2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 12

12
ግብጽ ይሁዳን ማጥቃትዋ
1እንዲህም ሆነ፤ የሮብዓም መንግሥት በጸናች ጊዜ፥ እርሱም በበረታ ጊዜ፥ እርሱና እስራኤል ሁሉ የጌታን ሕግ ተዉ። 2በጌታ ላይ አልታመኑምና ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን ሊወጋት ወጣ፥ 3እርሱም ሺህ ሁለት መቶ ሰረገሎችና ስልሳ ሺህ ፈረሰኞች ይዞ ነበር። ከእርሱም ጋር ከግብጽ ለመጣው ሕዝብ ቍጥር አልነበረውም፤ እነርሱም የልብያ ሰዎች ሱካውያን፥ የኢትዮጵያ ሰዎችም ነበሩ። 4የይሁዳም የነበሩትን የተመሸጉ ከተሞች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ። 5ነቢዩም ሸማያ ወደ ሮብዓምና ከሺሻቅ ሸሽተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡባት ወደ ይሁዳ መሳፍንት መጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እንናተ ተዋችሁኝ፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ በሺሻቅ እጅ ተውኋችሁ።’ ” 6የእስራኤልም መሳፍንትና ንጉሡ፦ “ጌታ ጻድቅ ነው” ብለው ራሳቸውን አዋረዱ። 7ጌታም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ የጌታ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሸማያ መጣ፦ “ራሳቸውን አዋርደዋል፤ አላጠፋቸውም፤ ከጥቂት ቀንም በኋላ አድናቸዋለሁ፥ ቁጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይወርድም፤ 8ነገር ግን ለእኔ መገዛትንና ለሌሎች ለምድሪቱ ነገሥታት መገዛትን እንዲያውቁ ለእርሱ ይገዙለታል።”
9 # 1ነገ. 10፥16፤17፤ 2ዜ.መ. 9፥15፤16። የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ የጌታንም ቤት መዛግብትና የንጉሡን ቤት መዛግብት ወሰደ፤ ሁሉንም ነገር ወሰደ፤ ደግሞም ሰሎሞን የሠራቸውን የወርቁን ጋሻዎች ወሰደ። 10ንጉሡም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ የናስ ጋሻዎችን ሠራ፥ የንጉሡንም ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቆች እጅ አኖራቸው። 11ንጉሡም ወደ ጌታ ቤት በገባ ቍጥር ዘበኞች መጥተው ይሸከሙአቸው ነበር፥ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸ ነበር። 12ራሱንም ባዋረደ ጊዜ የጌታ ቁጣ ፈጽሞ እንዳያጠፋው ከእርሱ ዘንድ ተመለሰ፤ በይሁዳም ደግሞ መልካም ሁኔታ ተፈጠረ።
ንጉሥ ሮብዓም መሞቱ
13ንጉሡም ሮብዓም በኢየሩሳሌም በረታ ንጉሥም ሆነ፤ ሮብዓምም በነገሠ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ ጌታም ስሙን እንዲያኖርባት ከእስራኤል አገር ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም ዐሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የአሞን ሴት ናዕማ ነበረች። 14ጌታንም ለመሻት ልቡን አላዘጋጀም ነበርና ክፉ ነገር አደረገ።
15የሮብዓምም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር በነቢዩ ሸማያና በባለ ራእዩ በአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከልም በዘመናቸው ሁሉ ጦርነት ነበረ። 16ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አብያ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ