሣፍጥ በአባቱ በአሳ እግር ተተክቶ ነገሠ፤ እስራኤልንም ለመውጋት ኀይሉን አጠናከረ፤ 2በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞችና በየገጠሩ ሁሉ እንዲሁም አባቱ ንጉሥ አሳ ድል አድርጎ በያዛቸው በኤፍሬም ግዛት ባሉት ከተሞች ሁሉ ወታደሮቹን አሰፈረ፤ 3ኢዮሣፍጥ አባቱ በዘመነ መንግሥቱ መጀመሪያ ላይ የነበረውን የዳዊትን መልካም ምሳሌነት ስለ ተከተለና ባዓል ተብሎ የሚጠራውን ጣዖት ስላላመለከ እግዚአብሔር ባረከው፤ 4ኢዮሣፍጥ የአባቱን አምላክ የእግዚአብሔርን መመሪያ ተከተለ፤ ትእዛዞቹንም ጠበቀ፤ የእስራኤል ነገሥታት ያደርጉት የነበረውንም ዐይነት ክፉ ሥራ ከቶ አልፈጸመም፤ 5ስለዚህ እግዚአብሔር የኢዮሣፍጥ መንግሥት በይሁዳ ላይ እንዲጸና አደረገ፤ የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ልዩ ልዩ ገጸ በረከት ያመጡለት ስለ ነበረም እጅግ የበለጸገና የከበረ ሆነ፤ 6እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ አገለገለ፤ ከዚህም በላይ በኰረብቶች ላይ የሚገኙትን የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችንና በይሁዳ የነበሩትን አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስሎች ሁሉ ደመሰሰ።
7ኢዮሣፍጥ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ቤንሐይል፥ አብድዩ፥ ዘካርያስ፥ ናትናኤልና ሚክያስ ተብለው የሚጠሩትን ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለሥልጣኖች በይሁዳ ከተሞች እንዲያስተምሩ ላካቸው። 8ከእነርሱም ጋር ዘጠኝ ሌዋውያንና ሁለት ካህናት ነበሩ፤ ሌዋውያኑ ሸማዕያ፥ ነታንያ፥ ዘባድያ፥ ዐሣሄል፥ ሸሚራሞት፥ ይሖናታን፥ ኦዶኒያ፥ ጦቢያና ጦባዶኒያ ሲሆኑ ካህናቱ ደግሞ ኤሊሻማዕና ይሖራም ናቸው፤ 9እነርሱም የእግዚአብሔርን የሕግ መጽሐፍ ይዘው ወደ መላው የይሁዳ ከተሞች በመሄድ ለሕዝቡ ሁሉ አስተማሩ።
የኢዮሣፍጥ ታላቅነት
10በይሁዳ ግዛት ዙሪያ የሚገኙ ነገሥታት በኢዮሣፍጥ ላይ ጦርነት ከማድረግ እንዲገቱ እግዚአብሔር ፍርሀት አሳደረባቸው፤ 11ከፍልስጥኤማውያን አንዳንዶቹ ብዙ ብርና ሌላም ዐይነት ስጦታ ለንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሲያበረክቱ፥ አንዳንድ ዐረቦች ደግሞ ሰባት ሺህ ሰባት መቶ በጎችና ሰባት ሺህ ሰባት መቶ ፍየሎች አመጡለት፤ 12-13ስለዚህ ኢዮሣፍጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ገናና እየሆነ ሄደ፤ በመላው ይሁዳ ምሽጎችንና፥ እጅግ የበዛ ስንቅና ትጥቅ የተከማቹባቸውን ከተማዎች ሠራ።
በኢየሩሳሌምም የተለየ ችሎታ ያላቸውን ተዋጊዎች አኖረ፤ 14ከይሁዳ ነገድ ለተመለመሉት ወታደሮች አዛዥ ዐድና ተብሎ የሚጠራ የጦር መኰንን ነበር፤ በእርሱም ሥር ሦስት መቶ ሺህ ወታደሮች ነበሩ፤ 15ከእርሱም ቀጥሎ በማዕርግ ሁለተኛ የሆነው የሆሐናን ተብሎ የሚጠራ የጦር አዛዥ ነበር፤ በእርሱም ሥር ሁለት መቶ ሰማኒያ ሺህ ወታደሮች ነበሩ፤ 16ከይሆሐናን ቀጥሎ በማዕርግ ሦስተኛ የሆነው የጦር መኰንን የዚክሪ ልጅ ዐማሥያ ነበር፤ በእርሱም ሥር ሁለት መቶ ሺህ ወታደሮች ነበሩ፤ እርሱም በገዛ ፈቃዱ ራሱን ለእግዚአብሔር አገልግሎት የለየ የጦር አዛዥ ነበር፤ 17ከብንያም ነገድ ለተመለመሉት ወታደሮች ዋና አዛዥ ኤሊያዳዕ ተብሎ የሚጠራ ጀግና ወታደር ነበር፤ በእርሱም ሥር ጋሻና ቀስት የያዙ ሁለት መቶ ሺህ ወታደሮች ነበሩ፤ 18ከእርሱ ቀጥሎ በማዕርግ ሁለተኛ የሆነው የሆዛባድ ተብሎ የሚጠራ የጦር አዛዥ ነበር፤ በእርሱም ሥር ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ አንድ መቶ ሰማኒያ ሺህ ወታደሮች ነበሩ፤ 19እነዚህ ሁሉ ወታደሮች ንጉሥ ኢዮሣፍጥን በኢየሩሳሌም የሚያገለግሉ ሲሆኑ፥ በተጨማሪም ንጉሡ በሌሎቹ በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሌሎች ወታደሮችን አስፍሮ ነበር።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 17: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997