ኦሪት ዘፍጥረት 12
12
የአብራም መጠራት
1እግዚአብሔር አብራምን እንዲህ አለው፤ “አገርህን ትተህ፥ ከዘመዶችህና ከአባትህ ቤተሰብ ተለይተህ፥ እኔ ወደማሳይህ አገር ሂድ፤ #ሐ.ሥ. 7፥2-3፤ ዕብ. 11፥8።
2ዘርህን አበዛዋለሁ፤ ታላቅ ሕዝብም ይሆናል፤ እባርክሃለሁ፤
ስምህንም ገናና አደርገዋለሁ፤ ለሌሎችም በረከት ትሆናለህ።
3የሚመርቁህን እመርቃለሁ፤
የሚረግሙህንም እረግማቸዋለሁ፤
በአንተም አማካይነት ሕዝቦች ሁሉ ይባረካሉ።” #ገላ. 3፥8።
4አብራም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ከካራን ወጥቶ ሄደ፤ በዚያን ጊዜ ዕድሜው ሰባ አምስት ዓመት ነበር፤ ሎጥም አብሮት ሄደ። 5አብራም፥ ሚስቱ ሣራይና የወንድሙ ልጅ ሎጥ፥ በካራን ሳሉ ያገኙትን ሀብትና አገልጋዮቻቸውን ሁሉ ይዘው ወደ ከነዓን ምድር ሄዱ።
ከነዓን በደረሱ ጊዜ፥ 6አብራም በሴኬም ወደሚገኘው ቅዱስ ስፍራ ወደ ሞሬ ዛፍ እስኪደርስ ድረስ ተጓዘ፤ በዚያን ጊዜ ከነዓናውያን በዚያች ምድር ይኖሩ ነበረ። 7እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና “ለዘርህ የምሰጠው ምድር ይህ ነው” አለው፤ ከዚህ በኋላ አብራም ለተገለጠለት አምላክ በዚያ ቦታ መሠዊያ ሠራ። #ሐ.ሥ. 7፥5፤ ገላ. 3፥16። 8ቀጥሎም ከቤትኤል በስተምሥራቅ ወዳለው ተራራማ አገር ወጣ፤ ቤትኤልን በስተምዕራብ፥ ዐይን በስተምሥራቅ አድርጎ ድንኳኑን ተከለ፤ በዚያም መሠዊያ ሠራና ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ 9ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረም ወደ ኔጌብ መጣ። #12፥9 ኔጌብ፦ በዕብራይስጥ “ደቡባዊ አገር” ማለት ነው።
አብራም በግብጽ አገር
10በከነዓን ምድር ራብ ገባ፤ ራብም እየበረታ በመሄዱ አብራም የራቡን ጊዜ ለማሳለፍ በስተደቡብ ርቆ ወደ ግብጽ አገር ሄደ። 11አብራም ወደ ግብጽ ምድር ለመግባት በተቃረበ ጊዜ ሚስቱን ሣራይን እንዲህ አላት፤ “አንቺ በጣም ቈንጆ ሴት መሆንሽን ዐውቃለሁ፤ 12ግብጻውያን አንቺን በሚያዩበት ጊዜ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ በማለት እኔን ይገድሉኛል፤ አንቺን ግን በሕይወት እንድትኖሪ ይተዉሻል። 13ስለዚህ ‘እኅቱ ነኝ’ በያቸው፤ በዚህ ዐይነት በአንቺ ምክንያት በሕይወት እንድኖር ይተዉኛል፤ በደኅና ዐይንም ይመለከቱኛል።” #ዘፍ. 20፥2፤ 26፥7።
14ወደ ግብጽ በገቡ ጊዜ በእርግጥም ግብጻውያን የአብራም ሚስት በጣም ቈንጆ እንደ ሆነች አዩ። 15እንዲሁም አንዳንድ የፈርዖን ባለሟሎች ባዩአት ጊዜ ስለ ቁንጅናዋ ለፈርዖን ተናገሩ፤ ስለዚህ ወደ ቤተ መንግሥት ተወሰደች። 16በእርስዋ ምክንያት ንጉሡ አብራምን በደኅና ዐይን ተመለከተው፤ በጎች፥ ከብቶች፥ አህዮች፥ ግመሎች፥ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን ሰጠው።
17ነገር ግን በአብርሃም ሚስት በሣራይ ምክንያት እግዚአብሔር በእርሱና በባለሟሎቹ ሁሉ ላይ አሠቃቂ በሽታዎች አመጣባቸው። 18ከዚህ በኋላ ፈርዖን አብራምን አስጠርቶ እንዲህ ሲል ጠየቀው “ይህ ያደረግኽብኝ ነገር ምንድን ነው? ሣራይ ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልነገርከኝም? 19‘እኅቴ ነች’ ብለህ በሚስትነት እንድወስዳት ለምን አደረግህ? ይህችውና ሚስትህ፥ ይዘሃት ውጣ፤” 20ንጉሡ ባዘዛቸው መሠረት ባለሟሎቹ አብራምንና ሚስቱን ካለው ሀብት ሁሉ ጋር ከአገር አስወጡአቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 12: አማ05
Qaqambisa
Share
Copy
Ufuna ukuba iimbalasane zakho zigcinwe kuzo zonke izixhobo zakho? Bhalisela okanye ngena
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997