አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 8:22-53

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 8:22-53 አማ54

የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ እያዩ ሰሎሞን በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆሞ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ። እንዲህም አለ “የእስራኤል አምላክ አቤቱ! በላይ በሰማይ በታችም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፤ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ ባሪያዎችህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ የጠበቅህ፤ በአፍህ ተናገርህ፤ እንደ ዛሬው ቀንም በእጅህ ፈጸምኸው። አሁንም የእስራኤል አምላክ አቤቱ! ‘አንተ በፊቴ እንደ ሄድህ ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው በፊቴ አታጣም፤’ ብለህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ ጠብቅ። አሁንም፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ! ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የተናገርኸው ቃል፥ እባክህ፥ ይጽና። “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ! ነገር ግን፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ! ወደ ባሪያህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፤ ዛሬም ባሪያህ በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ፤ ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ‘በዚያ ስሜ ይሆናል፤’ ወዳልኸው ስፍራ ወደዚህ ቤት ዐይኖችህ ሌሊትና ቀን የተገለጡ ይሁኑ። ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል። “ሰው ባልንጀራውን ቢበድል፥ በላዩም መሐላ ቢጫን፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በመሠዊያህ ፊት ቢምል፥ በሰማይ ስማ፤ አድርግም፤ በባሪያዎችህም ላይ ዳኛ ሁን፤ በበደለኛውም ላይ ፍረድ፤ መንገዱንም በራሱ ላይ መልስበት፤ ንጹሑን አጽደቀው፤ እንደ ጽድቁም ክፈለው። “ሕዝብህ እስራኤል አንተን ስለ በደሉ በጠላቶቻቸው ፊት ድል በተመቱ ጊዜ፥ ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ በዚህም ቤት ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥ አንተ በሰማይ ስማ፤ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ምድር መልሳቸው። “አንተን ስለ በደሉ ሰማይ በተዘጋ ጊዜ፥ ዝናብም ባልዘነበ ጊዜ፥ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ ባስጨነቅሃቸውም ጊዜ ከኀጢአታቸው ቢመለሱ፥ አንተ በሰማይ ስማ፤ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ በማሳየት የባሪያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለሕዝብህም ርስት አድርገህ ለሰጠሃት ምድር ዝናብ ስጥ። “በምድር ላይ ራብ፥ ወይም ቸነፈር፥ ወይም ዋግ፥ ወይም አረማሞ፥ ወይም አንበጣ፥ ወይም ኩብኩባ ቢሆን፥ የሕዝብህም ጠላት የአገሩን ቀበሌዎች ከብቦ ቢያስጨንቃቸው፥ መቅሠፍትና ደዌ ሁሉ ቢሆን፥ ማናቸውም ሰው የልቡን ሕመም አውቆ ጸሎትና ልመና ቢጸልይ፥ እጆቹንም ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ፥ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ይፈሩህ ዘንድ፥ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ይቅርም በል፤ አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ሁሉ ልብ ታውቃለህና፥ ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለውና ስጠው። “ክከሕዝብህም ከእስራኤል ወገን ያልሆነ እንግዳ ታላቁን ስምህን፥ ብርቱይቱንም እጅህን፥ የተዘረጋውንም ክንድህን ሰምቶ ስለ ስምህ ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ፥ መጥቶ ወደዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ፥ አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል ይፈሩህ ዘንድ፥ በዚህም በሠራሁት ቤት ስምህ እንደተጠራ ያውቁ ዘንድ፥ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ። “ሕዝብህም ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ቢወጡ፥ አንተም ወደ መረጥሃት ከተማ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤት ለእግዚአብሔር ቢጸልዩ፥ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ስማ፤ ፍርድንም አድርግላቸው። “የማይበድልም ሰው የለምና አንተን ቢበድሉ፥ ተቆጥተህም ለጠላቶቻቸው አሳልፈህ ብትሰጣቸው፥ ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ ወደ ጠላቶች አገር ቢማረኩም፥ በተማረኩበትም አገር ሆነው በልባቸው ንስሓ ቢገቡ፥ በማራኪዎቹም አገር ሳሉ ተመልሰው ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለንማል፤ ክፉንም አድርገናል፤’ ብለው ቢለምኑህ፥ በማረኩአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃት ወደ ምድራቸው ወደ መረጥሃትም ከተማ ለስምህም ወደ ሠራሁት ቤት ቢጸልዩ፥ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ፍርድንም አድርግላቸው፤ አንተንም የበደሉህን ሕዝብህን፥ በአንተም ላይ ያደረጉትን በደላቸውን ሁሉ ይቅር በል፤ ይራሩላቸውም ዘንድ በማረኩአቸው ፊት ምሕረት ስጣቸው፤ ከግብጽ ምድር ከብረት እቶን ውስጥ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸውና። በጠሩህ ጊዜ ሁሉ ትሰማቸው ዘንድ ለባሪያህና ለሕዝብህ ለእስራኤል ልመና ዐይኖችህ የተገለጡ ይሁኑ። ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ! አባቶቻችንን ከግብጽ ባወጣህ ጊዜ፥ በባሪያህ በሙሴ አማካይነት እንደ ተናገርህ ርስት ይሆኑህ ዘንድ ከምድር አሕዛብ ሁሉ ለይተሃቸዋልና።”