የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 13

13
አቢያ በኢዮርብዓም ላይ ያደረገው ጦርነት
(1ነገ. 15፥1-8)
1ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፥ አቢያ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 2መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱ ሚካያ ተብላ የምትጠራ የጊብዓ ከተማ ተወላጅ የሆነ የኡሪኤል ልጅ ነበረች።
በአቢያና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ተነሥቶ ነበር፤ 3በዚህ ጊዜ አቢያ አራት መቶ ሺህ ሠራዊት ይዞ ሲዘምት፥ ኢዮርብዓም ደግሞ ስምንት መቶ ሺህ ወታደሮችን አሰለፈ።
4ከዚህ በኋላ አቢያ ኰረብታማ በሆነ በኤፍሬም አገር ወደሚገኘው ወደ ጸማራይም ተራራ ወጥቶ ቆመ፤ ድምፁን ከፍ በማድረግም ለኢዮርብዓምና ለእስራኤላውያን በሙሉ እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ አድምጡኝ! 5ዳዊትና ልጆቹ በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም እንደሚነግሡ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር የማይሻር ቃል ኪዳን መግባቱን አታውቁምን? 6ይህ ሆኖ ሳለ፥ የሰሎሞን አሽከር የሆነው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በጌታው በሰሎሞን ላይ ዐመፀ፤ 7ዘግየት ብሎም ኢዮርብዓም የማይረቡ ወሮበሎችን ሰበሰበ፤ እነርሱም በዕድሜው ማነስና በዕውቀት ያልበሰለ በመሆኑ ሊቋቋማቸው የማይችለውን የሰሎሞንን ልጅ ሮብዓምን በረቱበት። 8አሁንም እናንተ እግዚአብሔር ለዳዊት ዘሮች የሰጠውን የመንግሥት ሥልጣን በመድፈር ለመቃወም ዐቅዳችኋል፤ ይህ ዕቅዳችሁ ግቡን እንዲመታ ለማድረግም እጅግ ብዙ የሆነ የጦር ሠራዊት አሰልፋችኋል፤ ለእናንተ አማልክት እንዲሆኑ ኢዮርብዓም ከወርቅ ያሠራቸውን የጥጃ ምስሎች ይዛችሁ መጥታችኋል። 9የእግዚአብሔር ካህናት የሆኑትን የአሮንን ልጆች ሌዋውያንን አባረራችሁ፤ በእነርሱም ምትክ ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ ለራሳችሁ ካህናትን ሾማችኋል፤ አንድ ወይፈንና ሰባት በጎች ይዞ ራሱን ለመለየት ወደ እናንተ የሚመጣውን ማንኛውንም ሰው ሐሰተኞች ለሆኑት አማልክታችሁ ካህን አድርጋችሁ ትሾማላችሁ።
10“እኛ ግን አሁንም እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ከእርሱም ፈቀቅ አላልንም፤ የአሮን ልጆች የሆኑ ካህናትም እግዚአብሔርን ማገልገላቸውን አላቋረጡም፤ ሌዋውያንም እንደ ወትሮው ሁሉ ካህናትን ይረዳሉ፤ 11በየቀኑ ጧትና ማታ መዓዛው ጣፋጭ የሆነውን ዕጣንና የሚቃጠለውን የእንስሳት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያሳርጋሉ፤ በነጻው ገበታም ላይ የመባ ኅብስት ያቀርባሉ፤ ዘወትር ማታ ማታም ከወርቅ በተሠራው መቅረዝ ላይ ያሉትን ቀንዲሎች ያበራሉ፤ እኛ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንፈጽማለን፤ እናንተ ግን እግዚአብሔርን ትታችኋል። 12የእኛ መሪ ራሱ እግዚአብሔር ነው፤ የእግዚአብሔር ካህናትም መለከት ለመንፋት ተዘጋጅተው እዚህ ከእኛ ጋር ይገኛሉ፤ እነርሱ እምቢልታ መንፋት እንደ ጀመሩም እኛ በእናንተ ላይ ጦርነት እንከፍታለን፤ ስለዚህ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ከቶ ድል ማድረግ ስለማትችሉ፥ ከቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ጦርነት አትግጠሙ!”
13በዚህ ጊዜ ኢዮርብዓም ከሠራዊቱ ከፊሉን ከይሁዳ ሠራዊት በስተጀርባ በማድፈጥ፥ አደጋ እንዲጥሉ ሲልክ፥ የቀሩትን ደግሞ የይሁዳን ሠራዊት ፊት ለፊት እንዲገጥሙአቸው አደረገ። 14የይሁዳ ሕዝብም ዙሪያውን ተመልክቶ መከበቡን ባየ ጊዜ እንዲረዳው ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ ካህናቱም እምቢልታ ነፉ፤ 15የይሁዳም ሰዎች ከፍ ባለ ድምፅ እየጮኹ፥ በንጉሥ አቢያ መሪነት አደጋ ጣሉ፤ እግዚአብሔርም ኢዮርብዓምንና የእስራኤልን ሠራዊት ድል አደረገ፤ 16እስራኤላውያንም ከይሁዳ ሰዎች ፊት ሸሹ፤ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ለይሁዳ ሕዝብ አሳልፎ ሰጣቸው፤ 17አቢያና ሠራዊቱ እስራኤላውያንን ድል አድርገው ከፍ ያለ ጒዳት አደረሱባቸው፤ በዚህ ጦርነት ከእስራኤል አምስት መቶ ሺህ ምርጥ ወታደሮች ተገደሉ። 18የይሁዳም ሰዎች በቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ስለ ታመኑ፥ በእስራኤል ላይ ድልን ተቀዳጁ፤ የእስራኤል ልጆች ግን ተዋረዱ።
19አቢያ የኢዮርብዓምን ሠራዊት አሳደደ፤ ከኢዮርብዓም ከተማዎች መካከልም ቤትኤልን፥ ይሻናንና ዔፍሮንን በአካባቢያቸው የሚገኙትን መንደሮች ጭምር በድል አድራጊነት ያዘ፤ 20ከዚያም በኋላ ኢዮርብዓም በአቢያ ዘመነ መንግሥት ኀይሉን ሊያንሠራራ አልቻለም፤ በመጨረሻም እግዚአብሔር በሞት ቀሠፈው።
21አቢያ ግን ይበልጥ እየበረታ ሄደ፤ ዐሥራ አራት ሚስቶችን አግብቶ ኻያ ሁለት ወንዶች ልጆችንና ዐሥራ ስድስት ሴቶች ልጆችን ወለደ፤ 22የቀረው የንጉሥ አቢያ ታሪክ፥ እርሱ የተናገራቸው ቃላትና ያከናወነው ሥራ ሁሉ፥ በነቢዩ ዒዶ የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ