የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 17

17
በአውሬው ላይ የተቀመጠችው ሴት
1ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ እንዲህ አለኝ፤ “ና፤ በብዙ ውሆች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን አመንዝራ ፍርድ አሳይሃለሁ። 2የምድር ነገሥታት ከእርሷ ጋር አመነዘሩ፤ የምድር ነዋሪዎችም በዝሙቷ የወይን ጠጅ ሰከሩ።”
3ቀጥሎም መልአኩ በመንፈስ ወደ በረሓ ወሰደኝ፤ በዚያም አንዲት ሴት በስድብ ስሞች በተሞላ፣ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ባሉት ቀይ አውሬ ላይ ተቀምጣ አየሁ። 4ሴቲቱም ሐምራዊና ቀይ ልብስ ተጐናጽፋ ነበር፤ ደግሞም በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቈችም አጊጣ ነበር፤ በእጇም የሚያስጸይፍ ነገርና የዝሙቷ ርኩሰት የሞላበትን የወርቅ ጽዋ ይዛ ነበር። 5በግንባሯም ላይ እንዲህ የሚል የምስጢር ስም ተጽፎ ነበር፤
ታላቂቱ ባቢሎን፣
የአመንዝሮችና
የምድር ርኩሰቶች እናት።
6ሴቲቱንም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት።
ባየኋትም ጊዜ እጅግ ተደነቅሁ። 7ከዚያም መልአኩ እንዲህ አለኝ፤ የምትደነቀው ለምንድን ነው? የሴቲቱን፣ እርሷ የተቀመጠችበትንም፣ እንዲሁም ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እነግርሃለሁ። 8ያየኸው አውሬ ቀደም ሲል ነበረ፤ አሁን ግን የለም፤ በኋላም ከጥልቁ ጕድጓድ ይወጣል፤ ወደ ጥፋቱም ይሄዳል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘ የምድር ነዋሪዎች አውሬው ቀድሞ የነበረ፣ አሁን ግን የሌለ፣ በኋላም የሚመጣ መሆኑን ሲያዩ ይደነቃሉ።
9“ይህም፣ ጥበብ ያለው አእምሮ ይጠይቃል። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የምትቀመጥባቸው ሰባት ተራሮች ናቸው፤ 10እነርሱም ደግሞ ሰባት ነገሥታት ናቸው። አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ አለ፤ ሌላውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣ ግን ሊቈይ የሚገባው ለጥቂት ጊዜ ነው። 11ቀድሞ የነበረውና አሁን የሌለው አውሬ ስምንተኛው ንጉሥ ነው፤ እርሱም ከሰባቱ አንዱ ሲሆን ወደ ጥፋቱ ይሄዳል።
12“ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ፣ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ነገር ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንዲነግሡ ሥልጣን ይቀበላሉ። 13አንድ ሐሳብም አላቸው፤ ኀይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ፤ 14እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉ ግን ድል ይነሣቸዋል፤ ምክንያቱም እርሱ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ነው፤ ከእርሱ ጋር ያሉ የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑትም አብረው ድል ይነሣሉ።”
15መልአኩም እንዲህ አለኝ፤ “አመንዝራዪቱ ተቀምጣባቸው ያየሃቸው ውሆች፣ ወገኖች፣ ብዙ ሰዎች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች ናቸው። 16አውሬውና ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች አመንዝራዪቱን ይጠሏታል፤ ባዶዋንና ዕራቍቷን ያስቀሯታል። ሥጋዋን ይበላሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል። 17የእግዚአብሔር ቃል እስኪፈጸም ድረስ ዕቅዱን እንዲፈጽሙ፣ ደግሞም በአንድ ሐሳብ እንዲስማሙና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው እንዲሰጡ ይህን ሐሳብ በልባቸው ያኖረ እግዚአብሔር ነውና። 18ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።”

Currently Selected:

ራእይ 17: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ