ኦሪት ዘሌዋውያን 3
3
የደኅንነት መሥዋዕት
1“ለእግዚአብሔር የሚቀርበው ቍርባን የደኅንነት መሥዋዕት ቢሆን፥ ከላሞች መንጋ ተባት ወይም እንስት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለበትን በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ። 2እጁንም ለቍርባን በቀረበው ራስ ላይ ይጭናል፤ በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ አጠገብ ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በሚቃጠለው መሥዋዕት፥ በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 3ከደኅንነቱም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርገው ያቀርባሉ፤ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 4ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶቹ ጋር ያመጣሉ። 5የአሮንም ልጆች ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በዕንጨቱ ላይ ያቀርቡታል፤ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ነው።
6“ለእግዚአብሔርም ለደኅንነት መሥዋዕት የሚያቀርበው ቍርባኑ ከበጎች ተባት ወይም እንስት ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ያቀርባል። 7ለቍርባኑ የበግ ጠቦትን ቢያቀርብ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፤ 8እጁንም ለቍርባን በቀረበው ራስ ላይ ይጭናል በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ያርደዋል፤ ካህናቱም የአሮን ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 9ከደኅንነቱም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል፤ ስቡን፥ እስከ ጀርባውም ድረስ የተቈረጠ ሙሉ ላቱን፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 10ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑም አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶቹ ጋር ይወስዳል። 11ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቀርበዋል፤ በጎ መዓዛ ያለው ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።
12“ቍርባኑም ፍየል ቢሆን በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፤ 13እጁንም በራሱ ላይ ይጭንበታል፤ በምስክሩ ድንኳን ደጃፍም ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 14ከእርሱም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርጎ ያቀርበዋል፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 15ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶቹ ጋር ይወስዳል። 16ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቀርበዋል፤ ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ያለው የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። ስቡ ሁሉ ለእግዚአብሔር ነው። 17ስብና ደም እንዳትበሉ በምትኖሩበት ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዐት ነው።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 3: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in