መጽሐፈ ዕዝራ 3:1-10

መጽሐፈ ዕዝራ 3:1-10 አማ05

በሰባተኛው ወር እስራኤላውያን በሙሉ በከተሞቻቸው በመስፈር በአንድነት በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ የኢዮጼዴቅ ልጅ ኢያሱም ከወገኖቹ ካህናትና የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልም ከዘመዶቹ ጋር በመተባበር የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን መሠዊያ እንደገና ሠሩ፤ የእግዚአብሔር ሰው ለሆነው ለሙሴ በተሰጠው የሕግ መጽሐፍ በተጻፈውም መመሪያ መሠረት በዚያ መሠዊያ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ ቻሉ። የተመለሱት ምርኮኞች በምድሪቱ ከሚኖሩት አሕዛብ ተቃውሞ የተነሣ ፍርሀት ቢያድርባቸውም እንኳ መሠዊያውን በዚያው ቀድሞ በቆመበት ቦታ መልሰው ሠሩት፤ ከዚያም በኋላ የሚቃጠል መሥዋዕት ዘወትር ጠዋትና ማታ በዚያ ላይ እንደገና ማቅረብ ጀመሩ። ሕጉም በሚያዘው መሠረት የዳስ በዓልን አከበሩ፤ ለእያንዳንዱም ቀን የተመደበውን መሥዋዕት አቀረቡ፤ በተጨማሪም ዘወትር በሙሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ በወር መባቻ በዓልና በሌሎችም የተቀደሱ የእግዚአብሔር በዓላት የሚቀርብ መሥዋዕትን በበጎ ፈቃድ ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ ጋር አቀረቡ። እነርሱ የቤተ መቅደሱን ሕንጻ እንደገና መሥራት ባይጀምሩም እንኳ ሰባተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረባቸውን ጀመሩ። እንዲሁም ሕዝቡ ለግንበኞችና ለአናጢዎች የሚከፈለውን ገንዘብ ሰጡ፤ ከሊባኖስ ዛፍ ቈርጠው በኢዮጴ የባሕር ጠረፍ በኩል እንዲልኩላቸው ለጢሮስና ለሲዶና ከተሞች ነዋሪዎች ምግብን፥ መጠጥንና የወይራ ዘይትን ላኩ፤ ይህም ሁሉ የሆነው የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ቂሮስ በሰጣቸው ፈቃድ መሠረት ነበር። ስለዚህም በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተሠርቶ ወደነበረበት ስፍራ በደረሱበት በሁለተኛው ዓመት፥ በሁለተኛው ወር፥ ዘሩባቤል፥ ኢያሱና ሌሎቹም የሀገራቸው ልጆች፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ ባጠቃላይም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው የመጡት ምርኮኞች ሥራውን ጀመሩ። ዕድሜአቸው ኻያ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ሌዋውያን ሁሉ የቤተ መቅደሱ ሕንጻ ሥራ ኀላፊዎች ሆነው ተመደቡ። ሌዋዊው ኢያሱና ወንዶች ልጆቹ፥ እንዲሁም ዘመዶቹ፥ ቃድሚኤልና ከሖዳዊያ ቤተሰብ ወገን የሆኑ ወንዶች ልጆቹም ሁሉ በአንድነት ተባብረው ቤተ መቅደሱን እንደገና የመሥራቱን ኀላፊነት ተረከቡ፤ የሔናዳድ ዘሮች የሆኑት ሌዋውያንም ይረዱአቸው ነበር። ሠራተኞቹ የቤተ መቅደሱን መሠረት ማኖር በጀመሩበት ጊዜ ካህናቱ ልብሰ ተክህኖአቸውን ለብሰው በእጃቸው እምቢልታ በመያዝ የአሳፍ ቤተሰብ ተወላጆች የሆኑ ሌዋውያንም ጸናጽል ይዘው በረድፍ ቆመው ነበር፤ እነርሱም ከንጉሥ ዳዊት ዘመን ጀምሮ ተያይዞ በመጣው መመሪያ መሠረት በመዝሙር እግዚአብሔርን አመሰገኑ።