“ከእርሷ ጋር ያመነዘሩና በምቾት የኖሩ የምድር ነገሥታት፣ እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም። ሥቃይዋንም በመፍራት በሩቅ ቆመው እንዲህ ይላሉ፤ “ ‘አንቺ ታላቂቱ ከተማ ወዮልሽ! ወዮልሽ! አንቺ ባቢሎን ብርቱዪቱ ከተማ፣ ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ውስጥ መጥቷል።’ “ጭነታቸውን ከእንግዲህ የሚገዛ ስለሌለ፣ የምድር ነጋዴዎችም ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉ፤ ጭነቱም፦ ወርቅ፣ ብር፣ የከበረ ድንጋይ፣ ዕንቍ፣ ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ፣ ሐምራዊ ልብስ፣ ሐር ልብስ፣ ቀይ ልብስ፣ መልካም ሽታ ያለው ዕንጨት ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስ፣ ከውድ ዕንጨት፣ ከናስ፣ ከብረትና ከእብነ በረድ የተሠራ ዕቃ ሁሉ፣ ቀረፋ፣ ቅመም፣ ከርቤ፣ ቅባት፣ ዕጣን፣ የወይን ጠጅ፣ የወይራ ዘይት፣ የተሰለቀ ዱቄት፣ ስንዴ፣ ከብቶች፣ በጎች፣ ፈረሶች፣ ሠረገሎች፣ እንዲሁም ባሮችና የሰዎች ነፍሶች ነው። “እነርሱም፣ ‘የተመኘሽው ፍሬ ከአንቺ ርቋል፤ ብልጽግናሽና ክብርሽ ሁሉ ጠፍቷል፤ ዳግመኛም ተመልሶ አይመጣም’ ይላሉ። እነዚህን ነገሮች በመሸጥ በእርሷ የበለጸጉ ነጋዴዎች ሥቃይዋን ፈርተው በሩቅ ይቆማሉ፤ እነርሱም ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም፤ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲህ ይላሉ፤ “ ‘ቀጭን የተልባ እግር፣ ሐምራዊና ቀይ ልብስ የለበሰች፣ በወርቅ፣ በከበረ ድንጋይና በዕንቍም ያጌጠች፣ ታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ያ ሁሉ ሀብት በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፋ።’ “የመርከብ አዛዦች ሁሉ፣ በመርከብ የሚጓዙ መንገደኞች ሁሉ፣ የመርከብ ሠራተኞችና ኑሯቸውን በባሕር ላይ የመሠረቱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ። እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ፣ ‘እንደዚህች ያለ ታላቅ ከተማ ከቶ የት አለ?’ እያሉ ይጮኻሉ። በራሳቸውም ላይ አቧራ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ እንዲህ ብለው ጮኹ፤ “ ‘በባሕር ላይ መርከቦች ያላቸው ሁሉ፣ በእርሷም ሀብት የበለጸጉ፣ ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፍታለች!’
ራእይ 18 ያንብቡ
ያዳምጡ ራእይ 18
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ራእይ 18:9-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos