ሰባተኛው ወር በደረሰ ጊዜ፣ እስራኤላውያን በየከተሞቻቸው ሳሉ፣ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ከዚያም የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱና ካህናት ዘመዶቹ እንዲሁም የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የሥራ ባልደረቦቹ፣ በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ በተጻፈው መሠረት የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ፣ የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ መሥራት ጀመሩ። በዙሪያቸው ካሉት አሕዛብ የተነሣ ፍርሀት ቢያድርባቸውም፣ መሠዊያውን በቀድሞው መሠረት ላይ ሠሩ፤ በመሠዊያውም ላይ ጧትና ማታ የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡ። ከዚያም ለእያንዳንዱ ቀን እንደ ታዘዘው፣ በሚያስፈልገው ቍጥር ልክ የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ የዳስ በዓልን በተጻፈው መሠረት አከበሩ። ከዚያም በኋላ መደበኛውን የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የወር መባቻን መሥዋዕት፣ በተቀደሱት የእግዚአብሔር በዓላት የሚቀርበውን መሥዋዕትና የበጎ ፈቃድ ስጦታ ለእግዚአብሔር አቀረቡ። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት ገና ያልተጣለ ቢሆንም፣ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ። ከዚያም ለድንጋይ ጠራቢዎችና ለየእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ገንዘብ ሰጡ፤ ከፋርስ ንጉሥ ከቂሮስ በተፈቀደው መሠረት የዝግባ ዛፎች ከሊባኖስ ወደ ኢዮጴ በባሕር እንዲያመጡላቸው፣ ለሲዶናና ለጢሮስ ሰዎችም ምግብ፣ መጠጥና ዘይት ሰጡ። ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ እግዚአብሔር ቤት በደረሱ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር፣ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ እንዲሁም የቀሩት ወንድሞቻቸው (ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ ከምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ሁሉ) ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆናቸው ሌዋውያን የእግዚአብሔርን ቤት ሕንጻ ሥራ እንዲቈጣጠሩ ሾሟቸው፤ ሥራውንም ጀመሩ። ኢያሱ፣ ወንዶች ልጆቹና ወንድሞቹ፣ የዮሖዳያ ዘሮች ቀድምኤልና ወንዶች ልጆቹ፣ የኤንሐዳድ ወንዶች ልጆች፣ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው፣ ሌዋውያኑም ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን ሰዎች ለመቈጣጠር በአንድ ላይ ሆኑ። ግንበኞቹ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሠረት በጣሉ ጊዜ፣ ካህናቱ ልብሰ ተክህኗቸውን ለብሰውና መለከታቸውን ይዘው፣ ሌዋውያኑ የአሳፍ ልጆች ደግሞ ጸናጽል ይዘው፣ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት መመሪያ መሠረት እግዚአብሔርን ለመወደስ ስፍራቸውን ያዙ።
ዕዝራ 3 ያንብቡ
ያዳምጡ ዕዝራ 3
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዕዝራ 3:1-10
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች