ኦሪት ዘፍጥረት 15

15
እግዚአብሔር ከአብራም ጋር የገባው ቃል ኪዳን
1ከዚህ በኋላ አብራም ራእይ አየ፤ እግዚአብሔርም
“አብራም፥ አትፍራ፤ እንደ ጋሻ ሆኜ ከአደጋ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤
ታላቅ በረከትም እሰጥሃለሁ” ሲል ሰማው።
2አብራምም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ጌታ አምላክ ሆይ፥ ምንም ልጅ ስለሌለኝ የምትሰጠኝ በረከት ምን ያደርግልኛል? ሀብቴን የሚወርሰው የደማስቆ ሰው የሆነው ኤሊዔዘር ነው። 3ምንም ዘር ስላልሰጠኸኝ ሀብቴን የሚወርሰው በቤቴ የተወለደ አገልጋይ ነው።”
4ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል “ይህ ኤሊዔዘር የተባለው አገልጋይ የአንተን ሀብት አይወርስም፤ ከአንተ የሚወለደው ልጅ ወራሽህ ይሆናል” ብሎ ሲነግረው ሰማ። 5ቀጥሎም እግዚአብሔር አብራምን ወደ ውጪ አወጣውና “ወደ ሰማይ ተመልከት፤ ከዋክብትን መቊጠር ትችል እንደሆን ሞክር፤ እንግዲህ የአንተም ዘሮች እንደዚህ ይበዛሉ” አለው። #ሮም 4፥18፤ ዕብ. 11፥12።
6አብራም በእግዚአብሔር አመነ፤ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት። #ሮም 4፥3፤ ገላ. 3፥6፤ ያዕ. 2፥23።
7ደግሞም እግዚአብሔር አብራምን “ይህችን አገር በውርስ ለአንተ እንድሰጥህ ዑር ከምትባለው ከከለዳውያን ምድር ያወጣሁህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ” አለው።
8አብራም ግን “ጌታ አምላክ ሆይ፥ ይህች ምድር የእኔ እንደምትሆን እንዴት ለማወቅ እችላለሁ?” ሲል ጠየቀ።
9እግዚአብሔርም “ሦስት፥ ሦስት ዓመት የሆናቸው አንድ ጊደር፥ አንድ ፍየልና፥ አንድ በግ፥ እንዲሁም ዋኖስና ርግብ አምጣልኝ” አለው። 10አብራምም እነዚህን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር አምጥቶ እያንዳንዱን እየቈረጠ በሁለት ከፈለው፤ የተከፈሉትንም ትይዩ አድርጎ በሁለት መስመር አስቀመጣቸው። ወፎቹን ግን ቈርጦ አልከፈላቸውም። 11አሞራዎች የተቈራረጠውን ሥጋ ለመብላት ሲመጡ አብራም አባረራቸው።
12የፀሐይ መጥለቂያ ሰዓት እየተቃረበ ሲሄድ አብራምን ከባድ እንቅልፍ ያዘው፤ እነሆ፥ ድንጋጤና ታላቅ ጨለማ መጣበት። #ኢዮብ 4፥13-14። 13እግዚአብሔር አብራምን እንዲህ አለው፦ “የልጅ ልጆችህ በባዕድ አገር ስደተኞች እንደሚሆኑ ዕወቅ፤ እዚያም በባርነትና በጭቈና ለአራት መቶ ዓመት ያስጨንቁአቸዋል፤ #ዘፀ. 1፥1-14፤ ሐ.ሥ. 7፥6። 14በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እቀጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ ብዙ ሀብት ይዘው ከዚያ አገር ይወጣሉ። #ዘፀ. 12፥40-41፤ ሐ.ሥ. 7፥7። 15አንተ ግን ብዙ ዘመን ኖረህ በሰላም ትሞታለህ፤ በሰላምም ትቀበራለህ። 16የልጅ ልጆችህ ወደዚህ ተመልሰው የሚመጡት በአራተኛው ትውልድ ነው፤ እስከዚያ የሚቈዩበትም ምክንያት የአሞራውያን ኃጢአት ገና ስላልተፈጸመ ነው።”
17ፀሐይ ጠልቃ በጨለመ ጊዜ የምድጃ እሳት ጢስና ነበልባል ታየ፤ በተቈራረጠውም ሥጋ መካከል አለፈ። 18በዚያን ዕለት እግዚአብሔር ለአብራም እንዲህ በማለት ቃል ኪዳን ገባለት፦ “ከግብጽ ወንዝ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለውን ምድር ሁሉ ለዘሮችህ እሰጣለሁ፤ #ሐ.ሥ. 7፥5። 19እንዲሁም የቄናውያንን፥ የቀኒዛውያንን፥ የቃድሞናውያንን፥ 20የሒታውያንን፥ የፈሪዛውያንን፥ የረፋያውያንን፥ 21የአሞራውያንን፥ የከነዓናውያንን፥ የጌርጌሳውያንን፥ የኢያቡሳውያንን ምድር እሰጣለሁ።”

Qaqambisa

Share

Copy

None

Ufuna ukuba iimbalasane zakho zigcinwe kuzo zonke izixhobo zakho? Bhalisela okanye ngena