ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 12
12
ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ እንደዘመተ (1ነገ.14፥ 25-28)
1እንዲህም ሆነ፤ የሮብዓም መንግሥት በጸናች ጊዜ፥ እርሱም በበረታ ጊዜ፥ እርሱና እስራኤል ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ። 2እግዚአብሔርን በድለዋልና ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ ሺህ ሁለት መቶ ሠረገሎችና ስድሳ ሺህ ፈረሰኞች ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 3ከእርሱም ጋር ከግብጽ ለመጣው ሕዝብ ቁጥር አልነበረውም፤ እነርሱም የልብያ ሰዎች፥ ሱካውያን፥ የኢትዮጵያ ሰዎችም ነበሩ። 4ለይሁዳም የነበሩትን ምሽጎች ከተሞች ወሰደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ። 5ነቢዩም ሸማያ ወደ ሮብዓምና ከሺሻቅ ሸሽተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡባት ወደ ይሁዳ መሳፍንት መጥቶ እንዲህ አላቸው“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘እንናተ ተዋችሁኝ፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ በሺሻቅ እጅ ተውኋችሁ።’” 6የእስራኤልም መሳፍንትና ንጉሡ“እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፤” ብለው ሰውነታቸውን አዋረዱ። 7እግዚአብሔርም ሰውነታቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል” ሰውነታቸውን አዋርደዋል፤ አላጠፋቸውም፤ ከጥቂት ቀንም በኋላ አድናቸዋለሁ፤ ቍጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም፤ 8ነገር ግን ለእኔ መገዛትንና ለምድር ነገሥታት መገዛትን ያውቁ ዘንድ ይገዙለታል” ሲል ወደ ሸማያ መጣ።
9የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት መዛግብትና የንጉሡን ቤት መዛግብት ወሰደ፤ ሁሉንም ወሰደ፤ ደግሞም ሰሎሞን የሠራቸውን የወርቁን ጋሻዎች ወሰደ። 10ንጉሡም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ የናስ ጋሻዎችን ሠራ፤ የንጉሡንም ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቃ እጅ አኖራቸው። 11ንጉሡም ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባ ቍጥር ዘበኞች መጥተው ይሸከሙአቸው ነበር፤ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸ ነበር። 12ሰውነቱንም ባዋረደ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ ፈጽሞ እንዳያጠፋው ከእርሱ ዘንድ ተመለሰ፤ በይሁዳም ደግሞ መልካም ነገር ተገኘ።
የሮብዓም ዘመነ መንግሥት ታሪክ ባጭሩ 1ነገ.14፥ 29-31)
13ንጉሡም ሮብዓም በኢየሩሳሌም በረታ፤ ንጉሥም ሆነ፤ ሮብዓምም በነገሠ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል አገር ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም ዐሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የአሞን ሴት ናዕማ ነበረች። 14እግዚአብሔርንም ይሻ ዘንድ ልቡን አላዘጋጀም ነበርና ክፉ ነገር አደረገ።
15የሮብዓምም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር በነቢዩ ሸማያና በባለ ራዕዩ በአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከልም በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ። 16ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አብያ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 12: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ