ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 11
11
ነቢዩ ሸማያ ሮበዓምን እንዳስጠነቀው (1ነገ.12፥21-24)
1ሮብዓምም ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ እስራኤልን ወግተው መንግስቱን ወደ ሮብዓም ይመልሱ ዘንድ ከይሁዳና ከብንያም ቤት የተመረጡትን አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ሰልፈኞች ሰዎች ሰበሰበ። 2የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሸማያ እንዲህ ሲል መጣ 3“ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም፥ በይሁዳና በብንያምም ላሉት ለእስራኤል ሁሉ 4እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ይህ ነገር ከእኔ ዘንድ ነውና አትውጡ፤ ወንድሞቻችሁንም አትውጉ፤ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ይመለስ፤’ ብለህ ንገራቸው።” የእግዚአብሔርንም ቃል ሰሙ፤ በኢዮርብዓምም ላይ ከመሄድ ተመለሱ።
ሮብዓም ለይሁዳ ከተሞች ምሽግ እንደሠራ
5ሮብዓምም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሠራ። 6በይሁዳና በብንያም ያሉትንም የተመሸጉትን ከተሞች ቤተልሔምን፥ ኤጣምን፥ ቴቁሔን፥ 7ቤትጹርን፥ ሦኮን፥ ዓዶላምን፥ 8ጌትን፥ መሪሳን፥ ዚፍን፥ 9አዶራይምን፥ ለኪሶን፥ ዓዜቃን፥ 10ጾርዓን፥ ኤሎንን፥ ኬብሮንን ሠራ። 11ምሽጎቹንም አጠነከረ፤ አለቆችንም አኖረባቸው፤ ምግቡን፥ ዘይቱን፥ የወይን ጠጁንም አከማቸባቸው። 12በከተሞቹ ሁሉ ጋሻና ጦርን አኖረ፤ ከተሞቹንም እጅግ አጠነከራቸው፤ ይሁዳና ብንያምም የእርሱ ወገን ነበሩ።
ካህናትና ሌዋውያን ከእስራኤል እንደመጡና ሮብዓምን እንደረዱ
13በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ የነበሩ ካህናትና ሌዋውያን ከየአገራቸው ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። 14የእግዚአብሔርም ካህናት እንዳይሆኑ ኢዮርብዓምና ልጆቹ አስለቅቀዋቸው ነበርና ሌዋውያን መሰማርያቸውንና ቦታቸውን ትተው ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 15እርሱ ግን ለኮረብታው መስገጃዎች፥ ለአጋንንቱ፥ ለሠራቸውም እምቦሶች ካህናትን አቆመ። 16ደግሞም ለአባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር ይሠዉ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልባቸውን የሰጡ ሁሉ እነርሱን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 17ሦስት ዓመት በዳዊትና በሰሎሞን መንገድ ይሄዱ ነበርና ሦስት ዓመት የይሁዳን መንግሥት አበረቱ፤ የሰሎሞንንም ልጅ ሮብዓምን አጸኑ።
የሮብዓም በቴሰብ
18ሮብዓምም መሐላትን አገባ፤ አባትዋ የዳዊት ልጅ ኢያሪሙት ነበረ፤ እናትዋም የእሴይ ልጅ፥ የኤልያብ ልጅ አቢካኢል ነበረች። 19እርስዋም የዑስን፥ ሰማራያን፥ ዘሃምን ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 20ከእርስዋም በኋላ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን አገባ፤ እርስዋም አብያን፥ ዓታይን፥ ዚዛንና ሰሎሚትን ወለደችለት። 21ሮብዓምም ከሚስቶቹና ከቁባቶቹ ሁሉ ይልቅ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን ወደደ፤ ዐሥራ ስምንትም ሚስቶችና ስድሳ ቁባቶች ነበሩት፤ ሀያ ስምንት ወንዶችና ስድሳ ሴቶች ልጆች ወለደ። 22ሮብዓምም ንጉሥ ያደርገው ዘንድ አስቦአልና የመዓካን ልጅ አብያን በወንድሞቹ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው። 23ተጠበበም፤ ልጆቹንም ሁሉ በይሁዳና በብንያም አገር ሁሉ በምሽጉ ከተሞች ሁሉ ከፋፈላቸው፤ ብዙም ምግብ ሰጣቸው፤ ብዙም ሚስቶች ፈለገላቸው።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 11: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ