ዕዝራ 3:1-10

ዕዝራ 3:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሰባ​ተ​ኛ​ውም ወር በደ​ረሰ ጊዜ፥ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች በከ​ተ​ሞ​ቻ​ቸው ሳሉ፥ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም ተሰ​በ​ሰቡ። የኢ​ዮ​ሴ​ዴ​ቅም ልጅ ኢያሱ፥ ወን​ድ​ሞ​ቹም ካህ​ናቱ፥ የሰ​ላ​ት​ያ​ልም ልጅ ዘሩ​ባ​ቤል፥ ወን​ድ​ሞ​ቹም ተነ​ሥ​ተው በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ የሚ​ቃ​ጠ​ለ​ውን መሥ​ዋ​ዕት ያቀ​ር​ቡ​በት ዘንድ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን አም​ላክ መሠ​ዊያ ሠሩ። በሀ​ገ​ሩም ካሉት አሕ​ዛብ ፈር​ተው ነበ​ርና መሠ​ዊ​ያ​ውን በስ​ፍ​ራው ላይ አስ​ቀ​መ​ጡት፤ በጥ​ዋ​ትና በማ​ታም የሚ​ቃ​ጠ​ለ​ውን መሥ​ዋ​ዕት ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አቀ​ረ​ቡ​በት። እንደ ተጻ​ፈ​ውም የዳስ በዓል አደ​ረጉ፤ እንደ ሥር​ዐ​ቱም ለየ​ዕ​ለቱ የተ​ገ​ባ​ውን የየ​ዕ​ለ​ቱን የሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕት በቍ​ጥር አቀ​ረቡ። ከዚ​ያም በኋላ ዘወ​ትር የሚ​ቃ​ጠ​ለ​ውን መሥ​ዋ​ዕት፥ የመ​ባ​ቻ​ው​ንም መሥ​ዋ​ዕት፥ የተ​ቀ​ደ​ሱ​ት​ንም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በዓ​ላት ሁሉ መሥ​ዋ​ዕት፥ ሰውም ሁሉ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በፈ​ቃድ የሰ​ጠ​ውን ቍር​ባን አቀ​ረቡ። በሰ​ባ​ተ​ኛ​ውም ወር በመ​ጀ​መ​ሪ​ያው ቀን ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕት ማቅ​ረብ ጀመሩ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መቅ​ደስ ግን ገና አል​ተ​መ​ሠ​ረ​ተም ነበር። ለጠ​ራ​ቢ​ዎ​ችና ለአ​ና​ጢ​ዎ​ችም ብር ሰጡ፤ የፋ​ር​ስም ንጉሥ ቂሮስ እንደ ፈቀ​ደ​ላ​ቸው የዝ​ግባ ዛፍ ከሊ​ባ​ኖስ በባ​ሕር ወደ ኢዮጴ ያመጡ ዘንድ ለሲ​ዶ​ናና ለጢ​ሮስ ሰዎች መብ​ልና መጠጥ፥ ዘይ​ትም ሰጡ። በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ወዳ​ለው ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤት በመጡ በሁ​ለ​ተ​ኛው ዓመት በሁ​ለ​ተ​ኛ​ውም ወር የሰ​ላ​ት​ያል ልጅ ዘሩ​ባ​ቤል፥ የኢ​ዮ​ሴ​ዴ​ቅም ልጅ ኢያሱ፥ የቀ​ሩ​ትም ወን​ድ​ሞ​ቻ​ቸው ካህ​ና​ትና ሌዋ​ው​ያን፥ ከም​ርኮ ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም የተ​መ​ለ​ሱት ሁሉ ጀመሩ፤ ሌዋ​ው​ያ​ን​ንም ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚ​ያም በላይ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቤት ሥራ እን​ዲ​ያ​ሠ​ሩት ሾሙ​አ​ቸው። ኢያ​ሱም፥ ልጆ​ቹም ተሾሙ፤ ወን​ድ​ሞ​ቹም፥ የይ​ሁ​ዳም ልጆች ቀደ​ም​ያ​ልና ልጆቹ፥ የኢ​ን​ሐ​ዳ​ድም ልጆች፥ ልጆ​ቻ​ቸ​ውና ወን​ድ​ሞ​ቻ​ቸው ሌዋ​ው​ያ​ንም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቤት የሚ​ሠ​ሩ​ትን ያሠሩ ዘንድ በአ​ን​ድ​ነት ቆሙ። አና​ጢ​ዎ​ቹም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መቅ​ደስ ይሠሩ ዘንድ መሠ​ረት በጣሉ ጊዜ ካህ​ናቱ ልብ​ሳ​ቸ​ውን ለብ​ሰው መለ​ከ​ቱን ይዘው፥ የአ​ሳ​ፍም ልጆች ሌዋ​ው​ያን ጸና​ጽል ይዘው እንደ እስ​ራ​ኤል ንጉሥ እንደ ዳዊት ሥር​ዐት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ያመ​ሰ​ግኑ ዘንድ ቆሙ።

ዕዝራ 3:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሰባተኛው ወር በደረሰ ጊዜ፣ እስራኤላውያን በየከተሞቻቸው ሳሉ፣ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ከዚያም የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱና ካህናት ዘመዶቹ እንዲሁም የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የሥራ ባልደረቦቹ፣ በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ በተጻፈው መሠረት የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ፣ የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ መሥራት ጀመሩ። በዙሪያቸው ካሉት አሕዛብ የተነሣ ፍርሀት ቢያድርባቸውም፣ መሠዊያውን በቀድሞው መሠረት ላይ ሠሩ፤ በመሠዊያውም ላይ ጧትና ማታ የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡ። ከዚያም ለእያንዳንዱ ቀን እንደ ታዘዘው፣ በሚያስፈልገው ቍጥር ልክ የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ የዳስ በዓልን በተጻፈው መሠረት አከበሩ። ከዚያም በኋላ መደበኛውን የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የወር መባቻን መሥዋዕት፣ በተቀደሱት የእግዚአብሔር በዓላት የሚቀርበውን መሥዋዕትና የበጎ ፈቃድ ስጦታ ለእግዚአብሔር አቀረቡ። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት ገና ያልተጣለ ቢሆንም፣ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ። ከዚያም ለድንጋይ ጠራቢዎችና ለየእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ገንዘብ ሰጡ፤ ከፋርስ ንጉሥ ከቂሮስ በተፈቀደው መሠረት የዝግባ ዛፎች ከሊባኖስ ወደ ኢዮጴ በባሕር እንዲያመጡላቸው፣ ለሲዶናና ለጢሮስ ሰዎችም ምግብ፣ መጠጥና ዘይት ሰጡ። ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ እግዚአብሔር ቤት በደረሱ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር፣ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ እንዲሁም የቀሩት ወንድሞቻቸው (ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ ከምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ሁሉ) ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆናቸው ሌዋውያን የእግዚአብሔርን ቤት ሕንጻ ሥራ እንዲቈጣጠሩ ሾሟቸው፤ ሥራውንም ጀመሩ። ኢያሱ፣ ወንዶች ልጆቹና ወንድሞቹ፣ የዮሖዳያ ዘሮች ቀድምኤልና ወንዶች ልጆቹ፣ የኤንሐዳድ ወንዶች ልጆች፣ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው፣ ሌዋውያኑም ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን ሰዎች ለመቈጣጠር በአንድ ላይ ሆኑ። ግንበኞቹ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሠረት በጣሉ ጊዜ፣ ካህናቱ ልብሰ ተክህኗቸውን ለብሰውና መለከታቸውን ይዘው፣ ሌዋውያኑ የአሳፍ ልጆች ደግሞ ጸናጽል ይዘው፣ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት መመሪያ መሠረት እግዚአብሔርን ለመወደስ ስፍራቸውን ያዙ።

ዕዝራ 3:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሰባተኛውም ወር በደረሰ ጊዜ፥ የእስራኤል ልጆች በከተሞቻቸው ሳሉ፥ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፥ ወንድሞቹም ካህናቱ፥ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል፥ ወንድሞቹም ተነሥተው በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡበት ዘንድ የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ ሠሩ። በአገሩም ካሉት አሕዛብ ፈርተው ነበርና መሠዊያውን በስፍራው ላይ አስቀመጡት፥ በጥዋትና በማታም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡበት። እንደተጻፈውም የዳስ በዓል አደረጉ፤ እንደ ሥርዓቱም ለየዕለቱ የተገባውን የየዕለቱን የሚቃጠል መሥዋዕት በቍጥር አቀረቡ። ከዚያም በኋላ ዘወትር የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የመባቻውንም መሥዋዕት፥ የተቀደሱትንም የእግዚአብሔር በዓላት ሁሉ መሥዋዕት፥ ሰውም ሁሉ ለእግዚአብሔር በፈቃድ የሰጠውን ቍርባን አቀረቡ። በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ጀመሩ፤ የእግዚአብሔር መቅደስ ገና አልተመሠረተም ነበር። ለጠራቢዎችና ለአናጢዎች ገንዘብ ሰጡ፤ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንደ ፈቀደላቸው የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ በባሕር ወደ ኢዮጴ ያመጡ ዘንድ ለሲዶናና ለጢሮስ ሰዎች መብልና መጠጥ፥ ዘይትም ሰጡ። በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በመጡ በሁለተኛው ዓመት፥ በሁለተኛውም ወር የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል፥ የኢዮሴዴቅም ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ወንድሞቻቸው ካህናትና ሌዋውያን፥ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ምርኮኞች ሁሉ ጀመሩ፤ ሌዋውያንንም ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ እንዲያሠሩት ሾሙአቸው። ኢያሱ፥ ልጆቹና ወንድሞቹ፥ የይሁዳም ልጆች ቀድምኤልና ልጆቹ፥ የኤንሐዳድም ልጆች፥ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው፥ ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን ያሠሩ ዘንድ በአንድነት ቆሙ። አናጢዎቹም የእግዚአብሔርን መቅደስ በመሠረቱ ጊዜ ካህናቱ ልብሳቸውን ለብሰው፥ መለከቱን ይዘው፥ የአሳፍም ልጆች ሌዋውያን ጸናጽል ይዘው እንደ እስራኤል ንጉሥ እንደ ዳዊት ሥርዓት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ቆሙ።

ዕዝራ 3:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በሰባተኛው ወር እስራኤላውያን በሙሉ በከተሞቻቸው በመስፈር በአንድነት በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ የኢዮጼዴቅ ልጅ ኢያሱም ከወገኖቹ ካህናትና የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልም ከዘመዶቹ ጋር በመተባበር የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን መሠዊያ እንደገና ሠሩ፤ የእግዚአብሔር ሰው ለሆነው ለሙሴ በተሰጠው የሕግ መጽሐፍ በተጻፈውም መመሪያ መሠረት በዚያ መሠዊያ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ ቻሉ። የተመለሱት ምርኮኞች በምድሪቱ ከሚኖሩት አሕዛብ ተቃውሞ የተነሣ ፍርሀት ቢያድርባቸውም እንኳ መሠዊያውን በዚያው ቀድሞ በቆመበት ቦታ መልሰው ሠሩት፤ ከዚያም በኋላ የሚቃጠል መሥዋዕት ዘወትር ጠዋትና ማታ በዚያ ላይ እንደገና ማቅረብ ጀመሩ። ሕጉም በሚያዘው መሠረት የዳስ በዓልን አከበሩ፤ ለእያንዳንዱም ቀን የተመደበውን መሥዋዕት አቀረቡ፤ በተጨማሪም ዘወትር በሙሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ በወር መባቻ በዓልና በሌሎችም የተቀደሱ የእግዚአብሔር በዓላት የሚቀርብ መሥዋዕትን በበጎ ፈቃድ ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ ጋር አቀረቡ። እነርሱ የቤተ መቅደሱን ሕንጻ እንደገና መሥራት ባይጀምሩም እንኳ ሰባተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረባቸውን ጀመሩ። እንዲሁም ሕዝቡ ለግንበኞችና ለአናጢዎች የሚከፈለውን ገንዘብ ሰጡ፤ ከሊባኖስ ዛፍ ቈርጠው በኢዮጴ የባሕር ጠረፍ በኩል እንዲልኩላቸው ለጢሮስና ለሲዶና ከተሞች ነዋሪዎች ምግብን፥ መጠጥንና የወይራ ዘይትን ላኩ፤ ይህም ሁሉ የሆነው የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ቂሮስ በሰጣቸው ፈቃድ መሠረት ነበር። ስለዚህም በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተሠርቶ ወደነበረበት ስፍራ በደረሱበት በሁለተኛው ዓመት፥ በሁለተኛው ወር፥ ዘሩባቤል፥ ኢያሱና ሌሎቹም የሀገራቸው ልጆች፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ ባጠቃላይም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው የመጡት ምርኮኞች ሥራውን ጀመሩ። ዕድሜአቸው ኻያ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ሌዋውያን ሁሉ የቤተ መቅደሱ ሕንጻ ሥራ ኀላፊዎች ሆነው ተመደቡ። ሌዋዊው ኢያሱና ወንዶች ልጆቹ፥ እንዲሁም ዘመዶቹ፥ ቃድሚኤልና ከሖዳዊያ ቤተሰብ ወገን የሆኑ ወንዶች ልጆቹም ሁሉ በአንድነት ተባብረው ቤተ መቅደሱን እንደገና የመሥራቱን ኀላፊነት ተረከቡ፤ የሔናዳድ ዘሮች የሆኑት ሌዋውያንም ይረዱአቸው ነበር። ሠራተኞቹ የቤተ መቅደሱን መሠረት ማኖር በጀመሩበት ጊዜ ካህናቱ ልብሰ ተክህኖአቸውን ለብሰው በእጃቸው እምቢልታ በመያዝ የአሳፍ ቤተሰብ ተወላጆች የሆኑ ሌዋውያንም ጸናጽል ይዘው በረድፍ ቆመው ነበር፤ እነርሱም ከንጉሥ ዳዊት ዘመን ጀምሮ ተያይዞ በመጣው መመሪያ መሠረት በመዝሙር እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

ዕዝራ 3:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሰባተኛውም ወር በደረሰ ጊዜ፥ የእስራኤልም ልጆች በከተሞች ነበሩ፥ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። የዮፃዳቅም ልጅ ኢያሱ ተነሣ፥ ወንድሞቹ ካህናትና፥ የሸአልቲኤል ልጅ ዘሩባቤልና ወንድሞቹም በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሊያቀርቡበት የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ ሠሩ። በምድሩ ካሉት ሕዝቦች የተነሣ ፈርተው ነበርና፥ መሠዊያውን በስፍራው ላይ አስቀመጡት በጠዋትና በማታ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለጌታ አቀረቡ። እንደተጻፈውም የዳስ በዓል አከበሩ፤ እንደ ሥርዓቱም የዕለቱን የሚቃጠል መሥዋዕት በዕለቱ በቍጥር አቀረቡ፤ የዕለቱን ነገር በዕለቱ። ከዚያም በኋላ ዘወትር የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የወር መባቻና፥ የተመረጡና የተቀደሱ የጌታ በዓላት ሁሉ መሥዋዕት፥ ሰውም ሁሉ ለጌታ በፈቃድ የሰጠውን ቁርባን አቀረቡ። ከሰባተኛው ወር ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ጀመሩ፤ ነገር ግን የጌታ መቅደስ አልተመሠረተም ነበር። ለጠራቢዎችና ለአናጢዎችም ገንዘብ ሰጡ፤ የፋርስም ንጉሥ ቂሮስ እንደ ፈቀደላቸው የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ ወደ ያፎ ባሕር እንዲያመጡ ለሲዶናውያንና ለጢሮሳውያን መብልና መጠጥ ዘይትም ሰጡ። በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በመጡ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛውም ወር የሸአልቲኤል ልጅ ዘሩባቤል፥ የዮፃዳቅም ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ወንድሞቻቸው ካህናትና ሌዋውያን፥ ወደ ኢየሩሳሌምም የተመለሱት ምርኮኞች ሁሉ፥ ሌዋውያንንም ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የጌታን ቤት ሥራ እንዲቆጣጠሩ መረጧቸው። ኢያሱ፥ ልጆቹ፥ ወንድሞቹ፥ የይሁዳም ልጆች ቃድሚኤልና ልጆቹ፥ የሔናዳድም ልጆች፥ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን እንዲቆጣጠሩ እንደ አንድ ቆሙ። ግንበኞቹም የጌታን መቅደስ መሠረቱ፤ ካህናቱ ሙሉ ልብስ ለብሰው፥ መለከት ይዘው፥ የአሳፍ ልጆች ሌዋውያን ጸናጽል ይዘው በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት መመሪያ መሠረት ጌታን እንዲያመሰግኑ መረጧቸው።