የዮሐንስ ወንጌል 19

19
የወታደሮች በኢየሱስ ላይ ማፌዝ
(ማቴ. 27፥27-32ማር. 15፥15-21)
1ከዚህ በኋላ ጲላጦስ ኢየሱስን ወስዶ አስገረፈው። 2ወታደሮችም የእሾኽ አክሊል ጐንጒነው በኢየሱስ ራስ ላይ አደረጉ፤ ቀይ ልብስም አለበሱት። 3ወደ እርሱም እየመጡ በማፌዝ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ላንተ ይሁን!” ይሉት ነበር፤ በጥፊም ይመቱት ነበር።
4ጲላጦስ እንደገና ወደ ውጪ ወጥቶ “እነሆ ምንም በደል እንዳላገኘሁበት እንድታውቁ እርሱን ወደ ውጪ አወጣላችኋለሁ” አላቸው፤ 5ስለዚህ ኢየሱስ የእሾኽ አክሊል ደፍቶና ቀይ ልብስ ለብሶ ወደ ውጪ ወጣ፤ ጲላጦስም “እነሆ፥ ሰውየው!” አላቸው።
6የካህናት አለቆችና የዘብ ኀላፊዎች ኢየሱስን ባዩት ጊዜ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ።
ጲላጦስ ግን “እኔ በበኩሌ ምንም በደል አላገኘሁበትም፤ ብትፈልጉ እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት” አላቸው።
7አይሁድም “እኛ ሕግ አለን፤ ይህ ሰው ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ስላደረገ በሕጋችን መሠረት መሞት ይገባዋል” አሉ። 8ይህን ሁሉ ነገር በሰማ ጊዜ ጲላጦስ በይበልጥ ፈራ፤ 9ወደ ግቢው ገባና ኢየሱስን “አንተ ከየት ነህ?” ሲል ጠየቀው።
ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም። 10ስለዚህ ጲላጦስ “አትነግረኝምን? እኔ ልፈታህ ወይም ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን?” አለው፤
11ኢየሱስም “ከእግዚአብሔር ሥልጣን ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልኖረህ ነበር፤ ሆኖም ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ የባሰ ኃጢአት አለበት” አለው።
በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ መፈረዱ
(ማቴ. 27፥15-31ማር. 15፥6-20ሉቃ. 23፥13-25)
12ጲላጦስ ይህን የኢየሱስን አነጋገር በሰማ ጊዜ ፈቶ ሊለቀው ፈልጎ ነበር፤ አይሁድ ግን “ይህን ሰው ከፈታኸው አንተ የሮም ንጉሠ ነገሥት ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የንጉሠ ነገሥቱ ጠላት ነው!” እያሉ ጮኹ።
13ጲላጦስ ይህን በሰማ ጊዜ ኢየሱስን ወደ ውጪ አውጥቶ “ጠፍጣፋ ድንጋይ” በተባለው ስፍራ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ፤ ይህ ስፍራ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ገበታ” ይባላል። 14የፋሲካ በዓል የዝግጅት ቀን ነበረ፤ ጊዜውም ወደ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበረ፤ በዚያን ጊዜ ጲላጦስ አይሁድን “እነሆ ንጉሣችሁ!” አላቸው። 15እነርሱ ግን “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አላቸው።
የካህናት አለቆችም “ከሮማው ንጉሠ ነገሥት በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም!” ሲሉ መለሱለት።
16በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲሰቀል ጲላጦስ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት።
የኢየሱስ መሰቀል
(ማቴ. 27፥32-44ማር. 15፥21-32ሉቃ. 23፥26-43)
17ከዚህ በኋላ ኢየሱስ መስቀሉን ተሸክሞ፥ “የራስ ቅል” ወደሚባለው ስፍራ ወጣ፤ ይህ ስፍራ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ጎልጎታ” ይባላል፤ 18እዚያ ሰቀሉት፤ ኢየሱስን በመካከል አድርገው፥ ከእርሱ ጋር ሌሎችንም ሁለት ሰዎች በግራና በቀኝ ሰቀሉ። 19ጲላጦስ “የናዝሬቱ ኢየሱስ፥ የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ጽሑፍ ጽፎ በመስቀሉ ራስጌ ላይ አኖረው። 20ኢየሱስ የተሰቀለበት ስፍራ ለከተማ ቅርብ ስለ ነበር፥ ከአይሁድ ብዙዎቹ ጽሑፉን አነበቡት፤ ጽሑፉም የተጻፈው በዕብራይስጥ፥ በላቲንና በግሪክ ቋንቋ ነበር። 21የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን፥ “አንተ ‘የአይሁድ ንጉሥ’ ብለህ አትጻፍ፤ ነገር ግን ‘ይህ ሰው እኔ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ ብሎአል ብለህ ጻፍ” አሉት።
22ጲላጦስ ግን “የጻፍኩትን ጽፌአለሁ” ሲል መለሰ።
23ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉት በኋላ፥ ልብሶቹን ወስደው፥ ለእያንዳንዱ ወታደር አንድ ክፍል እንዲደርስ በአራት ከፋፈሉአቸው፤ እጀ ጠባቡንም እንዲሁ አደረጉ፤ ነገር ግን እጀ ጠባቡ ሳይሰፋ፥ ከላይ እስከ ታች ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበር፤ 24ስለዚህ ወታደሮቹ “ለማን እንደሚደርስ ለማወቅ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ፥ አንቅደደው” ተባባሉ። ይህም የሆነው፥
“ልብሴን ተከፋፈሉ፤
በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉ”
የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው፤ ወታደሮቹም እንዲሁ አደረጉ። #መዝ. 22፥18።
25በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱና የእናቱ እኅት፥ የቀልዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር፤ 26ኢየሱስ እናቱንና የሚወደውን ደቀ መዝሙር አጠገቡ ቆመው ባያቸው ጊዜ፥ እናቱን “እናቴ ሆይ! እነሆ፥ ልጅሽ!” አላት።
27ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን “እነኋት እናትህ!” አለው፤ ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።
የኢየሱስ ሞት
(ማቴ. 27፥45-56ማር. 15፥33-41ሉቃ. 23፥44-49)
28ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አሁን ሁሉም ነገር እንደ ተፈጸመ ዐውቆ በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈውም ቃል እንዲፈጸም “ተጠማሁ!” አለ። #መዝ. 69፥21፤ 22፥15።
29እዚያ ሆምጣጤ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ ስለዚህ እዚያ የነበሩ ሰዎች፥ ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞሉና በሂሶጵ እንጨት አንጠልጥለው ወደ አፉ አቀረቡለት፤ #19፥29 ሰፍነግ፦ እንደ ኳስ ክብ ሆኖ በባሕር ውስጥ የሚበቅል ብቋያ፥ ሁለንተናው ዐይን፥ ውሃ መጣጭ የባሕር እንጒዳይ፥ ዐይነ በጎ መሳይ። #19፥29 ሂሶጵ፦ ቊጥቋጦ መሳይ ተክል። 30ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከቀመሰ በኋላ “ተፈጸመ!” አለ።
ራሱን ዘንበል አድርጎም ነፍሱን ሰጠ።
የኢየሱስ ጐኑን በጦር መወጋት
31ከዚህ በኋላ የአይሁድ ባለሥልጣኖች፥ የተሰቀሉትን ሰዎች ጭን ሰብረው፥ አስከሬናቸውን ከመስቀል እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት፤ ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት የሰንበት ዝግጅት ቀን ስለ ነበረና ያ ሰንበትም ትልቅ በዓል ስለ ሆነ፥ በሰንበት ቀን ሥጋቸው በመስቀል ላይ እንዳይሆን ነበር። 32ስለዚህ ወታደሮቹ ሄደው፥ ከኢየሱስ ጋር የተሰቀሉትን ሰዎች ጭን ሰበሩ፤ 33ወደ ኢየሱስ በሄዱ ጊዜ ግን፥ እርሱ ቀደም ብሎ እንደ ሞተ አይተው፥ ጭኑን አልሰበሩም። 34ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ፥ ጐኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውኑ ከጐኑ ደምና ውሃ ወጣ። 35ይህን ያየ፥ እናንተ እንድታምኑ መሰከረ፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ የሚናገረውም እውነት እንደ ሆነ፥ እርሱ ያውቃል። 36ይህም የሆነው፥ “ከእርሱ አንድ አጥንት እንኳ አይሰበርም” የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው። #ዘኍ. 9፥12፤ መዝ. 34፥20፤ ዘካ. 12፥10፤ ራዕ. 1፥7። 37ደግሞም በሌላው የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል “ያንን የወጉትን ያዩታል” ይላል።
የኢየሱስ መቀበር
(ማቴ. 27፥57-61ማር. 15፥42-47ሉቃ. 23፥50-56)
38የአይሁድ ባለሥልጣኖችን በመፍራት በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን አስከሬን ለመውሰድ ጲላጦስን ለመነ። ጲላጦስም ፈቀደለት። ስለዚህ ዮሴፍ ሄዶ አስከሬኑን ወሰደ። 39ከዚህ በፊት በሌሊት ወደ ኢየሱስ ሄዶ የነበረው ኒቆዲሞስም አንድ መቶ ነጥርየሚያኽል የከርቤና የሬት ቅልቅል ይዞ መጣ። #19፥39 ነጥር፦ ወደ 450 ግራም የሚሆን ክብደት አለው። #ዮሐ. 3፥1-2። 40ሁለቱ ሰዎች የኢየሱስን አስከሬን ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቶ ጋር በቀጭን ልብስ ከፈኑት። 41ኢየሱስ ተሰቅሎ በነበረበት ቦታ አንድ የአትክልት ስፍራ ነበረ፤ በዚያም የአትክልት ስፍራ ውስጥ ማንም ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር። 42የሰንበት ዝግጅት ቀን ስለ ነበረና መቃብሩም ቅርብ ስለ ነበረ የኢየሱስን አስከሬን እዚያ ቀበሩት።

Kleurmerk

Deel

Kopieer

None

Wil jy jou kleurmerke oor al jou toestelle gestoor hê? Teken in of teken aan