ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 12:1-16

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 12:1-16 አማ05

የሮብዓም መንግሥት በጽኑ በተመሠረተና ኀይል ባገኘ ጊዜ እርሱና እስራኤላውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ፤ ለእግዚአብሔር የነበራቸውን ታማኝነት በማጓደላቸውም ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ጣለበት። እርሱም አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሠረገሎችና ሥልሳ ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሺሻቅ ጦር ሠራዊት ውስጥ ከእርሱ ጋር ከግብጽ የመጡ ብዛታቸው ሊቈጠር የማይቻል ሊቢያውያን፥ ሱካውያንና ኢትዮጵያውያን ነበሩ፤ ንጉሥ ሺሻቅ የተመሸጉትን የይሁዳ ከተማዎች ወሮ ያዘ፤ እስከ ኢየሩሳሌምም ድረስ ገሥግሦ መጣ። ከዚህ በኋላ ነቢዩ ሸማዕያ ሺሻቅን በመፍራት፥ በኢየሩሳሌም በአንድነት ተሰብስበው ወደ ነበሩ ወደ ንጉሥ ሮብዓምና ወደ ይሁዳ መሪዎች ሄዶ፥ “እግዚአብሔር ‘እኔን ስለ ተዋችሁ እነሆ፥ እኔም በሺሻቅ እጅ እንድትወድቁ ትቼአችኋለሁ’ ይላችኋል” አላቸው። ንጉሥ ሮብዓምና የይሁዳ መሪዎችም ኃጢአት መሥራታቸውን በማመን፥ “እግዚአብሔር የሚያደርገው ነገር ሁሉ ትክክል ነው” በማለት ራሳቸውን አዋረዱ። እግዚአብሔርም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ፥ ነቢዩ ሸማዕያን እንደገና እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ በደላቸውን አምነው ራሳቸውን ስላዋረዱ፥ አላጠፋቸውም፤ ሺሻቅ አደጋ በሚጥልባቸው ጊዜ፥ ፈጥኜ በመታደግ አድናቸዋለሁ፤ በኢየሩሳሌምም ላይ ቊጣዬን ሙሉ በሙሉ አላወርድም፤ ይሁን እንጂ ለእኔ በመገዛትና ለምድር ነገሥታት በመገዛት መካከል ያለውን ልዩነት ይገነዘቡ ዘንድ፥ ሺሻቅ ድል አድርጎ ይገዛቸዋል።” ስለዚህ ንጉሥ ሺሻቅ በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም ገብቶ፥ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት የነበረውን ሀብት ሁሉ፥ ንጉሥ ሰሎሞን ከወርቅ ያሠራቸውን ጋሻዎች ጭምር ዘርፎ ወሰደ፤ ንጉሥ ሮብዓም ሺሻቅ በወሰዳቸው ጋሻዎች ምትክ፥ ሌሎች ጋሻዎችን ከነሐስ አሠርቶ፥ የቤተ መንግሥቱን ቅጽር በሮች በሚጠብቁ የዘበኞች አለቆች ኀላፊነት እንዲቀመጡ አደረገ፤ ንጉሡ ወደ ቤተ መቅደስ በመጣ ቊጥር ዘበኞቹ እነዚህን ጋሻዎች አንግበው ያጅቡት ነበር፤ ንጉሡ ከሄደ በኋላም መልሰው በዘበኞች ክፍል ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር፤ ንጉሥ ሮብዓም በደሉን አምኖ ራሱን ስላዋረደ፥ የእግዚአብሔር ቊጣ ሙሉ በሙሉ ጒዳት አላደረሰበትም፤ እንዲያውም በይሁዳ ሁሉ ነገር መልካም ሆነ። ሮብዓም መኖሪያውን እግዚአብሔር ከመላው የእስራኤል ግዛት መካከል ስሙ እንዲጠራባት በመረጣት በኢየሩሳሌም ከተማ አድርጎ፥ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፤ የመንግሥቱንም ሥልጣን አጠናከረ፤ እርሱም በነገሠ ጊዜ፥ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ የሮብዓም እናት ናዕማ ተብላ የምትጠራ የዐሞን አገር ተወላጅ ነበረች፤ ሮብዓም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ጥረት ባለማድረጉ ክፉ ነገር ሠራ። ንጉሥ ሮብዓም ያደረገው ነገር ሁሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ እንዲሁም የቤተሰቡ ታሪክ በነቢዩ ሸማዕያና በነቢዩ ዒዶ ታሪክ መጻሕፍት ተመዝግቦ ይገኛል፤ ሮብዓምና ኢዮርብዓም ባለማቋረጥ ዘወትር ይዋጉ ነበር፤ ሮብዓም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መካነ መቃብርም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አቢያ ነገሠ።