2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 13

13
አብያ በይሁዳ ላይ መንገሡ
1ንጉሡም ኢዮርብዓም በነገሠ በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ። 2ሦስት ዓመት በኢየሩሳሌም ነገሠ፤ የእናቱም ስም ሚካያ ነበረ፥ የገብዓ ሰው የኡርኤል ልጅ ነበረች። በአብያና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበረ። 3አብያም የተመረጡትን አራት መቶ ሺህ ኃያላን ተዋጊዎች ይዞ ወደ ጦርነት ወጣ፤ ኢዮርብዓምም የተመረጡትን ስምንት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ይዞ በእርሱ ላይ ተሰለፈ። 4አብያም በተራራማው በኤፍሬም አገር ባለው በጽማራይም ተራራ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ፦ “ኢዮርብዓምና እስራኤል ሁሉ ሆይ! ስሙኝ፤ 5የእስራኤል አምላክ ጌታ በእስራኤል ላይ መንግሥትን ለዳዊትና ለልጆቹ የጨው ቃል ኪዳን ለዘለዓለም እንደሰጠ በውኑ አታውቁምን? 6የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ባርያ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ግን ተነሥቶ በጌታው ላይ ዓመፀ። 7ክፉዎች ሰዎችና ምናምንቴዎችም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሮብዓም ሕፃንና ለጋ በነበረበት ጊዜ፥ ሊቋቋማቸውም ባልቻለበት ጊዜ፥ በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ላይ በረቱበት።
8“እንግዲህ አሁን እናንተ እጅግ ታላቅ ሕዝብ ናችሁና፥ ኢዮርብዓምም አማልክት አድርጎ የሠራላችሁ የወርቅ እምቦሶች ከእናንተ ጋር ናቸውና በዳዊት ልጆች እጅ የሚሆነውን የጌታን መንግሥት ልትቋቋሙ ታስባላችሁ። 9የአሮንን ልጆች የጌታን ካህናትና ሌዋውያንን አላሳደዳችሁምን? እንደ ሌሎችም አሕዛብ ልማድ ለራሳችሁ ካህናትን አልሾማችሁምን? አንድ ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ይዞ ለመቀደስ የሚመጣ ሁሉ አማልክት ላልሆኑት ለእነዚያ ካህን ይሆናል። 10ለእኛ ግን አምላካችን ጌታ ነው፥ አልተውነውም፤ የጌታም አገልጋዮች የአሮን ልጆች ካህናቱ ሌዋውያኑም በሥራቸው ከእኛ ጋር ናቸው። 11በየጥዋቱና በየማታውም ለጌታ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና መዓዛው ያማረ ዕጣን ያሳርጋሉ፤ የተቀደሰውንም ኅብስት በንጹሕ ገበታ ላይ፥ የወርቁን መቅረዝና ቀንዲሎቹንም ማታ ማታ እንዲያበሩ ያዘጋጃሉ፤ እኛም የአምላካችንን የጌታን ትእዛዝ እንጠብቃለን፥ እናንተ ግን ትታችሁታል። 12እነሆም፥ ጌታ በእኛ ላይ አለቃ ነው፥ መለከቱንም የሚነፉ ካህናቱ ከእኛ ጋር ናቸው፥ በእናንተም ላይ የጦርነት ማስጠንቀቅያ ድምፅ ያሰማሉ። የእስራኤል ልጆች ሆይ! አይበጃችሁምና ከአባቶቻችሁ አምላክ ከጌታ ጋር አትዋጉ።”
13ኢዮርብዓም ግን ድብቅ ጦር በስተ ኋላቸው አዞረ፤ እነርሱ በይሁዳ ፊት ለፊት ሆነው ድብቅ ጦሩ ግን በስተ ኋላቸው ነበረ። 14ይሁዳም ወደ ኋላው በተመለከተ ጊዜ፥ እነሆ፥ ጦርነቱ በፊቱና በኋላው ነበረ፤ ወደ ጌታም ጮኹ፥ ካህናቱም መለከቱን ነፉ። 15የይሁዳም ሰዎች ጮኹ፤#13፥15 አቅራሩ፤ የይሁዳም ሰዎች በጮኹ ጊዜ ጌታ ኢዮርብዓምንና እስራኤልን ሁሉ በአብያና በይሁዳ ፊት ድል አደረጋቸው። 16የእስራኤልም ልጆች ከይሁዳ ፊት ሸሹ፥ ጌታም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። 17አብያና ሕዝቡ በታላቅ ውግያ ድል አደረጓቸው፤ ከእስራኤልም አምስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች ተገድለው ወደቁ። 18በዚያም ጊዜ የእስራኤል ልጆች ተዋረዱ፥ የይሁዳም ልጆች በአባቶቻቸው አምላክ በጌታ ታምነው ነበርና አሸነፉ። 19አብያም ኢዮርብዓምን አሳደደው፥ ከእርሱም ከተሞቹን፥ ቤቴልንና መንደሮችዋን፥ ይሻናንና መንደሮችዋን፥ ዔፍሮንንና መንደሮችዋን ወሰደ። 20ኢዮርብዓምም ከዚያ በኋላ በአብያ ዘመን አልበረታም፤ ጌታም ቀሰፈው፥ ሞተም። 21አብያም ጸና፥ ዐሥራ አራትም ሚስቶች አገባ፥ ሀያ ሁለትም ወንዶች ልጆችንና ዐሥራ ስድስት ሴቶች ልጆች ወለደ። 22የአብያም የቀረው ነገርና አካሄዱ የተናገራቸውም ቃሎች በነቢዩ በአዶ መጽሐፍ ተጽፈዋል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ