የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 18:9-19

የዮሐንስ ራእይ 18:9-19 አማ05

ከእርስዋ ጋር ያመነዘሩና በምቾት የኖሩ የምድር ነገሥታት እርስዋ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ ሥቃይዋንም በመፍራት በሩቅ ቆመው “አንቺ ታላቂቱ ከተማ፥ አንቺ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን ሆይ! ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ውስጥ ስለ መጣ፥ ወዮልሽ! ወዮልሽ!” ይላሉ። የመርከባቸውን ጭነት ከእንግዲህ የሚገዛ ስለሌለ የምድር ነጋዴዎችም ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላታልም፤ በመርከባቸው የተጫነውም ወርቅ፥ ብር፥ የከበረ ድንጋይ፥ ዕንቊ፥ ቀጭን ልብስ፥ ሐምራዊ ልብስ፥ ሐር ልብስ፥ ቀይ ልብስና መልካም መዓዛ ያለው እንጨት ሁሉ፥ ከዝኆን ጥርስ፥ ውድ ከሆነ እንጨት፥ ከነሐስ፥ ከብረትና ከእብነበረድ የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋ፥ ቅመም፥ የሚሸት እንጨት፥ ከርቤ፥ ዕጣን፥ ወይን ጠጅ፥ የወይራ ዘይት፥ ዱቄት፥ ስንዴ፥ ከብቶች፥ በጎች፥ ፈረሶች፥ ሠረገላዎች፥ ባርያዎችና ሌሎችም ሰዎች ናቸው። ነጋዴዎቹም “አንቺ የተመኘሻቸው መልካም ነገሮች ሁሉ ከአንቺ ርቀው ሄደዋል፤ ሀብትሽም ጌጣ ጌጥሽም ሁሉ ጠፍቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ እነዚህን ሁሉ ከቶ አታገኚአቸውም!” ይሉአታል። እነዚህን ነገሮች ሁሉ እየገዙ ሀብታሞች የሆኑ ነጋዴዎች ሥቃይዋን በመፍራት በሩቅ ይቆማሉ፤ እያለቀሱና እያዘኑም፥ “ቀጭን ልብስና ሐምራዊ ልብስ ቀይ ልብስም ትለብስ የነበረች፥ በወርቅና በከበረ ድንጋይ በዕንቊም ታሸበርቅ የነበረች፤ ታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ያን ያኽል ሀብት በአንድ ሰዓት ጠፋ!” ይላሉ። የመርከብ አዛዦች ሁሉ፥ በመርከብ የሚጓዙ ሰዎች ሁሉ፥ በመርከብ ላይ የሚሠሩ ሁሉ፥ በባሕር ላይ የሚነግዱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ፤ እርስዋ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ባዩ ጊዜ “ይህችን ታላቅ ከተማ የሚመስል ከቶ ሌላ ከተማ ነበረን?” እያሉ ጮኹ። በራሳቸው ላይ አቧራ ነሰነሱ፤ እያለቀሱና እያዘኑም እንዲህ እያሉ ይጮኻሉ፤ “በባሕር ላይ መርከቦች ያላቸው ሁሉ በእርስዋ ሀብት ሀብታሞች የሆኑ፥ ያቺ ታላቅ ከተማ በአንድ ሰዓት ውስጥ ስለ ወደመች ወዮላት! ወዮላት!”