የሉቃስ ወንጌል 5
5
ስለ ስምዖንና ስለ ዘብዴዎስ ልጆች መጠራት
1ብዙ ሰዎችም በእርሱ ዘንድ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ይሰሙ ነበር፤ እርሱ ግን በጌንሴሬጥ ባሕር ወደብ ቁሞ ነበር። 2በባሕሩም ዳር ሁለት ታንኳዎች ቁመው አየ፤ ከእነርሱም ውስጥ ዓሣ አጥማጆች መረባቸውን ሊያጥቡ ወረዱ። 3#ማቴ. 13፥1-2፤ ማር. 3፥9-10፤ 4፥1። ከሁለቱ ታንኳዎች ወደ አንዲቱ ታንኳ ወጣ፤ ይቺውም ታንኳ የስምዖን ነበረች፤ “ከምድር ጥቂት እልፍ አድርጋት” አለው፤ በታንኳዪቱም ውስጥ ተቀምጦ ሕዝቡን አስተማራቸው። 4ትምህርቱንም ከፈጸመ በኋላ ስምዖንን፥ “ወደ ጥልቁ ባሕር ፈቀቅ በል፤ መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ” አለው። 5#ዮሐ. 21፥3። ስምዖንም መልሶ፥ “መምህር፥ ሌሊቱን ሁሉ ደክመናል፤ የያዝነውም የለም፤ ነገር ግን ስለ አዘዝኸን መረቦቻችንን እንጥላለን” አለው። 6#ዮሐ. 21፥6። እንዳዘዛቸውም ባደረጉ ጊዜ፥ መረቡ እስኪቀደድ ድረስ ብዙ ዓሣ ተያዘ። 7መጥተውም ይረዱአቸው ዘንድ በሌላ ታንኳ የነበሩትን ባልንጀሮቻቸውን ጠሩ፤ መጥተውም እስኪጠልቁ ድረስ ሁለቱን ታንኳዎች ሞሉ። 8ስምዖን ጴጥሮስም ይህን አይቶ ከጌታችን ከኢየሱስ እግር በታች ሰገደና፥ “እኔ ኀጢአተኛ ሰው ነኝና አቤቱ ከእኔ ፈቀቅ በል፤” አለው። 9እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ስለ ተያዘው ዓሣ ተደንቀው ነበርና። 10እንዲሁም የስምዖን ባልንጀራዎች የነበሩ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ተደነቁ፤ ጌታችን ኢየሱስም ስምዖንን፥ “አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህስ ሰውን ታጠምዳለህ” አለው። 11ታንኳዎቻቸውንም ወደ ምድር አወጡና ሁሉን ትተው ተከተሉት።
ለምጻሙን ስለ ማዳኑ
12በአንዲት ከተማ ሳለም ሁለመናው ለምጻም የሆነ ሰው መጣ፤ ጌታችን ኢየሱስንም ባየው ጊዜ በፊቱ ወድቆ ሰገደለትና፥ “አቤቱ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” እያለ ማለደው። 13እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና፥ “እወዳለሁ ንጻ” አለው፤ ያንጊዜም ለምጹ ለቀቀው። 14#ዘሌ. 14፥1-32። ለማንም እንዳይናገር ከለከለው፤ “ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አስመርምር፤ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ ነጻህ ሙሴ እንደ አዘዘ መባህን አቅርብ” ብሎ አዘዘው። 15ዜናውም በሁሉ ተሰማ፤ ብዙ ሰዎችም ትምህርቱን ሊሰሙ፥ ከደዌአቸውም ሊፈወሱ ይመጡ ነበር። 16እርሱ ግን ወደ ምድረ በዳ እየወጣ ይጸልይ ነበር።
ስለ መጻጒዕ መፈወስ
17ከዚህም በኋላ፥ ከዕለታት በአንድ ቀን ሲያስተምራቸው እንዲህ ሆነ፤ ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮች፥ ከኢየሩሳሌምም የመጡ ፈሪሳውያንና የኦሪት መምህራን ነበሩ፤ እርሱም ይፈውስ ዘንድ የእግዚአብሔር ኀይል ነበረ። 18እነሆ፥ ሰዎች በአልጋ ተሸክመው ሽባ የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እንዲፈውሰውም ወደ እርሱ ሊያስገቡት ወደዱ። 19ሰውም ተጨናንቆ ነበርና የሚያስገቡበት አጡ፤ ወደ ሰገነትም ወጡ፤ ጣራውንም አፍርሰው ወደ ቤቱ ውስጥ በጌታችን በኢየሱስ ፊት ከነአልጋው አወረዱት። 20እምነታቸውንም አይቶ ያን ሰው፥ “ኀጢአትህ ተሰረየልህ” አለው። 21ጻፎችና ፈሪሳውያንም፥ “የሚሳደብ ይህ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኀጢአትን ማስተስረይ ማን ይችላል?” ብለው ያስቡ ጀመር። 22ጌታችን ኢየሱስም የሚያስቡትን ዐወቀባቸውና እንዲህ አላቸው፥ “በልባችሁ ምን ታስባላችሁ? 23ኀጢአትህ ተሰረየልህ ከማለትና ተነሥተህ ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል? 24ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤ ያን ሽባ፦ ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ ብዬሃለሁ” አለው። 25ያንጊዜም ተነሥቶ ተኝቶበት የነበረውን አልጋ በፊታቸው ተሸክሞ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ። 26ሁሉም ተደነቁ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፤ እጅግም እየፈሩ፥ “ዛሬ ድንቅ ነገር አየን” አሉ።
ስለ ቀራጩ ሌዊ መጠራት
27ከዚህም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ሌዊ የሚባል ቀራጭ ሰው በቀረጥ መቀበያው ቦታ ተቀምጦ አየና፥ “ተከተለኝ” አለው። 28ሁሉንም ተወና ተነሥቶ ተከተለው። 29ሌዊም በቤቱ ታላቅ ግብዣ አደረገለት፤ ብዙ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ከእርሱም ጋር ለምሳ ተቀምጠው የነበሩ ቀራጮችና ኀጢአተኞች፥ ሌሎችም ብዙዎች ነበሩ። 30#ሉቃ. 15፥1-2። ጻፎችና ፈሪሳውያንም፥ “ከቀራጮችና ከኃጥኣን ጋር ለምን ትበላላችሁ? ትጠጡማላችሁ?” ብለው በደቀ መዛሙርቱ ላይ አንጐራጐሩ። 31ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ባለ መድኀኒትን በሽተኞች እንጂ ጤነኞች አይሹትም። 32ኃጥኣንን ወደ ንስሓ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም።”
ስለ ጾም
33እነርሱም፥ “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስለምን በብዙ ይጾማሉ? ጸሎትስ ስለምን ያደርጋሉ? የፈሪሳውያን ወገኖች የሆኑትም ስለምን እንዲሁ ያደርጋሉ? ያንተ ደቀ መዛሙርት ግን ለምን ይበላሉ? ይጠጣሉም?” አሉት። 34ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “የሙሽራው ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ መጾም አይችሉም። 35ነገር ግን ሙሽራውን ከእነርሱ የሚወስዱበት ቀን ይመጣል፤ ያንጊዜም ይጾማሉ።” 36በምሳሌም እንዲህ አላቸው፥ “በአሮጌ ልብስ ቀዳዳ ላይ የአዲስ ልብስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ያለዚያ ግን አዲሱ አሮጌውን ይቀድደዋል፤ አዲሱ እራፊም ከአሮጌው ጋር አይስማማም። 37አዲስ ጠጅንም በአሮጌ ረዋት የሚያደርግ የለም፤ ያለዚያ ግን ይቀድደዋል፤ ወይኑም ይፈስሳል፤ ረዋቱም ይቀደዳል። 38ነገር ግን አዲሱን ጠጅ በአዲስ ረዋት ያደርጉታል፤ እርስ በርሳቸውም ይጠባበቃሉ። 39የከረመውን የወይን ጠጅ ሊጠጣ ወድዶ አዲሱን የሚሻ የለም፤ የከረመው ይሻላል ይላልና።”
Právě zvoleno:
የሉቃስ ወንጌል 5: አማ2000
Zvýraznění
Sdílet
Kopírovat
Chceš mít své zvýrazněné verše uložené na všech zařízeních? Zaregistruj se nebo se přihlas