ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 12
12
ግብጽ ይሁዳን መውረርዋ
(1ነገ. 14፥25-28)
1የሮብዓም መንግሥት በጽኑ በተመሠረተና ኀይል ባገኘ ጊዜ እርሱና እስራኤላውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ፤ 2ለእግዚአብሔር የነበራቸውን ታማኝነት በማጓደላቸውም ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ጣለበት። 3እርሱም አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሠረገሎችና ሥልሳ ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሺሻቅ ጦር ሠራዊት ውስጥ ከእርሱ ጋር ከግብጽ የመጡ ብዛታቸው ሊቈጠር የማይቻል ሊቢያውያን፥ ሱካውያንና ኢትዮጵያውያን ነበሩ፤ 4ንጉሥ ሺሻቅ የተመሸጉትን የይሁዳ ከተማዎች ወሮ ያዘ፤ እስከ ኢየሩሳሌምም ድረስ ገሥግሦ መጣ።
5ከዚህ በኋላ ነቢዩ ሸማዕያ ሺሻቅን በመፍራት፥ በኢየሩሳሌም በአንድነት ተሰብስበው ወደ ነበሩ ወደ ንጉሥ ሮብዓምና ወደ ይሁዳ መሪዎች ሄዶ፥ “እግዚአብሔር ‘እኔን ስለ ተዋችሁ እነሆ፥ እኔም በሺሻቅ እጅ እንድትወድቁ ትቼአችኋለሁ’ ይላችኋል” አላቸው።
6ንጉሥ ሮብዓምና የይሁዳ መሪዎችም ኃጢአት መሥራታቸውን በማመን፥ “እግዚአብሔር የሚያደርገው ነገር ሁሉ ትክክል ነው” በማለት ራሳቸውን አዋረዱ።
7እግዚአብሔርም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ፥ ነቢዩ ሸማዕያን እንደገና እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ በደላቸውን አምነው ራሳቸውን ስላዋረዱ፥ አላጠፋቸውም፤ ሺሻቅ አደጋ በሚጥልባቸው ጊዜ፥ ፈጥኜ በመታደግ አድናቸዋለሁ፤ በኢየሩሳሌምም ላይ ቊጣዬን ሙሉ በሙሉ አላወርድም፤ 8ይሁን እንጂ ለእኔ በመገዛትና ለምድር ነገሥታት በመገዛት መካከል ያለውን ልዩነት ይገነዘቡ ዘንድ፥ ሺሻቅ ድል አድርጎ ይገዛቸዋል።”
9ስለዚህ ንጉሥ ሺሻቅ በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም ገብቶ፥ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት የነበረውን ሀብት ሁሉ፥ ንጉሥ ሰሎሞን ከወርቅ ያሠራቸውን ጋሻዎች ጭምር ዘርፎ ወሰደ፤ #1ነገ. 10፥16-17፤ 2ዜ.መ. 9፥15-16። 10ንጉሥ ሮብዓም ሺሻቅ በወሰዳቸው ጋሻዎች ምትክ፥ ሌሎች ጋሻዎችን ከነሐስ አሠርቶ፥ የቤተ መንግሥቱን ቅጽር በሮች በሚጠብቁ የዘበኞች አለቆች ኀላፊነት እንዲቀመጡ አደረገ፤ 11ንጉሡ ወደ ቤተ መቅደስ በመጣ ቊጥር ዘበኞቹ እነዚህን ጋሻዎች አንግበው ያጅቡት ነበር፤ ንጉሡ ከሄደ በኋላም መልሰው በዘበኞች ክፍል ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር፤ 12ንጉሥ ሮብዓም በደሉን አምኖ ራሱን ስላዋረደ፥ የእግዚአብሔር ቊጣ ሙሉ በሙሉ ጒዳት አላደረሰበትም፤ እንዲያውም በይሁዳ ሁሉ ነገር መልካም ሆነ።
የሮብዓም ዘመነ መንግሥት ታሪክ ባጭሩ
13ሮብዓም መኖሪያውን እግዚአብሔር ከመላው የእስራኤል ግዛት መካከል ስሙ እንዲጠራባት በመረጣት በኢየሩሳሌም ከተማ አድርጎ፥ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፤ የመንግሥቱንም ሥልጣን አጠናከረ፤ እርሱም በነገሠ ጊዜ፥ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ የሮብዓም እናት ናዕማ ተብላ የምትጠራ የዐሞን አገር ተወላጅ ነበረች፤ 14ሮብዓም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ጥረት ባለማድረጉ ክፉ ነገር ሠራ።
15ንጉሥ ሮብዓም ያደረገው ነገር ሁሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ እንዲሁም የቤተሰቡ ታሪክ በነቢዩ ሸማዕያና በነቢዩ ዒዶ ታሪክ መጻሕፍት ተመዝግቦ ይገኛል፤ ሮብዓምና ኢዮርብዓም ባለማቋረጥ ዘወትር ይዋጉ ነበር፤ 16ሮብዓም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መካነ መቃብርም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አቢያ ነገሠ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 12: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997