የሉቃስ ወንጌል 4
4
በዲያብሎስ ስለ መፈተኑ
1ጌታችን ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስን ተመልቶ ከዮርዳኖስ ተመለሰ፤ መንፈስም ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። 2አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ከዲያብሎስ ተፈተነ፥ በእነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፤ እነዚያም ቀኖች ከተፈጸሙ በኋላ ተራበ። 3ዲያብሎስም፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ ይህ ድንጋይ እንጀራ ይሁን በል” አለው። 4#ዘዳ. 8፥3። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ነው እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም የሚል ተጽፎአል” አለው። 5ዲያብሎስም ወደ ረዥም ተራራ አወጣው፤ የዓለምን መንግሥታትም ሁሉ በቅፅበት አሳየው። 6ዲያብሎስም እንዲህ አለው፥ “ይህን ሁሉ ግዛት፥ ይህንም ክብር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ለእኔ ተሰጥቶአልና፤ ለወደድሁትም እሰጠዋለሁና። 7ስለዚህ አንተ በፊቴ ብትሰግድልኝ ይህ ሁሉ ለአንተ ይሁንልህ።” 8#ዘዳ. 6፥13። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ሰይጣን ከኋላዬ ሂድ #በግሪኩና በአንዳንድ የግእዝ ትርጕም “ሰይጣን ከኋላዬ ሂድ” የሚለውን የሚጽፍም የማይጽፍም አለ። ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ልትሰግድ፥ እርሱንም ብቻ ልታመልክ ተጽፎአል” አለው። 9ወደ ኢየሩሳሌምም ወስዶ በቤተ መቅደሱ የማዕዘን ጫፍ ላይ አቆመው፤ እንዲህም አለው፥ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ አንተ ራስህ ወደ ታች መር ብለህ ውረድ። 10#መዝ. 90፥11። በመንገድህ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክትን ስለ አንተ ያዝዛቸዋል፤ 11#መዝ. 90፥12። እግርህም በድንጋይ እንዳትሰነካከል በእጃቸው ያነሡሃል” ተብሎ ተጽፎአልና። 12#ዘዳ. 6፥16። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ፈጣሪህ እግዚአብሔርን አትፈታተነው” ተብሎአል አለው። 13ዲያብሎስም በዚህ ሁሉ እርሱን መፈታተኑን ከፈጸመ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ።
ስለ መጀመሪያ ትምህርቱ
14ጌታችን ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተመልሶ ወደ ገሊላ ሄደ፤ ዝናውም በሀገሩ ሁሉ ተሰማ። 15በየምኵራባቸውም ሁሉ ያስተምራቸው ነበር፤ ትምህርቱንም ያደንቁ ነበር፤ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር።
በናዝሬት ስለ ማስተማሩ
16ወደ አደገበት ወደ ናዝሬትም ሄደ፤ በሰንበት ቀንም እንዳስለመደ ወደ ምኵራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ። 17የነቢዩን የኢሳይያስንም መጽሐፍ ሰጡት፤ መጽሐፉንም በገለጠ ጊዜ እንዲህ የሚል የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ። 18“የእግዚአብሔር መንፈስ በላዬ ነው፤ ስለዚህ ቀብቶ ለድሆች የምሥራችን እነግራቸው ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን እሰብክላቸው ዘንድ፥ ያዘኑትንም ደስ አሰኛቸው ዘንድ፥ ዕውሮችም ያዩ ዘንድ፥ የተገፉትንም አድናቸው ዘንድ፥ የታሰሩትንም እፈታቸው ዘንድ፥ የቈሰሉትንም አድናቸው ዘንድ፥ 19#ኢሳ. 61፥1-2። የተመረጠችውንም የእግዚአብሔርን ዓመት እሰብክ ዘንድ ላከኝ።” 20መጽሐፉንም አጥፎ ለተላላኪው ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኲራብም የነበሩት ሁሉ ዐይናቸውን አትኲረው ተመለከቱት። 21እርሱም፥ “የዚህ የመጽሐፍ ነገር ዛሬ በጆሮአችሁ ደረሰ፤ ተፈጸመም” ይላቸው ጀመር። 22ሁሉም የንግግሩን መከናወን መሰከሩለት፤ የአንደበቱንም ቅልጥፍና እያደነቁ፥ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር። 23እርሱም፥ “በውኑ ባለ መድኀኒት ራስህን አድን፤ በቅፍርናሆም ያደረግኸውንና የሰማነውን ሁሉ በዚህም በሀገርህ ደግሞ አድርግ ብላችሁ ይህችን ምሳሌ ትመስሉብኛላችሁ” አላቸው። 24#ዮሐ. 4፥44። እንዲህም አላቸው፥ “እውነት እላችኋለሁ፤ ነቢይ በሀገሩ አይከብርም። 25#1ነገ. 17፥8-16። እውነት እላችኋለሁ፤ በነቢዩ በኤልያስ ዘመን በምድር ሁሉ ብርቱ ረኃብ እስኪሆን ድረስ ሰማይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር በተዘጋበት ጊዜ ብዙ መበለቶች በእስራኤል ውስጥ ነበሩ። 26ኤልያስ የሲዶና ክፍል በምትሆን በስራጵታ ወደምትኖር ወደ አንዲት መበለት ሴት እንጂ ከእነዚህ ወደ አንዲቱ እንኳን አልተላከም። 27#2ነገ. 5፥1-14። በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም ብዙ ለምጻሞች በእስራኤል ውስጥ ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነዚያ አንድ እንኳን አልነጻም።”
28በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ይህን ሰምተው ተቈጡ። 29ያንጊዜም ተነሥተው ከከተማ ወደ ውጭ አወጡት፤ ገፍተውም ይጥሉት ዘንድ ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ተራራ ጫፍ ወሰዱት። 30እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።
ወደ ቅፍርናሆም ስለ መሄዱ
31ወደ ገሊላ ከተማም ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር። 32#ማቴ. 7፥28-29። አነጋገሩም በትእዛዝ ነበርና ትምህርቱን ያደንቁ ነበር።
ጋኔን የያዘውን ስለ ማዳኑ።
33በምኵራብም ርኩስ መንፈስ የያዘው አንድ ሰው ነበር፤ በታላቅ ቃልም ጮኾ፦ 34“የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ያለጊዜአችን ልታጠፋን መጣህን? የእግዚአብሔር ቅዱስ ሆይ፥ አንተ ማን እንደሆንህ ዐውቅሃለሁ” አለ። 35ጌታችን ኢየሱስም፥ “ዝም በልና ከእርሱ ውጣ” ብሎ ገሠጸው፤ ጋኔኑም በምኵራቡ መካከል ጣለውና ከእርሱ ወጣ፤ ነገር ግን ምንም አልጐዳውም። 36ሁሉም ደነገጡ፤ እርስ በርሳቸውም ተነጋገሩ፤ እንዲህም አሉ፥ “ይህ ነገር ምንድን ነው? ክፉዎችን አጋንንት በሥልጣንና በኀይል ያዝዛቸዋልና፥ እነርሱም ይወጣሉና።” 37ዝናውም በዙሪያዉ ባሉ መንደሮች ሁሉ ወጣ፤ ተሰማም።
ስለ ጴጥሮስ አማትና ስለ ሌሎችም በሽተኞች መፈወስ
38ከምኵራቡም ወጥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ፤ የስምዖን አማትም በብርቱ ንዳድ ታማ ነበርና ስለ እርስዋ ነገሩት። 39በአጠገብዋም ቁሞ ንዳድዋን ገሠጸውና ተዋት፤ ወዲያውም ተነሥታ አገለገለቻቸው። 40ፀሐይም በገባ ጊዜ ልዩ ልዩ ደዌ ያለባቸውን ድውያን ሁሉ አመጡለት፤ ከእነርሱም በእያንዳንዱ ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው። 41ብዙ አጋንንትም፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” እያሉና እየጮሁ ይወጡ ነበር፤ እርሱም ይገሥጻቸው ነበር፤ ክርስቶስም እንደ ሆነ ያውቁ ነበርና እንዲናገሩ አይፈቅድላቸውም ነበር።
42በነጋ ጊዜም ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም እየፈለጉት ወደ እርሱ ሄዱ፤ አልፎአቸው እንዳይሄድም አቆሙት። 43እርሱ ግን፥ “ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎች ከተሞች ደግሞ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል እነግራቸው ዘንድ ይገባኛል” አላቸው። 44በገሊላ ምኲራቦችም ይሰብክ ነበር።
Právě zvoleno:
የሉቃስ ወንጌል 4: አማ2000
Zvýraznění
Sdílet
Kopírovat
Chceš mít své zvýrazněné verše uložené na všech zařízeních? Zaregistruj se nebo se přihlas