ኦሪት ዘኍልቍ 29
29
በበዓለ መጥቅዕ የሚቀርብ መሥዋዕት
(ዘሌ. 23፥23-25)
1“በሰባተኛውም ወር ከወሩ የመጀመሪያዋ ቀን ለእናንተ ይህች ዕለት የተቀደሰች ናት፤#ዕብ. “በመጀመሪያ ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ” ይላል። የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩባት፤ ምልክት ያለባት ቀን ትሁንላችሁ።#ዕብ. “መለከቶች የሚነፉበት ቀን ነው” ይላል። 2ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ ከላሞች አንድ በሬ፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት፥ የበግ ጠቦቶች፥ 3ለእህል ቍርባናቸው በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለበሬው ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራው በግ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥ 4ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ዐሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ። 5ማስተስረያም የሚሆንላችሁን ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ። 6በወሩ መባቻ ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን እንደ ሕጋቸው ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን በእሳት የሚቀርቡ ናቸው።
በኀጢአት ማስተስረያ ቀን የሚቀርብ መሥዋዕት
(ዘሌ. 23፥26-32)
7“የዚህም ወር ዐሥረኛዋ ቀን ለእናንተ የተቀደሰች ትሁንላችሁ፤#ዕብ. “በዐሥረኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ” ይላል። ሰውነታችሁን አስጨንቁአት፤ ከሥራ ሁሉ ምንም አታድርጉ። 8ለእግዚአብሔርም በጎ መዓዛ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት ፥ ከላሞች አንድ በሬ፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ ነውር የሌለባቸውም ይሁኑላችሁ። 9ለእህል ቍርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለበሬው ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራው በግ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥ 10ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ዐሥረኛ እጅ፥ 11ለኀጢአት መሥዋዕት፥ ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ። ከሚያስተሰርየው ከኀጢአት መሥዋዕት፥ በዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጥ ቍርባናቸውም ሌላ አቅርቡት።
በዳስ በዓል ቀን የሚቀርብ መሥዋዕት
(ዘሌ. 23፥33-44)
12“በሰባተኛውም ወር ዐሥራ አምስተኛዋ ቀን ለእናንተ የተቀደሰች ትሁንላችሁ፤#ዕብ. “በዐሥራ አምስተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ” ይላል። የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩባት፤ ሰባት ቀንም ለእግዚአብሔር በዓል አድርጉ። 13ለእግዚአብሔርም በጎ መዓዛ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ ዐሥራ ሦስት በሬዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ነውር የሌለባቸውም ይሁኑ። 14ለእህል ቍርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለዐሥራ ሦስት በሬዎች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለሁለቱ አውራ በጎች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥ 15ለዐሥራ አራቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ዐሥረኛ እጅ፥ 16ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ የሚቀርቡ ናቸው።
17“በሁለተኛውም ቀን ዐሥራ ሁለት በሬዎችን፥ ሁለት አውራ በጎችን፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶችን፥ 18ለበሬዎቹና ለአውራ በጎቹ፥ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራችው መጠን እንደ ሕጉ፥ 19ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየልን ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባናቸው ሌላ የሚቀርቡ ናቸው።
20“በሦስተኛውም ቀን ዐሥራ አንድ በሬዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 21ለበሬዎቹና ለአውራ በጎቹ፥ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጋቸው፥ 22ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
23“በአራተኛውም ቀን ዐሥር በሬዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸው ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 24ለበሬዎቹና ለአውራ በጎቹ፥ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራችው መጠን እንደ ሕጋቸው፥ 25ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
26“በአምስተኛው ቀን ዘጠኝ በሬዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸው ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 27ለበሬዎቹና ለአውራ በጎቹ፥ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጋቸው፥ 28ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
29“በስድስተኛውም ቀን ስምንት በሬዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 30ለበሬዎችና ለአውራ በጎቹ፥ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጋቸው፥ 31ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
32“በሰባተኛውም ቀን ሰባት በሬዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 33ለበሬዎቹ፥ ለአውራ በጎቹ፥ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጋቸው፥ 34ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
35“ስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ በዓል ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። 36ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን በእሳት የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ በሬ፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ። 37የእህል ቍርባናቸውና የመጠጥ ቍርባናቸው ለበሬው፥ ለአውራውም በግ፥ ለጠቦቶቹም እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጋቸው ይሆናሉ። 38ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ የሚቀርቡ ናቸው።
39“እነዚህንም፥ ከስእለታችሁና በፈቃዳችሁ ከምታመጡት ሌላ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለእህልም፥ ለመጠጥም ቍርባን፥ ለደኅንነትም መሥዋዕታችሁ በበዓላችሁ ጊዜ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።” 40ሙሴም ለእስራኤል ልጆች እግዚአብሔር ለሙሴ ያዘዘውን ሁሉ ነገራቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 29: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in