የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 18:9-19

ራእይ 18:9-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“ከእርሷ ጋር ያመነዘሩና በምቾት የኖሩ የምድር ነገሥታት፣ እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም። ሥቃይዋንም በመፍራት በሩቅ ቆመው እንዲህ ይላሉ፤ “ ‘አንቺ ታላቂቱ ከተማ ወዮልሽ! ወዮልሽ! አንቺ ባቢሎን ብርቱዪቱ ከተማ፣ ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ውስጥ መጥቷል።’ “ጭነታቸውን ከእንግዲህ የሚገዛ ስለሌለ፣ የምድር ነጋዴዎችም ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉ፤ ጭነቱም፦ ወርቅ፣ ብር፣ የከበረ ድንጋይ፣ ዕንቍ፣ ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ፣ ሐምራዊ ልብስ፣ ሐር ልብስ፣ ቀይ ልብስ፣ መልካም ሽታ ያለው ዕንጨት ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስ፣ ከውድ ዕንጨት፣ ከናስ፣ ከብረትና ከእብነ በረድ የተሠራ ዕቃ ሁሉ፣ ቀረፋ፣ ቅመም፣ ከርቤ፣ ቅባት፣ ዕጣን፣ የወይን ጠጅ፣ የወይራ ዘይት፣ የተሰለቀ ዱቄት፣ ስንዴ፣ ከብቶች፣ በጎች፣ ፈረሶች፣ ሠረገሎች፣ እንዲሁም ባሮችና የሰዎች ነፍሶች ነው። “እነርሱም፣ ‘የተመኘሽው ፍሬ ከአንቺ ርቋል፤ ብልጽግናሽና ክብርሽ ሁሉ ጠፍቷል፤ ዳግመኛም ተመልሶ አይመጣም’ ይላሉ። እነዚህን ነገሮች በመሸጥ በእርሷ የበለጸጉ ነጋዴዎች ሥቃይዋን ፈርተው በሩቅ ይቆማሉ፤ እነርሱም ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም፤ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲህ ይላሉ፤ “ ‘ቀጭን የተልባ እግር፣ ሐምራዊና ቀይ ልብስ የለበሰች፣ በወርቅ፣ በከበረ ድንጋይና በዕንቍም ያጌጠች፣ ታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ያ ሁሉ ሀብት በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፋ።’ “የመርከብ አዛዦች ሁሉ፣ በመርከብ የሚጓዙ መንገደኞች ሁሉ፣ የመርከብ ሠራተኞችና ኑሯቸውን በባሕር ላይ የመሠረቱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ። እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ፣ ‘እንደዚህች ያለ ታላቅ ከተማ ከቶ የት አለ?’ እያሉ ይጮኻሉ። በራሳቸውም ላይ አቧራ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ እንዲህ ብለው ጮኹ፤ “ ‘በባሕር ላይ መርከቦች ያላቸው ሁሉ፣ በእርሷም ሀብት የበለጸጉ፣ ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፍታለች!’

ራእይ 18:9-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከእርስዋ ጋር ያመነዘሩና በምቾት የኖሩ የምድር ነገሥታት እርስዋ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ ሥቃይዋንም በመፍራት በሩቅ ቆመው “አንቺ ታላቂቱ ከተማ፥ አንቺ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን ሆይ! ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ውስጥ ስለ መጣ፥ ወዮልሽ! ወዮልሽ!” ይላሉ። የመርከባቸውን ጭነት ከእንግዲህ የሚገዛ ስለሌለ የምድር ነጋዴዎችም ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላታልም፤ በመርከባቸው የተጫነውም ወርቅ፥ ብር፥ የከበረ ድንጋይ፥ ዕንቊ፥ ቀጭን ልብስ፥ ሐምራዊ ልብስ፥ ሐር ልብስ፥ ቀይ ልብስና መልካም መዓዛ ያለው እንጨት ሁሉ፥ ከዝኆን ጥርስ፥ ውድ ከሆነ እንጨት፥ ከነሐስ፥ ከብረትና ከእብነበረድ የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋ፥ ቅመም፥ የሚሸት እንጨት፥ ከርቤ፥ ዕጣን፥ ወይን ጠጅ፥ የወይራ ዘይት፥ ዱቄት፥ ስንዴ፥ ከብቶች፥ በጎች፥ ፈረሶች፥ ሠረገላዎች፥ ባርያዎችና ሌሎችም ሰዎች ናቸው። ነጋዴዎቹም “አንቺ የተመኘሻቸው መልካም ነገሮች ሁሉ ከአንቺ ርቀው ሄደዋል፤ ሀብትሽም ጌጣ ጌጥሽም ሁሉ ጠፍቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ እነዚህን ሁሉ ከቶ አታገኚአቸውም!” ይሉአታል። እነዚህን ነገሮች ሁሉ እየገዙ ሀብታሞች የሆኑ ነጋዴዎች ሥቃይዋን በመፍራት በሩቅ ይቆማሉ፤ እያለቀሱና እያዘኑም፥ “ቀጭን ልብስና ሐምራዊ ልብስ ቀይ ልብስም ትለብስ የነበረች፥ በወርቅና በከበረ ድንጋይ በዕንቊም ታሸበርቅ የነበረች፤ ታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ያን ያኽል ሀብት በአንድ ሰዓት ጠፋ!” ይላሉ። የመርከብ አዛዦች ሁሉ፥ በመርከብ የሚጓዙ ሰዎች ሁሉ፥ በመርከብ ላይ የሚሠሩ ሁሉ፥ በባሕር ላይ የሚነግዱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ፤ እርስዋ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ባዩ ጊዜ “ይህችን ታላቅ ከተማ የሚመስል ከቶ ሌላ ከተማ ነበረን?” እያሉ ጮኹ። በራሳቸው ላይ አቧራ ነሰነሱ፤ እያለቀሱና እያዘኑም እንዲህ እያሉ ይጮኻሉ፤ “በባሕር ላይ መርከቦች ያላቸው ሁሉ በእርስዋ ሀብት ሀብታሞች የሆኑ፥ ያቺ ታላቅ ከተማ በአንድ ሰዓት ውስጥ ስለ ወደመች ወዮላት! ወዮላት!”

ራእይ 18:9-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከእርስዋም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ እየጮሁ እያሉ ያለቅሳሉ፤ ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው “አንቺ ታላቂቱ ከተማ! ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን! ወዮልሽ! ወዮልሽ! በአንድ ሰዓት ፍርድሽ ደርሶአልና፤” እያሉ ይናገራሉ። የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላትማል፤ ጭነትም ወርቅና ብር፥ የከበረም ድንጋይ ዕንቁም፥ ቀጭንም ተልባ እግር፥ ቀይም ሐር፥ ሐምራዊም ልብስ፥ የሚሸትም እንጨት ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ እጅግም ከከበረ እንጨት፥ ከናስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋም፥ ቅመምም፥ የሚቃጠልም ሽቱ፥ ቅባትም፥ ዕጣንም፥ የወይን ጠጅም፥ ዘይትም፥ የተሰለቀ ዱቄትም፥ ስንዴም፥ ከብትም፥ በግም፥ ፈረስም፥ ሰረገላም፥ ባሪያዎችም፥ የሰዎችም ነፍሳት ነው። “ነፍስሽም የጎመጀችው ፍሬ ከአንቺ ዘንድ አልፎአል፤ የሚቀማጠልና የሚያጌጥም ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፤ ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አያገኙአቸውም።” እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለ ጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ “በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና፤” እያሉ ስቃይዋን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ይቆማሉ። የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፤ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ “ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች?” እያሉ ጮኹ። በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ “በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከባለ ጠግነትዋ የተነሣ ባለ ጠጋዎች ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና፤” እያሉ ጮኹ።

ራእይ 18:9-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከእርስዋም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ፤ ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው፦ አንቺ ታላቂቱ ከተማ፥ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን፥ ወዮልሽ፥ ወዮልሽ፥ በአንድ ሰዓት ፍርድሽ ደርሶአልና እያሉ ይናገራሉ። የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል ያዝኑላትማል፤ ጭነትም ወርቅና ብር የከበረም ድንጋይ ዕንቁም፥ ቀጭንም ተልባ እግር ቀይም ሐርም ሐምራዊም ልብስ የሚሸትም እንጨት ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፥ እጅግም ከከበረ እንጨት ከናስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋም ቅመምም የሚቃጠልም ሽቱ ቅባትም ዕጣንም የወይን ጠጅም ዘይትም የተሰለቀ ዱቄትም ስንዴም ከብትም በግም ፈረስም ሰረገላም ባሪያዎችም የሰዎችም ነፍሳት ነው። ነፍስሽም የጎመጀችው ፍሬ ከአንቺ ዘንድ አልፎአል፥ የሚቀማጠልና የሚያጌጥም ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፥ ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አያገኙአቸውም። እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለ ጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ፦ በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና እያሉ ስቃይዋን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ይቆማሉ። የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፥ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ፦ ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች? እያሉ ጮኹ። በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ፦ በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከባለ ጠግነትዋ የተነሣ ባለ ጠጋዎች ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና እያሉ ጮኹ።

ራእይ 18:9-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከእርሷም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርሷ እየጮሁ ያለቅሳሉ፤ ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው “አንቺ ታላቂቱ ከተማ! ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን! ወዮልሽ! ወዮልሽ! በአንድ ሰዓት ውስጥ ፍርድሽ ይፈጸማልና፤” እያሉ ይናገራሉ። የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላትማል፤ ጭነቱም ወርቅና ብር፥ የከበረም ድንጋይ ዕንቁም፥ ቀጭንም ተልባ እግር፥ ቀይም ሐር፥ ሐምራዊም ልብስ፥ መልካም መዐዛ ያለውም እንጨት ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ እጅግም ከከበረ እንጨት፥ ከነሐስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋም፥ ቅመምም፥ የሚቃጠልም ሽቱ፥ ቅባትም፥ ዕጣንም፥ የወይን ጠጅም፥ የወይራ ዘይትም፥ ምርጥ ዱቄትም፥ ስንዴም፥ ከብትም፥ በግም፥ ፈረስም፥ ሠረገላም፥ ባርያዎችም፥ የሰዎችም ነፍሳት ነው። “ነፍስሽም የጎመጀችለት ፍሬ ከአንቺ ተለይቶ ሄዶአል፤ የድሎትና የጌጥ ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፤ ከእንግዲህ ወዲህም ከቶ አይገኙም።” እነዚህን የነገዱ በእርሷም ሀብታም የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ “በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ይላሉ። ይህን የሚያህል ታላቅ ሀብት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና፤” የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፤ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ “ታላቂቱን ከተማ የምትመስል ሌላ ከተማ ነበረችን?” እያሉ ጮኹ። በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ “በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከሀብቷ የተነሣ ሀብታም ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና፤” እያሉ ጮኹ።