2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2
2
የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ወታደር ስለ መሆን
1እንግዲህ ልጄ ሆይ! አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ። 2በብዙ ምስክሮች ፊት ከእኔ የሰማኸውን ታማኝ ለሆኑ ሌሎችንም ደግሞ ማስተማር ለሚችሉ ሰዎች አደራ ስጥ። 3እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ መልካም ወታደር ሆነህ መከራን ተቀበል። 4በማገልገል ላይ ያለ ማንም ወታደር፥ ዐላማው ለወታደርነት የመለመለውን ሰው ለማስደሰት እስከሆነ ድረስ፥ እንደ ማናቸውም ሰው በዕለት ተዕለት ጉዳዮች አይጠመድም። 5እንዲሁም ደግሞ ማንም ሯጭ ውድድሩን እንደ ሕጉ ካልተወዳደረ የድሉን አክሊል አያገኝም። 6በርትቶ ለሚሠራው ገበሬ የፍሬው የመጀመሪያ ድርሻ ለእርሱ ሊሆን ይገባዋል። 7ጌታ በሁሉ ነገር ማስተዋልን ይሰጥሃልና የምለውን ደኅና አድርገህ አሰላስል።
8በወንጌል የምሰብከውን፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ። 9ለዚህም ወንጌል ስል መከራን እቀበላለሁ፥ እንደ ወንጀለኛም በሰንሰለት እስከመታሰር ደርሻለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም። 10ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሰሱስ ያለውን መዳን ከዘለዓለም ክብር ጋር እንዲያገኙ ስል ስለ ተመረጡት ደግሞ ሁሉን ነገር እታገሣለሁ። 11እንዲህ የሚለው ቃል የታመነ ነው፦
“ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፤
12 #
ማቴ. 10፥33፤ ሉቃ. 12፥9። ብንጸና፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤
ብንክደው፥ እርሱ ደግሞ ይክደናል፤
13እኛ ታማኝ ባንሆን፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና።”
በእግዚአብሔር የተመሰከረለት ትጉህ ሠራተኛ
14ይህን አሳስብ፤ እንዲሁም በቃላት እንዳይከራከሩ በእግዚአብሔር ፊት እዘዝ፤ ይህ የሚሰሙትን ሰዎች ያጠፋል እንጂ ምንም ጥቅም የለውምና። 15የእውነትን ቃል በትክክለኛው መንገድ እየገለጥህ፥ የሚያፍርበት ነገር እንደሌለው ሠራተኛ፥ ለእግዚአብሔር ብቁ ተደርገህ ራስህን ለማቅረብ የተቻለህን ሁሉ ጣር። 16ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ምክንያቱም ሰዎችን ከፊት ይልቅ ወደ ኃጢአት ይመራልና፤ 17ቃላቸውም እንደ ቈላ ቊስል ይባላል፤ ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ከእነርሱ መካከል ናቸው፤ 18እነዚህም፦ “ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል፤” እያሉ በእውነት ነገር ስተው ሄደዋል፤ የአንዳንዶችንም እምነት አጥፍተዋል። 19#ዘኍ. 16፥5።ሆኖም የእግዚአብሔር ጠንካራ መሠረት የቆመው፦ “ጌታ የራሱ የሆኑትን ያውቃል፤” እንዲሁም “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዐመፅ ይራቅ፤” የሚለውን ማኅተም ታትሞ ነው።
20በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ የወርቅና የብር ዕቃዎች ብቻ ሳይሆኑ የእንጨትና የሸክላ ዕቃዎችም ደግሞ ይኖራሉ፤ እኩሌቶቹም ለክብር፥ እኩሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ 21እንግዲህ ማንም ለውርደት ከሚሆነው ነገር ራሱን ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን፥ የተቀደሰ፥ ለጌታውም የሚጠቅም፥ ለመልካምም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል። 22ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፤ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን፥ እምነትን፥ ፍቅርን፥ ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። 23ጠብንም እንደሚያመጡ ታውቃለህና ከሞኝነትና ከከንቱ ንትርክ ራቅ። 24የጌታም ባርያ ጠበኛ መሆን አይገባውም፤ ይልቁንስ ለሰው ሁሉ ገር፥ ለማስተማር ብቃት ያለው፥ 25ትዕግሥተኛና የሚቃወሙትን በየዋህነት የሚገሥጽ ሊሆን ይገባዋል። ከዚህም የተነሣ ምናልባት እግዚአብሔር ንስሓ ገብተው እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲመጡ፥ 26እንዲሁም ፈቃዱን ለመፈጸም ታስረው ከተያዙበት ከዲያብሎስ ወጥመድ ወጥተው ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ ያደርጋቸዋልና።
Currently Selected:
2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in