ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በሕዝቡ ፊት ተነሥቶ በመሠዊያው ፊት ለፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ለአገልጋዮቹ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅና ከልባቸው ታማኞች እስከ ሆኑ ድረስ ፍቅሩን የሚያጸና በላይ በሰማይ በታችም በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም! ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውንም የተስፋ ቃል አጽንተሃል፤ የተናገርከውም ቃል ሁሉ እነሆ ዛሬ ተፈጽሞአል፤ አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ለአባቴ ለዳዊት ‘አንተ ታደርግ በነበረው ዐይነት ልጆችህ ታዛዦች ቢሆኑና በፊቴም በቅንነት ቢመላለሱ ሁልጊዜ ከዘርህ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚነግሥ ልጅ አላሳጣህም’ ስትል የተናገርከውን የተስፋ ቃል ፈጽም! አሁንም የእስራኤል አምላክ ሆይ! አገልጋይህ ለነበረው ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ሁሉ እንዲፈጸም አድርግ። “በውኑ እግዚአብሔር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ ሰማያት፥ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ሊይዝህ አይችልም፤ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ? ይሁን እንጂ፥ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! ወደ አገልጋይህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፤ ዛሬም አገልጋይህ በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ። ስሜ ይጠራበታል ወዳልከው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቀንና ሌሊት ተመልከት፤ እኔም አገልጋይህ ወደዚህ ቤተ መቅደስ የምጸልየውን ጸሎት ስማ። ፊታችንን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መልሰን በምንጸልይበት ጊዜ የእኔንና የሕዝብህን ጸሎት ስማ፤ ከመኖሪያህ ከሰማይ ሆነህ ስማን፤ ይቅርም በለን። “አንድ ሰው ባልንጀራውን መበደሉን የሚገልጥ ክስ ቀርቦበት በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ ወደሚገኘው መሠዊያ አምጥተውት ከበደል ንጹሕ መሆኑን በመሐላ በሚያረጋግጥበት ጊዜ፥ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ለአገልጋዮችህም ፍርድን ስጥ፤ ይኸውም በደል የሠራው ሰው በጥፋቱ መጠን እንዲቀጣ፥ ንጹሑም ነጻ እንዲወጣ አድርግ። “ሕዝብህ እስራኤል በደል ሠርተው አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት በጠላቶቻቸው ድል ሲሆኑ ተጸጽተውም ወደ አንተ በመመለስ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢመጡና የአንተን ይቅርታ ለማግኘት ራሳቸውን ዝቅ አድርገው በትሕትና ቢለምኑህ፥ አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ በምርኮ የሚገኙትንም ሕዝብህን ኃጢአት ይቅር በማለት ለቀድሞ አባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር መልሰህ አግባቸው። “ሕዝብህ በደል ሠርተው አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት ዝናብ እንዳይዘንብላቸው አድርገህ በምትቀጣቸው ጊዜ፥ በፈጸሙት በደል በመጸጸት ፊታቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መልሰው በትሕትና ቢለምኑህ፥ አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ የአገልጋዮችህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ቅን የሆነውንም ነገር ማድረግ ይችሉ ዘንድ አስተምራቸው፤ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሆይ፥ ለዘለዓለም ርስት አድርገህ ለሕዝብህ በሰጠሃቸው በዚህች ምድር ዝናብ እንዲዘንብ አድርግ። “በምድሪቱ ላይ ረሀብ ወይም ቸነፈር በሚመጣበት ጊዜ፥ እንዲሁም በውርጭ በዋግና በአንበጣ ወይ በኩብኩባ መንጋ በሚወድምበት ጊዜ፥ ወይም ጠላቶቻቸው በሕዝብ ላይ አደጋ በሚጥሉበት ጊዜ፥ ወይም በሕዝብህ ላይ ልዩ በሽታና ደዌ በሚደርስባቸው ጊዜ፥ ጸሎታቸውን ስማ፤ በሕዝብህ በእስራኤል መካከል ልብን የሚያሸብር መራር ሐዘን ደርሶባቸው እጃቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ በመዘርጋት በሚጸልዩበት ጊዜ፥ ጸሎታቸውን ስማ፤ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን በመስማት በደላቸውን ይቅር በላቸው፤ ርዳቸውም፤ በሰው ልብና አእምሮ ያለውን ሐሳብ ሁሉ መርምረህ የምታውቅ አንተ ብቻ ነህ፤ ስለዚህ ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የሚገባውን ዋጋ ስጠው፤ በዚህም ዐይነት ሕዝብህ ለቀድሞ አባቶቻችን ርስት አድርገህ በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ለአንተ ታዛዦች እንዲሆኑና እንዲያከብሩህ አድርግ። “በሩቅ አገር የሚኖር የውጪ አገር ሰው የስምህን ገናናነትና ለሕዝብህ ያደረግኸውን ድንቅ ነገር ሁሉ ሰምቶ፥ በዚህ ቤተ መቅደስ ሊያመልክህና ሊጸልይ ቢመጣ፥ አንተ ጸሎቱን ስማ፤ ሕዝብህ እስራኤላውያን እንደሚያደርጉት በመላው ዓለም የሚኖሩ ሕዝቦች አንተን በማወቅ እንዲታዘዙህና እንዲያከብሩህ አድርግ፥ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ የዚህን ሰው ጸሎት ስማ፤ እንድታደርግለት የሚለምንህንም ሁሉ ፈጽምለት፤ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ይህ እኔ የሠራሁት ቤተ መቅደስ የአንተ ስም የሚጠራበት መሆኑን ያውቃሉ። “ጠላቶቻቸውን ለመውጋት እንዲዘምቱ ሕዝብህን በምታዝበት ጊዜ በየትኛውም ስፍራ ሆነው ወደዚህች ወደ መረጥኻት ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው በሚጸልዩበት ጊዜ፥ በሰማይም ሆነህ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በመስማት ዓላማቸውን ደግፍ። “መቼም በደል የማይሠራ የለምና ሕዝብህ ኃጢአት በመሥራት አንተን ሲያሳዝኑህ፥ አንተም ተቈጥተህ ጠላቶቻቸው ድል እንዲነሡአቸውና ወደ ሌላ አገር ማርከው እንዲወስዱአቸው በምትፈቅድበት ጊዜ፥ ምንም እንኳ ያ አገር ሩቅ ቢሆን፥ ምርኮኞች ሆነው በሚኖሩባት በዚያች አገር ሳሉ ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ዐምፀናልም’ ብለው በመናዘዝ ተጸጽተው ንስሓ ቢገቡ፥ ማርከው በወሰዱአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸው በእውነትና በቅን መንፈስ ተጸጽተው ንስሓ በመግባት አንተ ለቀድሞ አባቶቻችን ወደ ሰጠሃቸው ወደዚህች ምድር፥ አንተም ወደ መረጥኻት ወደዚህች ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፥ በመኖሪያህ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን በመስማት ፍረድላቸው፤ ኃጢአታቸውንና አንተን ያሳዘኑበትን ዐመፅ ሁሉ ይቅር በል፤ ጠላቶቻቸውም እንዲራሩላቸው አድርግ፤ እነርሱ እኮ እንደ እቶን እሳት ከምታቃጥል ከግብጽ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህ ናቸው። “በጠሩህ ጊዜ ሁሉ ትሰማቸው ዘንድ ለአገልጋይህና ለሕዝብህ ልመና ዐይኖችህ የተገለጡ ይሁኑ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! የቀድሞ አባቶቻችንን ከግብጽ ምድር ባወጣህ ጊዜ ከዓለም ሕዝብ ሁሉ መካከል እስራኤልን የራስህ ሕዝብ እንዲሆን የመረጥከው መሆኑን በአገልጋይህ በሙሴ አማካይነት ተናግረሃል።”
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 8 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 8:22-53
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች