ዕዝራ 3
3
መሠዊያው እንደ ገና ተሠራ
1ሰባተኛው ወር በደረሰ ጊዜ፣ እስራኤላውያን በየከተሞቻቸው ሳሉ፣ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 2ከዚያም የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱና ካህናት ዘመዶቹ እንዲሁም የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የሥራ ባልደረቦቹ፣ በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ በተጻፈው መሠረት የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ፣ የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ መሥራት ጀመሩ። 3በዙሪያቸው ካሉት አሕዛብ የተነሣ ፍርሀት ቢያድርባቸውም፣ መሠዊያውን በቀድሞው መሠረት ላይ ሠሩ፤ በመሠዊያውም ላይ ጧትና ማታ የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡ። 4ከዚያም ለእያንዳንዱ ቀን እንደ ታዘዘው፣ በሚያስፈልገው ቍጥር ልክ የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ የዳስ በዓልን በተጻፈው መሠረት አከበሩ። 5ከዚያም በኋላ መደበኛውን የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የወር መባቻን መሥዋዕት፣ በተቀደሱት የእግዚአብሔር በዓላት የሚቀርበውን መሥዋዕትና በበጎ ፈቃድ ለእግዚአብሔር የሚሰጠውን መባ አቀረቡ። 6የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት ገና ያልተጣለ ቢሆንም፣ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ።
ቤተ መቅደሱ እንደ ገና ተሠራ
7ከዚያም ለድንጋይ ጠራቢዎችና ለዐናጢዎች ገንዘብ ሰጡ፤ ከፋርስ ንጉሥ ከጢሮስ በተፈቀደው መሠረት የዝግባ ዛፎች ከሊባኖስ ወደ ኢዮጴ በባሕር እንዲያመጡላቸው፣ ለሲዶናና ለጢሮስ ሰዎችም ምግብ፣ መጠጥና ዘይት ሰጡ።
8ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ እግዚአብሔር ቤት በደረሱ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር፣ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ እንዲሁም የቀሩት ወንድሞቻቸው (ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ ከምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ሁሉ) ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆናቸው ሌዋውያን የእግዚአብሔርን ቤት ሕንጻ ሥራ እንዲቈጣጠሩ ሾሟቸው፤ ሥራውንም ጀመሩ። 9ኢያሱ፣ ወንዶች ልጆቹና ወንድሞቹ፣ የዮሖዳያ#3፥9 ዕብራይስጡ፣ ይሁዳ ይላል፤ ምናልባት ከዮሖዳያ ጋር ተመሳሳይ ነው። ዘሮች ቀድምኤልና ወንዶች ልጆቹ፣ የኤንሐዳድ ወንዶች ልጆች፣ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው፣ ሌዋውያኑም ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን ሰዎች ለመቈጣጠር በአንድ ላይ ሆኑ።
10ግንበኞቹ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሠረት በጣሉ ጊዜ፣ ካህናቱ ልብሰ ተክህኗቸውን ለብሰውና መለከታቸውን ይዘው፣ ሌዋውያኑ የአሳፍ ልጆች ደግሞ ጸናጽል ይዘው፣ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት መመሪያ መሠረት እግዚአብሔርን ለመወደስ ስፍራቸውን ያዙ። 11በውዳሴና በምስጋናም ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲሉ ዘመሩ፤
“ቸር ነውና፤ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።” የእግዚአብሔር ቤት መሠረት ስለ ተጣለ፣ ሕዝቡ ሁሉ በታላቅ ድምፅ እልል እያሉ፣ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ። 12የቀድሞውን ቤተ መቅደስ ያዩ በዕድሜ የሸመገሉ ብዙ ካህናት፣ ሌዋውያንና የቤተ ሰብ አለቆች የዚህ ቤተ መቅደስ መሠረት ሲጣል ባዩ ጊዜ፣ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ሌሎቹ ግን የደስታ ጩኸት አሰሙ። 13የሕዝቡ ጩኸት ድብልቅልቅ ያለ ስለ ነበር፣ የደስታውን እልልታ ከልቅሶው ጩኸት መለየት የሚችል ማንም አልነበረም፤ ድምፁም ከሩቅ ይሰማ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.