የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 18

18
የባቢሎን ውድቀት
1ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም ነጸብራቅ የተነሣ ምድር በራች፤ 2እርሱም በብርቱ ድምፅ እንዲህ ብሎ ጮኸ፤
“ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች!
የአጋንንት መኖሪያ፣
የርኩሳን መናፍስት ሁሉ መጠጊያ፣
የርኩስና የአስጸያፊ ወፎች ሁሉ መጠለያ ሆነች።
3ሕዝቦች ሁሉ የዝሙቷን ቍጣ ወይን ጠጅ ጠጥተዋልና፤
የምድር ነገሥታት ከእርሷ ጋር አመንዝረዋል፤
የምድርም ነጋዴዎች ከብዙ ምቾቷ ኀይል
የተነሣ በልጽገዋል።”
4ከዚያም ከሰማይ ሌላ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤
“ሕዝቤ ሆይ፤ በኀጢአቷ እንዳትተባበሩ፤
ከመቅሠፍቷም እንዳትካፈሉ፤
ከእርሷ ውጡ፤
5ኀጢአቷ እስከ ሰማይ ድረስ ተከምሯልና፤
እግዚአብሔርም ዐመፃዋን አስታውሷል።
6በሰጠችው መጠን ብድራቷን መልሱላት፤
ለሠራችው ሁሉ ዕጥፍ ክፈሏት፤
በቀላቀለችውም ጽዋ ዕጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት።
7ለራሷ ክብርና ምቾት የሰጠችውን ያህል፣
ሥቃይና ሐዘን ስጧት፤
በልቧም እንዲህ እያለች ትመካለች፤
‘እንደ ንግሥት ተቀምጬአለሁ፤
መበለትም አይደለሁም፤ ከቶም
አላዝንም፤’
8ስለዚህ መቅሠፍቶቿ በአንድ ቀን ይመጡባታል፤
ሞት፣ ሐዘንና ራብ ይሆኑባታል፤
የሚፈርድባት ጌታ እግዚአብሔር ብርቱ ስለሆነ፣
በእሳት ትቃጠላለች።
9“ከእርሷ ጋር ያመነዘሩና በምቾት የኖሩ የምድር ነገሥታት፣ እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም። 10ሥቃይዋንም በመፍራት በሩቅ ቆመው እንዲህ ይላሉ፤
“ ‘አንቺ ታላቂቱ ከተማ ወዮልሽ! ወዮልሽ!
አንቺ ባቢሎን ብርቱዪቱ ከተማ፣
ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ውስጥ መጥቷል።’
11“ጭነታቸውን ከእንግዲህ የሚገዛ ስለሌለ፣ የምድር ነጋዴዎችም ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉ፤ 12ጭነቱም፦ ወርቅ፣ ብር፣ የከበረ ድንጋይ፣ ዕንቍ፣ ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ፣ ሐምራዊ ልብስ፣ ሐር ልብስ፣ ቀይ ልብስ፣ መልካም ሽታ ያለው ዕንጨት ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስ፣ ከውድ ዕንጨት፣ ከናስ፣ ከብረትና ከእብነ በረድ የተሠራ ዕቃ ሁሉ፣ 13ቀረፋ፣ ቅመም፣ ከርቤ፣ ቅባት፣ ዕጣን፣ የወይን ጠጅ፣ የወይራ ዘይት፣ የተሰለቀ ዱቄት፣ ስንዴ፣ ከብቶች፣ በጎች፣ ፈረሶች፣ ሠረገሎች፣ እንዲሁም ባሮችና#18፥13 ግሪኩ ሰውነቶችና ይላል። የሰዎች ነፍሶች ነው።
14“እነርሱም፣ ‘የተመኘሽው ፍሬ ከአንቺ ርቋል፤ ብልጽግናሽና ክብርሽ ሁሉ ጠፍቷል፤ ዳግመኛም ተመልሶ አይመጣም’ ይላሉ። 15እነዚህን ነገሮች በመሸጥ በእርሷ የበለጸጉ ነጋዴዎች ሥቃይዋን ፈርተው በሩቅ ይቆማሉ፤ እነርሱም ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም፤ 16ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲህ ይላሉ፤
“ ‘ቀጭን የተልባ እግር፣ ሐምራዊና ቀይ ልብስ የለበሰች፣
በወርቅ፣ በከበረ ድንጋይና በዕንቍም ያጌጠች፣
ታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት!
17ያ ሁሉ ሀብት በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፋ።’
“የመርከብ አዛዦች ሁሉ፣ በመርከብ የሚጓዙ መንገደኞች ሁሉ፣ የመርከብ ሠራተኞችና ኑሯቸውን በባሕር ላይ የመሠረቱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ። 18እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ፣ ‘እንደዚህች ያለ ታላቅ ከተማ ከቶ የት አለ?’ እያሉ ይጮኻሉ። 19በራሳቸውም ላይ አቧራ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ እንዲህ ብለው ጮኹ፤
“ ‘በባሕር ላይ መርከቦች ያላቸው ሁሉ፣
በእርሷም ሀብት የበለጸጉ፣
ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት!
በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፍታለች!’
20“ሰማይ ሆይ፤ በእርሷ ላይ ሐሤት አድርግ!
ቅዱሳን፣ ሐዋርያትና ነቢያትም ሐሤት አድርጉ!
በእናንተ ላይ ባደረሰችው ነገር እግዚአብሔር ፈርዶባታልና።”
21ከዚያም አንድ ብርቱ መልአክ፣ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ የሚመስል ድንጋይ አንሥቶ ወደ ባሕር ወረወረው፤ እንዲህም አለ፤
“ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን፣
እንዲህ ባለ ኀይል ትወረወራለች፤
ተመልሳም አትገኝም።
22የበገና ደርዳሪዎችና የሙዚቀኞች ድምፅ፣
የዋሽንትና የመለከት ነፊዎች ድምፅ፣
ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም፤
የእጅ ጥበብ ባለሙያ፣
ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይገኝም፤
የወፍጮ ድምፅም፣
ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም።
23የመብራት ብርሃን፣
ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይበራም፤
የሙሽራውና የሙሽራዪቱ ድምፅ፣
ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም፤
ነጋዴዎችሽ የዓለም ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፤
በአስማትሽም ሕዝቦች ሁሉ ስተዋል።
24በእርሷም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን፣
በምድርም የተገደሉት ሁሉ ደም ተገኘ።”

Currently Selected:

ራእይ 18: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ