YouVersion Logo
Search Icon

2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1

1
ሰላምታ
1በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው የሕይወት ተስፋ መሠረት በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፤ 2#የሐዋ. 16፥1።ለተወደደው ልጄ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን።
ለወንጌል ታማኝ መሆን እንደሚገባ
3ያለማቋረጥ ሌሊትና ቀን በጸሎቴ አንተን በማስታወስ፥ አባቶቼ እንዳደረጉት በንጹሕ ኅሊና የማገለግለውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ 4በደስታ እንድሞላ እንባህን እያስታወስኩ ላይህ እናፍቃለሁ። 5#የሐዋ. 16፥1።በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስታውሳለሁ፤ ይህም እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድና በእናትህ በኤውንቄ የነበረ ነው፤ አሁን ደግሞ በአንተ እንዳለ እርግጠኛ ነኝ። 6በዚህም ምክንያት እጆቼን ስጭን የተሰጠህን በአንተ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እንድታቀጣጥል አሳስብሃለሁ። 7እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።
8እንግዲህ ስለ ጌታችን ምስክርነት በመስጠት ወይም ስለ እርሱ በታሰርሁ በእኔ አትፈር ይልቁንም እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል።
የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ
9እንደ ሥራችን መጠን ሳይሆን እንደ ራሱ ዕቅድና እንደ ጸጋው መጠን አዳነን፥ በቅዱስም አጠራር ጠራን፤ ይህም ጸጋ ከዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፤ 10አሁን ግን በወንጌል አማካይነት ሞትን በሻረው፥ ሕይወትንና ያለመበስበስን ወደ ብርሃን ባመጣው በአዳኛችን በክርስቶስ ኢየሱስ መገለጥ በኩል ተገለጠ። 11#1ጢሞ. 2፥7።እኔም ለዚህ ወንጌል ሰባኪና ሐዋርያ አስተማሪም ሆኜ ተሾምሁ፤ 12በዚህም ምክንያት ይህን መከራ ደግሞ እቀበላለሁ፤ ነገር ግን ያመንኩትን አውቃለሁና አላፍርበትም፤ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ለመጠበቅ እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ። 13በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር ከእኔ የሰማኸውን እውነተኛ ቃላት ምሳሌ አድርገህ ያዝ፤ 14በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ መልካሙን አደራ ጠብቅ።
15በእስያ ያሉት ሁሉ ከእኔ ዘወር ብለው እንደ ሄዱ ታውቃለህ፤ ከእነርሱም መካከል ፊሎጎስና ሄርዋጌኔስ ይገኛሉ። 16ጌታ ለሄኔሲፎሩ ቤተሰብ ምሕረትን ይስጥ፤ ብዙ ጊዜ አሳርፎኛልና፤ በሰንሰለቴም አላፈረበትም፤ 17ነገር ግን ወደ ሮም በመጣ ጊዜ በትጋት ፈልጎ አገኘኝ፤ 18በዚያን ቀን ከጌታ ምሕረትን እንዲያገኝ ጌታ ይስጠው፤ በኤፌሶንም ያከናወነውን አገልግሎት ሁሉ አንተ ደኅና አድርገህ ታውቃለህ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1