1 ነገሥት 8:22-53

1 ነገሥት 8:22-53 NASV

ከዚያም ሰሎሞን መላው የእስራኤል ጉባኤ ባለበት በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ፣ እንዲህም አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልባቸው በመንገድህ ከሚሄዱት ባሪያዎችህ ጋራ የፍቅር ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ በላይ በሰማይም ሆነ በታች በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ አጽንተሃል፤ በአፍህ የተናገርኸውን ዛሬም እንደ ሆነው በእጅህ ፈጸምኸው። “አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት፣ ‘ልጆችህ አንተ እንደ አደረግኸው ሁሉ በሚያደርጉት ሁሉ በጥንቃቄ በፊቴ ቢመላለሱ፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አታጣም’ ብለህ የሰጠኸውን ተስፋ አጽናለት። እንግዲህ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ይፈጸም። “ነገር ግን አምላክ በርግጥ በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማይ፣ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ እንኳ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ! ይሁን እንጂ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ የባሪያህን ጸሎትና ስለ ምሕረት ያቀረበውን ልመና አድምጥ፤ በዛሬው ዕለት ባሪያህ በፊትህ የሚያቀርበውን ጩኸትና ጸሎት ስማ። ባሪያህ ወደዚህ ቦታ የሚያቀርበውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ፣ ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’ ወደ አልኸው በዚህ ስፍራ ወዳለው ቤተ መቅደስ ዐይኖችህ ሌትና ቀን የተከፈቱ ይሁኑ። ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ ጸሎት በሚያቀርቡበት ጊዜ፣ ልመናቸውን ተቀበል፤ መኖሪያህ በሆነው በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል። “አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢበድልና እንዲምል ቢጠየቅ፣ እርሱም መጥቶ በቤተ መቅደሱ በመሠዊያህ ፊት ቢምል፣ ይህን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ አድርግም፤ በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ፤ ለበደለኛው ስለ አድራጎቱ የእጁን ክፈል፤ ከበደል ነጻ ለሆነውም ንጽሕናውን ይፋ በማድረግ ይህንኑ አረጋግጥለት። “ሕዝብህ እስራኤል አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ በጠላቶቻቸው ድል በሚሆኑበት ጊዜ፣ ወደ አንተም ተመልሰው ስምህን ቢጠሩ፣ በዚህም ቤተ መቅደስ ወደ አንተ ቢጸልዩና ልመናቸውን ቢያቀርቡ፣ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸውም ምድር መልሳቸው። “አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ ሰማዩ ተዘግቶ ዝናብ ሳይዘንብ ቢቀር፣ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩና ስምህን ቢጠሩ፣ ስላስጨነቅሃቸውም ከኀጢአታቸው ቢመለሱ፣ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የባሪያዎችህን የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ የሚሄዱበትን ቀናውን መንገድ አስተምራቸው፤ ርስት አድርገህ ለሕዝብህ በሰጠሃቸውም ምድርህ ላይ ዝናብን አዝንብ። “በምድሪቱ ላይ ራብ ወይም ቸነፈር፣ ዋግ ወይም አረማሞ፣ አንበጣ ወይም ኵብኵባ በሚከሠትበት ጊዜ፣ ወይም ከተሞቻቸውን ጠላት በሚከብብበት ጊዜ፣ እንዲሁም ማንኛውም ዐይነት ጥፋት ወይም በሽታ በሚደርስባቸው ጊዜ፣ ከሕዝብህ ማንኛውም ሰው ወይም መላው እስራኤል የልቡን ጭንቀት ዐውቆ እጆቹን ወደዚህ ቤት በመዘርጋት ማንኛውንም ጸሎትና ልመና በሚያቀርብበት ጊዜ ሁሉ፣ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ይቅር በል፤ አድርግም። የሰውን ልጆች ሁሉ ልብ የምታውቅ አንተ ብቻ ስለ ሆንህ ልቡን ለምታውቀው ለእያንዳንዱ ሰው እንደ አካሄዱ ክፈለው፤ ይኸውም እነርሱ ለአባቶቻችን በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ፣ አንተን እንዲፈሩህ ነው። “ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ፣ ነገር ግን ከስምህ ታላቅነት የተነሣ ከሩቅ የመጣ ባዕድ ሰው ቢኖር፣ ሰዎች ከሩቅ የመጣው ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ጠንካራዪቱ እጅህ፣ ስለ ተዘረጋችው ክንድህ ሰምቶ ነውና፤ እንግዳው መጥቶ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢጸልይ፣ አንተ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደ ገዛ ሕዝብህ እንደ እስራኤል፣ ስምህን በማወቅ እንዲፈሩህ፣ የሠራሁትም ይህ ቤት ስምህ የሚጠራበት ቤት መሆኑን እንዲያውቁ ባዕዱ ሰው የሚጠይቅህን ሁሉ አድርግ። “ሕዝብህ ጠላታቸውን ለመውጋት አንተ ወደምትልካቸው ወደ የትኛውም ቦታ ለጦርነት በሚወጡበት ጊዜ፣ አንተ ወደ መረጥሃት ከተማና እኔ ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ወደ እግዚአብሔር ቢጸልዩ፣ ጸሎትና ልመናቸውን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ፍትሕንም አጐናጽፋቸው። “መቼም ኀጢአት የማይሠራ ሰው የለምና ሕዝብህ በአንተ ላይ ኀጢአት ቢሠሩ፣ አንተም ተቈጥተህ ለጠላቶቻቸው አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣ እነርሱም ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ የጠላት ምድር ቢጋዙ፣ በተጋዙበት አገር ሳሉ ወደ ልቡናቸው ቢመለሱ፣ ንስሓ ቢገቡና በምርኮ ምድር ሳሉ፣ ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ ብለው ቢለምኑህ፣ እንዲሁም ማርከው በወሰዷቸው ጠላቶቻቸው አገር፣ በምርኮ ምድር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፣ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር፣ ወደ መረጥሃትም ከተማና እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፣ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውንና፤ ልመናቸውን ስማ፤ ፍረድላቸውም። በአንተ ላይ ስለ ሠሩት ኀጢአት፣ የበደሉህንም የሕዝብህን ኀጢአት ይቅር በል፤ የማረኳቸውም እንዲራሩላቸው አድርግ። ከዚያች እንደ ብረት ማቅለጫ እቶን እሳት ከሆነችው፣ ከግብጽ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህም ርስትህም ናቸውና። “አሁንም ዐይኖችህ ለባሪያህና ለሕዝብህ ለእስራኤል ልመና የተከፈቱ ይሁኑ፤ ወደ አንተ በሚጮኹበትም ጊዜ ሁሉ ስማቸው፤ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አባቶቻችንን ከግብጽ ባወጣህ ጊዜ፣ በባሪያህ በሙሴ አማካይነት እንደ ተናገርኸው ሁሉ፣ ርስትህ ይሆኑ ዘንድ ከምድር ሕዝቦች ሁሉ ለይተሃቸዋልና።”