ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 10
10
በሰሜን ግዛት የሚኖሩ የእስራኤል ነገዶች ማመፅ
(1ነገ. 12፥1-20)
1እስራኤልም ሁሉ ያነግሡት ዘንድ ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ። 2የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ሸሽቶ በግብጽ ይኖር ነበርና ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮርብዓም ከግብጽ ተመለሰ። 3ልከውም ጠሩት፤ ኢዮርብዓምና እስራኤልም ሁሉ መጥተው ሮብዓምን 4“አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቅልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን፤” ብለው ተናገሩት። 5እርሱም “ከሦስት ቀን በኋላ ወደ እኔ ተመለሱ፤” አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ።
6ንጉሡም ሮብዓም “ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው?” ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወት ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ። 7እነርሱም “ለዚህ ሕዝብ ቸርነት ብታደርግላቸው፥ ደስም ብታሰኛቸው፥ በገርነትም ብትናገራቸው፥ ለዘላለም ባሪያዎች ይሆኑልሃል” ብለው ተናገሩት። 8እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ነገር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ። 9እርሱም “‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልን’ ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው?” አላቸው። 10ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች “‘አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አንተ ግን አቅልልልን፤’ ለሚሉህ ሕዝብ ‘ታናሽቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፤ 11አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ፤’ በላቸው፤” ብለው ተናገሩት።
12ንጉሡም “በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ፤” ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓብ መጡ። 13ንጉሡም ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው፤ ንጉሡም ሮብዓም የሽማግሌዎቹን ምክር ትቶ 14“አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፤ እኔ ግን እጨምርበታለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ፤” ብሎ እንደ ብላቴኖቹ ምክር ተናገራቸው። 15እግዚአብሔርም በሴሎናዊው በአሒያ አድርጎ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ቃል እንዲያጸና ከእግዚአብሔር ዘንድ ተወስኖ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።
16እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ እንዳልሰማቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ “በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም፤ እስራኤል ሆይ! ወደ እየድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ! አሁን ቤትህን ተመልከት፤” በለው ለንጉሡ መለሱለት። እስራኤልም ሁሉ ወደ እየድንኳኖቻቸው ሄዱ። 17በይሁዳ ከተሞች በተቀመጡት በእስራኤል ልጆች ላይ ግን ሮብዓም ነገሠባቸው። 18ንጉሡም ሮብዓም አስገባሪውን አዶራምን ሰደደ፤ የእስራኤልም ልጆች በድንጋይ ወገሩት፤ ሞተም፤ ንጉሡም ሮብዓም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ወጣ ወደ ኢየሩሳሌምም ሸሸ። 19እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከዳዊት ቤት ሸፈተ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 10: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ