ሮብዓም መንግሥቱን ከመሠረተና ካጸና በኋላ፣ እርሱና እስራኤል ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ። እግዚአብሔርን ካለመታመናቸው የተነሣም፣ ሮብዓም በነገሠ በዐምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። ከግብጽ ዐብረውት የመጡትን ዐሥራ ሁለት ሺሕ ሠረገላዎች፣ ስድሳ ሺሕ ፈረሰኞችና ስፍር ቍጥር የሌላቸውን የሊቢያ፣ የሱኪምና የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዞ፣ የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች በቍጥጥሩ ሥር በማድረግ እስከ ኢየሩሳሌም ዘለቀ። ከዚህ በኋላ ነቢዩ ሸማያ ወደ ሮብዓምና ሺሻቅን ፈርተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡት ወደ ይሁዳ መሪዎች መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ ትታችሁኛል፤ ስለዚህ እኔም በሺሻቅ እጅ ትቼአችኋለሁ’ ” አላቸው። የእስራኤል መሪዎችና ንጉሡ ራሳቸውን በማዋረድ፣ “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው” አሉ። እግዚአብሔርም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሸማያ መጣ፤ “ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ስላዋረዱ እታደጋቸዋለሁ እንጂ አላጠፋቸውም፤ ቍጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም። ይሁን እንጂ እኔን በማገልገልና የሌሎችን አገሮች ነገሥታት በማገልገል መካከል ያለውን ልዩነት ያውቁ ዘንድ፣ ለርሱ ይገዛሉ።” የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ንብረትና የቤተ መንግሥቱን ንብረት ዘርፎ ወሰደ፤ ሰሎሞን ያሠራቸው የወርቅ ጋሻዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ሁሉንም ነገር አጋዘ። ስለዚህ ንጉሥ ሮብዓም እነዚህን ለመተካት ሲል፣ የናስ ጋሻዎች ሠርቶ የቤተ መንግሥቱን ቅጥር በር ለሚጠብቁ የዘብ አለቆች በኀላፊነት ሰጠ። ንጉሡ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ፣ ዘቦቹ ጋሻዎቹን አንግበው ያጅቡት ነበር፤ ከዚያም በዘብ ጥበቃው ክፍል መልሰው ያስቀምጡ ነበር። ሮብዓም ራሱን ዝቅ አድርጎ ስላዋረደ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ ከርሱ ተመለሰ፤ ፈጽሞም አላጠፋውም። በይሁዳም ደግሞ በጥቂቱም ቢሆን መልካም ነገር ተገኝቶ ነበር። ንጉሥ ሮብዓም በሚገባ ተደላድሎ በኢየሩሳሌም በንጉሥነቱ ቀጠለ፣ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ እርሱም እግዚአብሔር ስሙን በዚያ ለማኖር ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጣት በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀምጦም፣ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ናዓማ የተባለች አሞናዊት ነበረች። እግዚአብሔርን ይሻ ዘንድ ልቡን ስላላዘጋጀ ክፉ ነገር አደረገ። ሮብዓም በዘመነ መንግሥቱ ያከናወናቸው ተግባሮች ሁሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ነቢዩ ሸማያ በጻፈው የታሪክ መዝገብና ባለራእዩ አዶ በዘገበው የትውልድ ሐረግ ታሪክ የሚገኝ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር። ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁ አብያም በርሱ ፈንታ ነገሠ።
2 ዜና መዋዕል 12 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ዜና መዋዕል 12
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ዜና መዋዕል 12:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች