ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 9

9
የንግሥተ ሳባ ጕብኝት
(1ነገ. 9፥10-28)
1የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በግመሎች ላይ ሽቱና ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ሰሎሞንን በኢየሩሳሌም በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች፤ ወደ ሰሎሞንም በገባች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። 2ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሰሎሞንም ያልፈታው ስውር ነገር አልነበረም። 3የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፥ 4የማዕዱንም መብል፥ የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም አሠራር አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም አለባበሳቸውንም፥ በእግዚአብሔርም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ መንፈስ አልቀረላትም። 5ንጉሡንም አለችው “ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። 6እኔ ግን መጥቼ በዐይኔ እስካየሁ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም፤ እነሆ፥ የጥበብህን ታላቅነት እኵሌታ አልነገሩኝም፤ ከሰማሁት ዝና ትበልጣለህ። 7በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙ ጥበብህንም የሚሰሙ ሰዎችህና እነዚህ ባሪያዎችህ ምስጉኖች ናቸው። 8በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ንጉሥ እንድትሆን በዙፋኑ ላይ ያስቀምጥህ ዘንድ የወደደህ አምላክህ እግዚአብሔር ብሩክ ይሁን፤ አምላክህ እስራኤልን ለዘላለም ያጸናቸው ዘንድ ወድዶአቸዋልና ስለዚህ ፍርድና ጽድቅ ታደርግ ዘንድ በላያቸው አነገሠህ።”
9ለንጉሡም መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ፥ እጅግም ብዙ ሽቱ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባም ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ ሽቱ ከቶ አልነበረም። 10ከኦፊርም ወርቅ ያመጡ የኪራም ባሪያዎችና የሰሎሞን ባሪያዎች የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቍ ደግሞ አመጡ። 11ንጉሡም ከሰንደሉ እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና ለንጉሡ ቤት ደርብ፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና አደረገ፤ እንደዚህም ያለ በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም ነበር። 12የሳባም ንግሥት ወደ ንጉሡ ካመጣችው የሚበልጥ፥ ንጉሡ ሰሎሞን የወደደችውን ሁሉ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ ሰጣት፤ እርስዋም ተመልሳ ከባሪያዎችዋ ጋር ወደ ምድርዋ ሄደች።
የንጉሥ ሰሎሞን ሀብት ብዛት
(1ነገ. 10፥14-25)
13ነጋድራሶችና ነጋዴዎች ካመጡለት ሌላ በየዓመቱ ወደ ሰሎሞን የሚመጣ የወርቅ ሚዛን ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበረ። 14የዓረብም ነገሥታት ሁሉ የምድሩም ሹማምት ወርቅና ብር ወደ ሰሎሞን ያመጡ ነበር። 15ንጉሡም ሰሎሞን በጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ አላባሽ አግሬ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም አላባሽ አግሬ ጋሻ ውስጥ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበረ። 16ከጥፍጥም ወርቅ ሦስት መቶ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም ጋሻ የገባው ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበረ፤ ንጉሡም የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤት ውስጥ አኖራቸው። 17ንጉሡም ደግሞ ከዘሆን ጥርስ ታላቅ ዙፋን አሠራ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው። 18ከዙፋኑም ጋር ተጋጥመው ወደ ዙፋኑም የሚያስሄዱ ስድስት እርከኖች ነበሩ፤ የወርቅ ብርኩማም ነበረ፤ በዚህና በዚያም በመቀመጫው አጠገብ ሁለት የክንድ መደገፊያዎች ነበሩበት፤ በመደገፊያዎችም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር። 19በስድስቱም እርከኖች ላይ በዚህና በዚያ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በመንግሥታት ሁሉ እንዲህ ያለ ሥራ አልተሠራም። 20ንጉሡም ሰሎሞን የሚጠጣበት ዕቃ ሁሉ የወርቅ ነበረ፤ የሊባኖስ ዱር በተባለውም ቤቱ የነበረው ዕቃ ሁሉ ጥሩ ወርቅ ነበረ፤ በሰሎሞን ዘመን ብር ከቶ አይቈጠርም ነበር። 21ለንጉሡም ከኪራም ባሪያዎች ጋር ወደ ተርሴስ የሚሄዱ መርከቦች ነበሩት፤ በሦስት በሦስት ዓመትም አንድ ጊዜ የተርሴስ መርከቦች ወርቅና ብር የዝሆንም ጥርስ ዝንጀሮና ዝንጕርጕር ወፍም ይዘው ይመጡ ነበር።
22ንጉሡም ሰሎሞን ከምድር ነገሥታት ሁሉ በባለጠግነትና በጥበብ በለጠ። 23የምድርም ነገሥታት ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበቡን ይሰሙ ዘንድ የሰሎሞንን ፊት ሊያዩ ይመኙ ነበር። 24እያንዳንዱም ገጸ በረከቱን፥ የወርቅንና የብርን ዕቃ፥ ልብስንና የጦር መሣሪያን፥ ሽቱውንም፥ ፈረሶችንና በቅሎችን እየያዘ በየዓመቱ ያመጣ ነበር። 25ሰሎሞንም ለፈረሶችና ለሠረገሎች አራት ሺህ ጋጥ፥ ዐሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፥ በሠረገሎችም ከተሞች፥ ከንጉሡም ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። 26ከኤፍራጥስም ወንዝ ጀምሮ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብጽ ዳርቻ ድረስ ባሉ ነገሥታት ሁሉ ላይ ነገሠ። 27ንጉሡም ብሩን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባውንም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ አደረገው። 28ለሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብጽና ከየአገሩ ሁሉ ያመጡለት ነበር።
የሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ
(1ነገ. 11፥41-43)
29የቀረውም ፊተኛውና ኋለኛው የሰሎሞን ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክ፥ በሴሎናዊውም በአሒያ ትንቢት፥ ስለ ናባጥም ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው በባለ ራእዩ በአዶ ራእይ የተጻፈ አይደለምን? 30ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም በእስራኤል ሁሉ ላይ አርባ ዓመት ነገሠ። 31ሰሎሞንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ