የዮሐንስ ወንጌል 10
10
የበጎች በር ምሳሌ
1“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች ስፍራ በበሩ የማይገባ፥ በሌላም በኩል የሚገባ ሌባ፥ ወንበዴም ነው። 2በበሩ የሚገባ ግን የበጎች ጠባቂ ነው። 3ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፤ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ አውጥቶም ያሰማራቸዋል። 4ሁሉንም አውጥቶ ባሰማራቸው ጊዜ በፊት በፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ይከተሉታል፤ ቃሉን ያውቃሉና። 5ሌላውን ግን ይሸሹታል እንጂ አይከተሉትም፤ የሌላውን ቃሉን አያውቁምና።” 6ጌታችን ኢየሱስም ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸውን አላወቁም።
7ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የበጎች በር እኔ ነኝ። 8ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ነገር ግን፤ በጎች አልሰሙአቸውም። 9እውነተኛዉ የበጎች#“እውነተኛ የበጎች” የሚለው በግሪኩ የለም። በር እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩልም የሚገባ ይድናል፤ ይገባልም ይወጣልም፤ መሰማርያም ያገኛል። 10ሌባ ግን ሊሰርቅና ሊያርድ፥ ሊያጠፋም ካልሆነ በቀር አይመጣም፤ እኔ ግን የዘለዓለም#“የዘለዓለም” የሚለው በግሪኩ የለም። ሕይወትን እንዲያገኙ፥ እጅግም እንዲበዛላቸው መጣሁ።
ስለ ቸር ጠባቂ
11“ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። 12ጠባቂ ያይደለ፥ በጎቹም ገንዘቡ ያይደሉ ምንደኛ ግን፥ ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም መጥቶ በጎችን ይነጥቃቸዋል፥ ይበትናቸዋልም። 13ምንደኛስ ይሸሻል፤ ስለ በጎችም አያዝንም፤ ምንደኛ ነውና። 14ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤ የእኔ የሆኑትን መንጋዎችን አውቃለሁ፤ የእኔ የሆኑትም ያውቁኛል። 15#ማቴ. 11፥27፤ ሉቃ. 22፥33፤ ዘሌ. 24፥16። አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን አውቀዋለሁ፤ ለበጎችም ቤዛ አድርጌ ሰውነቴን አሳልፌ እሰጣለሁ። 16ከዚህ ቦታ ያይደሉ ሌሎች በጎችም አሉኝ፤ እነርሱንም ወደዚህ አመጣቸው ዘንድ ይገባኛል፤ ቃሌንም ይሰሙኛል፤ ለአንድ እረኛም አንድ መንጋ ይሆናሉ። 17ስለዚህም፤ አብ ይወድደኛል፥ እንደ ገና አስነሣት ዘንድ እኔ ነፍሴን እሰጣለሁና። 18ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ ነገር ግን እኔ በፈቃዴ እሰጣታለሁ፤ እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝና፤ ይህንም ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።”
አይሁድ ለሁለተኛ ጊዜ ስለ መለያየታቸው
19ስለዚህም ነገር አይሁድ እንደገና እርስ በርሳቸው ተለያዩ። 20ከእነርሱም ብዙዎች፥ “ጋኔን ይዞት ያብዳል፤ ለምንስ ታዳምጡታላችሁ?” አሉ። 21ሌሎችም ይህ ነገር ጋኔን ከያዘው ሰው የሚገኝ አይደለም፤ ጋኔን የዕዉሮችን ዐይን ማብራት ይችላልን?” አሉ።
ስለ ቤተ መቅደስ መታደስ
22በዚያም ወራት በኢየሩሳሌም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ክረምትም ነበር። 23ጌታችን ኢየሱስም በቤተ መቅደስ በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ይመላለስ ነበር። 24አይሁድም እርሱን ከብበው፥ “እስከ መቼ ድረስ ሰውነታችንን ታስጨንቀናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን” አሉት። 25ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “አታምኑኝም እንጂ ነገርኋችሁ፤ እኔ በአባቴ ስም የምሠራው ሥራ እርሱ ምስክሬ ነው። 26እናንተ ግን አታምኑኝም፤ እንደ ነገርኋችሁ ከበጎች ውስጥ አይደላችሁምና። 27የእኔ የሆኑ በጎች ግን ቃሌን ይሰሙኛል፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል። 28እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘለዓለሙም አይጠፉም፤ ከእጄም የሚነጥቃቸው የለም። 29እነርሱን የሰጠኝ አባቴ እርሱ ከሁሉ ይበልጣልና፤ ከአባቴም እጅ መንጠቅ የሚችል የለም። 30እኔና አብ አንድ ነን።”
ስለ አይሁድ ጥላቻ
31ዳግመኛም አይሁድ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ። 32ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ በየትኛው ሥራ ምክንያት ትወግሩኛላችሁ?” 33አይሁድም፥ “አንተ፥ ሰው ስትሆን ራስህን እግዚአብሔርን ታደርጋለህና፤ ስለ መሳደብህ ነው እንጂ ስለ መልካም ሥራህስ አንወግርህም” አሉት። 34#መዝ. 81፥6። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እኔ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በኦሪታችሁ ተጽፎ የለምን? 35የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን እነዚያን አማልክት ካላቸው፥ የመጽሐፉ ቃል ይታበል ዘንድ አይቻልም። 36እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብላችሁ፥ አብ የቀደሰውንና ወደ ዓለምም የላከውን እንዴት ትሳደባለህ? ትሉኛላችሁ። 37የአባቴን ሥራ ባልሠራ በእኔ አትመኑ። 38ከሠራሁ ግን፥ እኔን እንኳን ባታምኑ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ታውቁና ትረዱ ዘንድ ሥራዬን እመኑ።” 39ዳግመኛም ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም አመለጠ።
ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ስለ መሄዱ
40 #
ዮሐ. 1፥28። ዳግመኛም ቀድሞ ዮሐንስ ያጠምቅበት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ሄደ፤ በዚያም ተቀመጠ። 41ብዙዎችም ወደ እርሱ ሄደው፥ “ዮሐንስ ምንም ያደረገው ተአምራት የለም፤ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ሆነ” አሉ። 42በዚያም ብዙ ሰዎች አመኑበት።
Pilihan Saat Ini:
የዮሐንስ ወንጌል 10: አማ2000
Sorotan
Berbagi
Salin
Ingin menyimpan sorotan di semua perangkat Anda? Daftar atau masuk