የዮሐንስ ወንጌል 18

18
የኢየሱስ ተላልፎ መሰጠትና መያዝ
(ማቴ. 26፥47-56ማር. 14፥43-50ሉቃ. 22፥47-53)
1ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቄድሮን ሸለቆ ማዶ ሄደ፤ እዚያ ወደነበረውም የአትክልት ቦታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ገባ። 2ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እዚያ ቦታ ዘወትር ይሰበሰቡ ስለ ነበር አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ያን ቦታ ያውቅ ነበር። 3ስለዚህ ይሁዳ አንድ የወታደሮች ጭፍራ፥ እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩትን የዘብ ኀላፊዎችን አስከትሎ ወደዚያ ቦታ መጣ፤ እነርሱም ፋኖስና ችቦ፥ የጦር መሣሪያም ይዘው ነበር። 4ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወደ እነርሱ ወጣ ብሎ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 5እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ እንፈልጋለን” አሉት። እርሱም “እኔ ነኝ!” አላቸው። አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። 6ኢየሱስ “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈገፈጉና በምድር ላይ ወደቁ። 7ኢየሱስም “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ሲል እንደገና ጠየቃቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ እንፈልጋለን” አሉ። 8እርሱም “እኔ ነኝ ብዬአችኋለሁ፤ እንግዲህ የምትፈልጉት እኔን ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አለ። 9ይህም የሆነው፥ “አባት ሆይ፥ ከሰጠኸኝ ሰዎች አንዱን እንኳ አላጠፋሁም” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው።
10ስምዖን ጴጥሮስ ሰይፍ ይዞ ስለ ነበረ መዘዘና የካህናት አለቃውን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የአገልጋዩም ስም “ማልኮስ” ይባል ነበር። 11ኢየሱስ ግን ጴጥሮስን፥ “ሰይፍህን ወደ አፎቱ ክተተው፤ አብ የሰጠኝን የመከራ ጽዋ የማልጠጣው ይመስልሃልን?” አለው። #ማቴ. 26፥39፤ ማር. 14፥36፤ ሉቃ. 22፥42።
የኢየሱስ ወደ ሊቀ ካህናቱ መወሰድ
12ከዚህ በኋላ ወታደሮቹና አዛዣቸው፥ የአይሁድ የዘብ ኀላፊዎችም ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። 13በመጀመሪያ ወደ ሐና ወሰዱት፤ ሐና በዚያ ዓመት የካህናት አለቃ ለነበረው ለቀያፋ ዐማቱ ነበር። 14ቀያፋ “አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት የተሻለ ነው” ሲል የአይሁድ ባለሥልጣኖችን የመከረ ነው። #ዮሐ. 11፥49-50።
የጴጥሮስ ኢየሱስን መካድ
(ማቴ. 26፥69-70ማር. 14፥66-68ሉቃ. 22፥55-57)
15ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉት፤ ያ ሌላው ደቀ መዝሙር በካህናት አለቃው ዘንድ የታወቀ ነበር፤ ስለዚህ ከኢየሱስ ጋር ወደ ካህናት አለቃው ግቢ ገባ፤ 16ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ በካህናት አለቃው የታወቀው ደቀ መዝሙር መጣና ለበረኛይቱ ልጃገረድ ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው፤ 17በረኛይቱም ልጃገረድ ጴጥሮስን “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው።
እርሱ ግን “አይደለሁም” አለ።
18ጊዜው ብርድ ስለ ነበረ አገልጋዮቹና የዘብ ኀላፊዎች የከሰል እሳት አንድደው ቆመው ይሞቁ ነበር፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር።
ከካህናት አለቃው ለኢየሱስ የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 26፥59-66ማር. 14፥55-64ሉቃ. 22፥66-71)
19በዚያን ጊዜ የካህናት አለቃው ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። 20ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ለሰው ሁሉ በግልጥ ተናገርኩ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኲራብም ሆነ በቤተ መቅደስ፥ ዘወትር አስተማርኩ፤ በስውር የተናገርኩት ምንም ነገር የለም፤ 21ታዲያ፥ ስለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? ስናገራቸው የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ የተናገርኩትን እነርሱ ያውቃሉ።”
22ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ እዚያ ቆመው ከነበሩት የዘብ ኀላፊዎች አንዱ፥ “ለካህናት አለቃው የምትመልሰው እንዲህ ነውን?” ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው።
23ኢየሱስም “ክፉ ቃል ተናግሬ እንደ ሆነ ክፉ መናገሬን መስክር፤ የተናገርኩት ትክክል ከሆነ ግን ስለምን ትመታኛለህ?” አለው።
24ከዚህ በኋላ ሐና፥ ኢየሱስን እንደ ታሰረ ወደ ካህናት አለቃው ወደ ቀያፋ ሰደደው።
ጴጥሮስ እንደገና ኢየሱስን መካዱ
(ማቴ. 26፥71-75ማር. 14፥69-72ሉቃ. 22፥58-62)
25የዚያን ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር፤ ሌሎች ሰዎችም “አንተስ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አሉት። እርሱም “አይደለሁም” ብሎ ካደ።
26ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመዱ የሆነው ከካህናት አለቃው ሎሌዎች አንዱ “በአትክልቱ ቦታ ከእነርሱ ጋር አይቼህ አልነበረምን?” አለው።
27ጴጥሮስም እንደገና ካደ፤ ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ።
የኢየሱስ ወደ ጲላጦስ መወሰድ
(ማቴ. 27፥1-211-14ማር. 15፥1-5ሉቃ. 23፥1-5)
28ከዚህ በኋላ ኢየሱስን ከቀያፋ ቤት ወደ አገረ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ ጊዜውም ጠዋት ማለዳ ነበር፤ አይሁድ ለፋሲካ በዓል የሚታረደውን በግ መብላት ስለ ነበረባቸው እንዳይረክሱ በማለት ወደ አገረ ገዢው ግቢ ውስጥ አልገቡም። 29ስለዚህ ጲላጦስ ወደ እነርሱ ወጣና “በዚህ ሰው ላይ ያቀረባችሁት ክስ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው።
30እነርሱም “ይህ ሰው ክፉ አድራጊ ባይሆን ኖሮ ለአንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር” ሲሉ መለሱለት።
31ጲላጦስም “እናንተ ራሳችሁ ወስዳችሁ በሕጋችሁ መሠረት ፍረዱበት” አላቸው።
አይሁድም “እኛ ሰውን ለመግደል አልተፈቀደልንም” አሉት። 32ይህም የሆነው ኢየሱስ በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው። #ዮሐ. 3፥14፤ 12፥32።
33ጲላጦስ እንደገና ወደ ግቢው ተመልሶ ገባ፤ ኢየሱስንም ጠርቶ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው።
34ኢየሱስ “አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን? ወይስ ሌሎች ይህን ስለ እኔ ነግረውሃል?” አለው። 35ጲላጦስም “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? አንተን ለእኔ አሳልፈው የሰጡህ ወገኖችህና የካህናት አለቆች ናቸው፤ ምንድን ነው ያደረግኸው?” አለው። 36ኢየሱስ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴ ከዚህ ዓለም ብትሆን ኖሮ በአይሁድ ባለሥልጣኖች እጅ እንዳልወድቅ ሎሌዎቼ በተዋጉልኝ ነበር፤ መንግሥቴ ግን ከዚህ ዓለም አይደለችም” ሲል መለሰ። 37ጲላጦስም “ታዲያ፥ አንተ ንጉሥ ነኻ?” አለው። ኢየሱስም “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንኩ አንተ ትላለህ፤ እኔ የተወለድኩትና ወደ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ልመሰክር ነው፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ቃሌን ይሰማል” ሲል መለሰ።
38ጲላጦስም “እውነት ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ። ከዚህ በኋላ ጲላጦስ እንደገና ወደ አይሁድ ወጣና እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም፤ 39ነገር ግን እንደ ልማዳችሁ በፋሲካ በዓል ሁልጊዜ አንድ እስረኛ እፈታላችኋለሁ፤ ስለዚህ የአይሁድን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?”
40እነርሱ ግን “በርባንን ፍታልን እንጂ ይህን አይደለም!” እያሉ ጮኹ። በርባን ግን ወንበዴ ነበር።

Kleurmerk

Deel

Kopieer

None

Wil jy jou kleurmerke oor al jou toestelle gestoor hê? Teken in of teken aan