የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 18:9-19

የዮሐንስ ራእይ 18:9-19 አማ54

ከእርስዋም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ፤ ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው፦ አንቺ ታላቂቱ ከተማ፥ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን፥ ወዮልሽ፥ ወዮልሽ፥ በአንድ ሰዓት ፍርድሽ ደርሶአልና እያሉ ይናገራሉ። የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል ያዝኑላትማል፤ ጭነትም ወርቅና ብር የከበረም ድንጋይ ዕንቁም፥ ቀጭንም ተልባ እግር ቀይም ሐርም ሐምራዊም ልብስ የሚሸትም እንጨት ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፥ እጅግም ከከበረ እንጨት ከናስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋም ቅመምም የሚቃጠልም ሽቱ ቅባትም ዕጣንም የወይን ጠጅም ዘይትም የተሰለቀ ዱቄትም ስንዴም ከብትም በግም ፈረስም ሰረገላም ባሪያዎችም የሰዎችም ነፍሳት ነው። ነፍስሽም የጎመጀችው ፍሬ ከአንቺ ዘንድ አልፎአል፥ የሚቀማጠልና የሚያጌጥም ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፥ ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አያገኙአቸውም። እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለ ጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ፦ በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና እያሉ ስቃይዋን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ይቆማሉ። የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፥ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ፦ ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች? እያሉ ጮኹ። በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ፦ በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከባለ ጠግነትዋ የተነሣ ባለ ጠጋዎች ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና እያሉ ጮኹ።