የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ዕዝራ 3

3
በኢየሩሳሌም ማምለክ እንደገና መጀመሩ
1ሰባተኛውም ወር በደረሰ ጊዜ፥ የእስራኤልም ልጆች በከተሞች ነበሩ፥ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 2#ዘፀ. 27፥1።የዮፃዳቅም ልጅ ኢያሱ ተነሣ፥ ወንድሞቹ ካህናትና፥ የሸአልቲኤል ልጅ ዘሩባቤልና ወንድሞቹም በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሊያቀርቡበት የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ ሠሩ። 3#ዘኍ. 28፥1-8።በምድሩ ካሉት ሕዝቦች የተነሣ ፈርተው ነበርና፥ መሠዊያውን በስፍራው ላይ አስቀመጡት በጠዋትና በማታ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለጌታ አቀረቡ። 4#ዘኍ. 29፥12-38።እንደተጻፈውም የዳስ በዓል አከበሩ፤ እንደ ሥርዓቱም የዕለቱን የሚቃጠል መሥዋዕት በዕለቱ በቍጥር አቀረቡ፤ የዕለቱን ነገር በዕለቱ። 5#ዘኍ. 28፥11—29፥39።ከዚያም በኋላ ዘወትር የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የወር መባቻና፥ የተመረጡና የተቀደሱ የጌታ በዓላት ሁሉ መሥዋዕት፥ ሰውም ሁሉ ለጌታ በፈቃድ የሰጠውን ቁርባን አቀረቡ። 6ከሰባተኛው ወር ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ጀመሩ፤ ነገር ግን የጌታ መቅደስ አልተመሠረተም ነበር። 7ለጠራቢዎችና ለአናጢዎችም ገንዘብ ሰጡ፤ የፋርስም ንጉሥ ቂሮስ እንደ ፈቀደላቸው የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ ወደ ያፎ ባሕር እንዲያመጡ ለሲዶናውያንና ለጢሮሳውያን መብልና መጠጥ ዘይትም ሰጡ።
የቤተ መቅደሱ መሰረት መጣል
8በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በመጡ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛውም ወር የሸአልቲኤል ልጅ ዘሩባቤል፥ የዮፃዳቅም ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ወንድሞቻቸው ካህናትና ሌዋውያን፥ ወደ ኢየሩሳሌምም የተመለሱት ምርኮኞች ሁሉ፥ ሌዋውያንንም ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የጌታን ቤት ሥራ እንዲቆጣጠሩ መረጧቸው። 9ኢያሱ፥ ልጆቹ፥ ወንድሞቹ፥ የይሁዳም ልጆች ቃድሚኤልና ልጆቹ፥ የሔናዳድም ልጆች፥ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን እንዲቆጣጠሩ እንደ አንድ ቆሙ። 10#1ዜ.መ. 25፥1።ግንበኞቹም የጌታን መቅደስ መሠረቱ፤ ካህናቱ ሙሉ ልብስ ለብሰው፥ መለከት ይዘው፥ የአሳፍ ልጆች ሌዋውያን ጸናጽል ይዘው በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት መመሪያ መሠረት ጌታን እንዲያመሰግኑ መረጧቸው። 11#1ዜ.መ. 16፥34፤ 2ዜ.መ. 5፥13፤ 7፥3፤ መዝ. 99፥5፤ 105፥1፤ 106፥1፤ 117፥1፤ 135፥1፤ ኤር. 40፥11።ደግሞም ጌታን እያከበሩና እያመሰገኑ “ቸር ነውና፥ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና” እያሉ ዘመሩ። ሕዝቡ ሁሉ ጌታን እያመሰገኑ በታላቅ ድምፅ እልል አሉ፥ ይህም የጌታ ቤት ስለ ተመሠረተ ነው። 12#ጦቢ. 14፥5።የመጀመሪያውን ቤት ያዩ ብዙ ካህናት፥ ሌዋውያን፥ የአባቶች አለቆችና ሽማግሌዎች ግን ይህ ቤት በፊታቸው በተመሠረተ ጊዜ በታላቅ ድምፅ ያለቅሱ ነበር፥ ብዙ ሰዎችም በደስታ እልል ይሉ ነበር፤ 13ሕዝቡ ግን ደስ ብሎአቸው የሚጮኹትን ድምፅ ከሕዝቡ ልቅሶ ድምፅ መለየት አልቻለም፤ ሕዝቡም በታላቅ ድምፅ እልል ይሉ ነበር፥ ድምፁም ከሩቅ ይሰማ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ