2 ዜና መዋዕል 12:1-16
2 ዜና መዋዕል 12:1-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም ሆነ፤ የሮብዓም መንግሥት በጸናች ጊዜ፥ እርሱም በበረታ ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን ሕግ ረሳ፤ እስራኤልም ሁሉ ከእርሱ ጋር ረሱ። ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሱስቀም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። እግዚአብሔርን በድለዋልና፤ ሺህ ሁለት መቶ ሰረገሎችንና ስድሳ ሺህ ፈረሰኞችን ይዞ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ከግብፅ ለመጣው ሕዝብ ቍጥር አልነበረውም፤ እነርሱም የልብያ ሰዎች፥ ሞጠግሊያናውያን፥ የኢትዮጵያም ሰዎች ነበሩ። በይሁዳም የነበሩትን ምሽጎች ከተሞች ያዙ። እስከ ኢየሩሳሌምም ደረሱ። ነቢዩም ሰማያ ወደ ሮብዓምና ከሱስቀም ሸሽተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡት ወደ ይሁዳ መሳፍንት መጥቶ እንዲህ አላቸው፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተ ተዋችሁኝ፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ በግብፅ ንጉሥ በሱስቀም እጅ ተውኋችሁ።” የእስራኤልም መሳፍንትና ንጉሡ አፈሩ፥ “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው” አሉ። እግዚአብሔርም እንደ ተመለሱና እንደ ተፀፀቱ ባየ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል፥ “ከተመለሱ አላጠፋቸውም፤ ከጥቂት ቀንም በኋላ አድናቸዋለሁ፤ ቍጣዬም በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም” ሲል ወደ ሰማያ መጣ። ለእኔ መገዛትንና ለምድር ነገሥታት መገዛትን ያውቃሉና አገልጋዮች ይሆናሉ። የግብፅ ንጉሥ ሱስቀምም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ የእግዚአብሔርንም ቤተ መዛግብትና የንጉሡን ቤተ መዛግብት ወሰደ፤ ሁሉንም ወሰደ፤ ደግሞም ሰሎሞን የሠራቸውን የወርቁን አላባሽ አግሬ ጋሻዎችን ወሰደ። ንጉሡም ሮብዓም በእነርሱ ፋንታ የናስ አላባሽ አግሬ ጋሻዎችን ሠራ፤ ሮብዓምም የንጉሡን ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቃ እጅ አኖራቸው። ንጉሡም ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባ ቍጥር ዘበኞች መጥተው ይሸከሙአቸው ነበር፤ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር። በተፀፀተም ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ ከእርሱ ዘንድ ራቀ፤ ፈጽሞም አላጠፋውም፤ በይሁዳ መልካም ነገር ተገኝቶአልና። ንጉሡም ሮብዓም በኢየሩሳሌም ጸና፤ ንጉሥም ሆነ፤ ሮብዓምም በነገሠ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል ሀገር ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም ዐሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የአሞን ሴት ንዑማ ነበረች። እግዚአብሔርንም ይሻ ዘንድ ልቡን አላቀናም ነበርና ክፉ ነገርን አደረገ። የሮብዓምም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር እነሆ፥ በነቢዩ ሰማያና በባለ ራእዩ በአዶ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ሮብዓምም ከኢዮርብዓም ጋር በዘመኑ ሁሉ ይዋጋ ነበር። ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አብያ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
2 ዜና መዋዕል 12:1-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሮብዓም መንግሥቱን ከመሠረተና ካጸና በኋላ፣ እርሱና እስራኤል ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ። እግዚአብሔርን ካለመታመናቸው የተነሣም፣ ሮብዓም በነገሠ በዐምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። ከግብጽ ዐብረውት የመጡትን ዐሥራ ሁለት ሺሕ ሠረገላዎች፣ ስድሳ ሺሕ ፈረሰኞችና ስፍር ቍጥር የሌላቸውን የሊቢያ፣ የሱኪምና የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዞ፣ የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች በቍጥጥሩ ሥር በማድረግ እስከ ኢየሩሳሌም ዘለቀ። ከዚህ በኋላ ነቢዩ ሸማያ ወደ ሮብዓምና ሺሻቅን ፈርተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡት ወደ ይሁዳ መሪዎች መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ ትታችሁኛል፤ ስለዚህ እኔም በሺሻቅ እጅ ትቼአችኋለሁ’ ” አላቸው። የእስራኤል መሪዎችና ንጉሡ ራሳቸውን በማዋረድ፣ “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው” አሉ። እግዚአብሔርም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሸማያ መጣ፤ “ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ስላዋረዱ እታደጋቸዋለሁ እንጂ አላጠፋቸውም፤ ቍጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም። ይሁን እንጂ እኔን በማገልገልና የሌሎችን አገሮች ነገሥታት በማገልገል መካከል ያለውን ልዩነት ያውቁ ዘንድ፣ ለርሱ ይገዛሉ።” የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ንብረትና የቤተ መንግሥቱን ንብረት ዘርፎ ወሰደ፤ ሰሎሞን ያሠራቸው የወርቅ ጋሻዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ሁሉንም ነገር አጋዘ። ስለዚህ ንጉሥ ሮብዓም እነዚህን ለመተካት ሲል፣ የናስ ጋሻዎች ሠርቶ የቤተ መንግሥቱን ቅጥር በር ለሚጠብቁ የዘብ አለቆች በኀላፊነት ሰጠ። ንጉሡ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ፣ ዘቦቹ ጋሻዎቹን አንግበው ያጅቡት ነበር፤ ከዚያም በዘብ ጥበቃው ክፍል መልሰው ያስቀምጡ ነበር። ሮብዓም ራሱን ዝቅ አድርጎ ስላዋረደ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ ከርሱ ተመለሰ፤ ፈጽሞም አላጠፋውም። በይሁዳም ደግሞ በጥቂቱም ቢሆን መልካም ነገር ተገኝቶ ነበር። ንጉሥ ሮብዓም በሚገባ ተደላድሎ በኢየሩሳሌም በንጉሥነቱ ቀጠለ፣ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ እርሱም እግዚአብሔር ስሙን በዚያ ለማኖር ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጣት በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀምጦም፣ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ናዓማ የተባለች አሞናዊት ነበረች። እግዚአብሔርን ይሻ ዘንድ ልቡን ስላላዘጋጀ ክፉ ነገር አደረገ። ሮብዓም በዘመነ መንግሥቱ ያከናወናቸው ተግባሮች ሁሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ነቢዩ ሸማያ በጻፈው የታሪክ መዝገብና ባለራእዩ አዶ በዘገበው የትውልድ ሐረግ ታሪክ የሚገኝ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር። ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁ አብያም በርሱ ፈንታ ነገሠ።
2 ዜና መዋዕል 12:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም ሆነ፤ የሮብዓም መንግሥት በጸናች ጊዜ፥ እርሱም በበረታ ጊዜ፥ እርሱና እስራኤል ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ። እግዚአብሔርን በድለዋልና ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ ሺህ ሁለት መቶ ሠረገሎችና ስድሳ ሺህ ፈረሰኞች ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። ከእርሱም ጋር ከግብጽ ለመጣው ሕዝብ ቁጥር አልነበረውም፤ እነርሱም የልብያ ሰዎች፥ ሱካውያን፥ የኢትዮጵያ ሰዎችም ነበሩ። ለይሁዳም የነበሩትን ምሽጎች ከተሞች ወሰደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ። ነቢዩም ሸማያ ወደ ሮብዓምና ከሺሻቅ ሸሽተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡባት ወደ ይሁዳ መሳፍንት መጥቶ እንዲህ አላቸው“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘እንናተ ተዋችሁኝ፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ በሺሻቅ እጅ ተውኋችሁ።’” የእስራኤልም መሳፍንትና ንጉሡ“እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፤” ብለው ሰውነታቸውን አዋረዱ። እግዚአብሔርም ሰውነታቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል” ሰውነታቸውን አዋርደዋል፤ አላጠፋቸውም፤ ከጥቂት ቀንም በኋላ አድናቸዋለሁ፤ ቍጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም፤ ነገር ግን ለእኔ መገዛትንና ለምድር ነገሥታት መገዛትን ያውቁ ዘንድ ይገዙለታል” ሲል ወደ ሸማያ መጣ። የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት መዛግብትና የንጉሡን ቤት መዛግብት ወሰደ፤ ሁሉንም ወሰደ፤ ደግሞም ሰሎሞን የሠራቸውን የወርቁን ጋሻዎች ወሰደ። ንጉሡም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ የናስ ጋሻዎችን ሠራ፤ የንጉሡንም ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቃ እጅ አኖራቸው። ንጉሡም ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባ ቍጥር ዘበኞች መጥተው ይሸከሙአቸው ነበር፤ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸ ነበር። ሰውነቱንም ባዋረደ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ ፈጽሞ እንዳያጠፋው ከእርሱ ዘንድ ተመለሰ፤ በይሁዳም ደግሞ መልካም ነገር ተገኘ። ንጉሡም ሮብዓም በኢየሩሳሌም በረታ፤ ንጉሥም ሆነ፤ ሮብዓምም በነገሠ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል አገር ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም ዐሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የአሞን ሴት ናዕማ ነበረች። እግዚአብሔርንም ይሻ ዘንድ ልቡን አላዘጋጀም ነበርና ክፉ ነገር አደረገ። የሮብዓምም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር በነቢዩ ሸማያና በባለ ራዕዩ በአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከልም በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ። ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አብያ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
2 ዜና መዋዕል 12:1-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የሮብዓም መንግሥት በጽኑ በተመሠረተና ኀይል ባገኘ ጊዜ እርሱና እስራኤላውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ፤ ለእግዚአብሔር የነበራቸውን ታማኝነት በማጓደላቸውም ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ጣለበት። እርሱም አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሠረገሎችና ሥልሳ ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሺሻቅ ጦር ሠራዊት ውስጥ ከእርሱ ጋር ከግብጽ የመጡ ብዛታቸው ሊቈጠር የማይቻል ሊቢያውያን፥ ሱካውያንና ኢትዮጵያውያን ነበሩ፤ ንጉሥ ሺሻቅ የተመሸጉትን የይሁዳ ከተማዎች ወሮ ያዘ፤ እስከ ኢየሩሳሌምም ድረስ ገሥግሦ መጣ። ከዚህ በኋላ ነቢዩ ሸማዕያ ሺሻቅን በመፍራት፥ በኢየሩሳሌም በአንድነት ተሰብስበው ወደ ነበሩ ወደ ንጉሥ ሮብዓምና ወደ ይሁዳ መሪዎች ሄዶ፥ “እግዚአብሔር ‘እኔን ስለ ተዋችሁ እነሆ፥ እኔም በሺሻቅ እጅ እንድትወድቁ ትቼአችኋለሁ’ ይላችኋል” አላቸው። ንጉሥ ሮብዓምና የይሁዳ መሪዎችም ኃጢአት መሥራታቸውን በማመን፥ “እግዚአብሔር የሚያደርገው ነገር ሁሉ ትክክል ነው” በማለት ራሳቸውን አዋረዱ። እግዚአብሔርም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ፥ ነቢዩ ሸማዕያን እንደገና እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ በደላቸውን አምነው ራሳቸውን ስላዋረዱ፥ አላጠፋቸውም፤ ሺሻቅ አደጋ በሚጥልባቸው ጊዜ፥ ፈጥኜ በመታደግ አድናቸዋለሁ፤ በኢየሩሳሌምም ላይ ቊጣዬን ሙሉ በሙሉ አላወርድም፤ ይሁን እንጂ ለእኔ በመገዛትና ለምድር ነገሥታት በመገዛት መካከል ያለውን ልዩነት ይገነዘቡ ዘንድ፥ ሺሻቅ ድል አድርጎ ይገዛቸዋል።” ስለዚህ ንጉሥ ሺሻቅ በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም ገብቶ፥ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት የነበረውን ሀብት ሁሉ፥ ንጉሥ ሰሎሞን ከወርቅ ያሠራቸውን ጋሻዎች ጭምር ዘርፎ ወሰደ፤ ንጉሥ ሮብዓም ሺሻቅ በወሰዳቸው ጋሻዎች ምትክ፥ ሌሎች ጋሻዎችን ከነሐስ አሠርቶ፥ የቤተ መንግሥቱን ቅጽር በሮች በሚጠብቁ የዘበኞች አለቆች ኀላፊነት እንዲቀመጡ አደረገ፤ ንጉሡ ወደ ቤተ መቅደስ በመጣ ቊጥር ዘበኞቹ እነዚህን ጋሻዎች አንግበው ያጅቡት ነበር፤ ንጉሡ ከሄደ በኋላም መልሰው በዘበኞች ክፍል ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር፤ ንጉሥ ሮብዓም በደሉን አምኖ ራሱን ስላዋረደ፥ የእግዚአብሔር ቊጣ ሙሉ በሙሉ ጒዳት አላደረሰበትም፤ እንዲያውም በይሁዳ ሁሉ ነገር መልካም ሆነ። ሮብዓም መኖሪያውን እግዚአብሔር ከመላው የእስራኤል ግዛት መካከል ስሙ እንዲጠራባት በመረጣት በኢየሩሳሌም ከተማ አድርጎ፥ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፤ የመንግሥቱንም ሥልጣን አጠናከረ፤ እርሱም በነገሠ ጊዜ፥ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ የሮብዓም እናት ናዕማ ተብላ የምትጠራ የዐሞን አገር ተወላጅ ነበረች፤ ሮብዓም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ጥረት ባለማድረጉ ክፉ ነገር ሠራ። ንጉሥ ሮብዓም ያደረገው ነገር ሁሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ እንዲሁም የቤተሰቡ ታሪክ በነቢዩ ሸማዕያና በነቢዩ ዒዶ ታሪክ መጻሕፍት ተመዝግቦ ይገኛል፤ ሮብዓምና ኢዮርብዓም ባለማቋረጥ ዘወትር ይዋጉ ነበር፤ ሮብዓም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መካነ መቃብርም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አቢያ ነገሠ።
2 ዜና መዋዕል 12:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም ሆነ፤ የሮብዓም መንግሥት በጸናች ጊዜ፥ እርሱም በበረታ ጊዜ፥ እርሱና እስራኤል ሁሉ የጌታን ሕግ ተዉ። በጌታ ላይ አልታመኑምና ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን ሊወጋት ወጣ፥ እርሱም ሺህ ሁለት መቶ ሰረገሎችና ስልሳ ሺህ ፈረሰኞች ይዞ ነበር። ከእርሱም ጋር ከግብጽ ለመጣው ሕዝብ ቍጥር አልነበረውም፤ እነርሱም የልብያ ሰዎች ሱካውያን፥ የኢትዮጵያ ሰዎችም ነበሩ። የይሁዳም የነበሩትን የተመሸጉ ከተሞች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ። ነቢዩም ሸማያ ወደ ሮብዓምና ከሺሻቅ ሸሽተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡባት ወደ ይሁዳ መሳፍንት መጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እንናተ ተዋችሁኝ፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ በሺሻቅ እጅ ተውኋችሁ።’ ” የእስራኤልም መሳፍንትና ንጉሡ፦ “ጌታ ጻድቅ ነው” ብለው ራሳቸውን አዋረዱ። ጌታም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ የጌታ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሸማያ መጣ፦ “ራሳቸውን አዋርደዋል፤ አላጠፋቸውም፤ ከጥቂት ቀንም በኋላ አድናቸዋለሁ፥ ቁጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይወርድም፤ ነገር ግን ለእኔ መገዛትንና ለሌሎች ለምድሪቱ ነገሥታት መገዛትን እንዲያውቁ ለእርሱ ይገዙለታል።” የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ የጌታንም ቤት መዛግብትና የንጉሡን ቤት መዛግብት ወሰደ፤ ሁሉንም ነገር ወሰደ፤ ደግሞም ሰሎሞን የሠራቸውን የወርቁን ጋሻዎች ወሰደ። ንጉሡም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ የናስ ጋሻዎችን ሠራ፥ የንጉሡንም ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቆች እጅ አኖራቸው። ንጉሡም ወደ ጌታ ቤት በገባ ቍጥር ዘበኞች መጥተው ይሸከሙአቸው ነበር፥ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸ ነበር። ራሱንም ባዋረደ ጊዜ የጌታ ቁጣ ፈጽሞ እንዳያጠፋው ከእርሱ ዘንድ ተመለሰ፤ በይሁዳም ደግሞ መልካም ሁኔታ ተፈጠረ። ንጉሡም ሮብዓም በኢየሩሳሌም በረታ ንጉሥም ሆነ፤ ሮብዓምም በነገሠ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ ጌታም ስሙን እንዲያኖርባት ከእስራኤል አገር ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም ዐሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የአሞን ሴት ናዕማ ነበረች። ጌታንም ለመሻት ልቡን አላዘጋጀም ነበርና ክፉ ነገር አደረገ። የሮብዓምም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር በነቢዩ ሸማያና በባለ ራእዩ በአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከልም በዘመናቸው ሁሉ ጦርነት ነበረ። ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አብያ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።