YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 12

12
ዮናታን ከሮም እና ከእስፖርታ የነበረው ግንኙነት
1ዮናታን የጊዜው ሁናቴ ለእርሱ ምቹ ሆኖ ስላገኘው ከሮማውያን ጋር የነበረውን ወዳጅነት ለማጽናትና ለማሳደስ ፈልጐ ወደ ሮም የሚልካቸውን ሰዎች መረጠ። 2እንዲሁም በዚሁ ዓይነት ወደ እስፖርታ ወደ ሌሎችም ቦታዎች ደብዳቤዎችን ላከ። 3ወደ ሮም የሄዱት መልእክተኞች በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው እንዲህ አሉ፤ “ሊቀ ካህናት ዮናታንና የአይሁድ ሕዝብ ቀድሞ የነበረውን ወዳጅነትና የስምምነት ውል ለማደስ ልከውናል”። 4ምክር ቤቱም ለእያንዳንዱ አገር ባለ ሥልጣኖች በሰላም ወደ ይሁዳ አገር እንዲያሳልፉቸው ደብዳቤዎች ሰጧቸው። 5ዮናታን ለእስፖርታ ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ ግልባጭ እንዲህ የሚል ነበር፤ 6“ሊቀ ካህናቱ ዮናታንና የሕዝቡ ምክር ቤት፥ ካህናቱ፥ የቀረውም የአይሁድ ሕዝብ ለወንድሞቻቸው ለእስፖርታውያን ሰዎች ሰላምታ ያቀርባሉ፤ 7ከዚህ በታች የሚገኘው ግልባጭ እንደሚመሰክረው ከዚህ ቀደምም በእናንተ ነግሦ ከነበረው ከአሪዮስ የወንድምነት ምልክት የሆነ ደብዳቤ ለሊቀ ካህናት ኦንያስ ተልኳል፤ 8ኦንያስ መልእክተኛውን በክብር አስተናግዷል፤ የስምምነትና የወዳጅነት ጉዳይ ያለበትን ደብዳቤም ተቀብሏል። 9በእኛ በኩል ይህ ጉዳይ አስፈላጊያችን ባይሆንም የቅዱሳት መጽሐፍትን ጽናት ይዘን የቀደመውንና ከእናንተ ጋር የነበረንን 10ወንድማማችነት በማደስ ባዕድነትን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው፥ የመጨረሻውን ደብዳቤ ከላካችሁልን እጅግ ብዙ ዘመናት ተቆጥረዋል፤ 11በበዓላትና በሌሎችም ቀናት በምናደርጋቸው መሥዋዕቶችና ጸሎቶች ሁልጊዜ ለወንድሞች መደረግ እንደሚገባና እንደሚያስፈልግ እናንተን ሳናስታውስ ቀርተን አናውቅም። 12በክብራችሁ እንደሰታለን። 13እኛ ግን መከራዎችንና ጦርነቶች ደርሰውብናል፤ በዙሪያችን ያሉ ነገሥታም ወግተውናል። 14በእነዚህ በጦርነቶች ምክንያት እንተና ሌሎችን የጦር ጓደኞቻችንን፤ ወዳጆቻችንን ማስቸገር አልፈልግም። 15እኛን ለማገዝ ከሰማይ የሚመጣልን እርዳታ አለን፤ እኛ ከጠላቶቻችን እጅ ድነናል፤ እነርሱ ግን ተዋርደው ቀርተዋል፤ 16የአንጥዮኩስን ልጅ ኑምንዩስንና የኢያሶንን ልጅ አንቲጳጠሮስን መርጠን ከሮማውያን ጋር የነበረንን የቀድሞ ወዳጅነታችንንና ስምምነታችንን ለማደስ ወደ ሮማውያን ልከናቸዋል። 17እንዲሁም ወደ እናንተ መጥተው ሰላምታ እንዲያቀርቡና ስለ ስምምነታችንና ስለ ወንድማዊ ግንኙነታችን ተሐድሶ ጉዳይ ደብደቤ እንዲሰጧቸሁ ልከናቸዋል። 18ስለዚህ ጉዳይ መልሳችሁን እንጠባበቃለን”። 19ለኦንያ የተላከው ደብዳቤ ግልባጩ እንዲህ ይላል፤ 20“የእስፖርታውያን ንጉሥ አርዮስ ለሊቀ ካህናት ኦንያ ሰላምታ ያቀርባል፤ 21እስፖርታውያንና አይሁዳውያን ወንድማማች መሆናቸውንና ከአብርሃም ዘር መወለዳቸውን የሚገልጽ ጽሑፍ አግኘተናል። 22አሁን ይህን ነገር ካወቅን ዘንዳ ስለ መልካም አኗኗራችሁ ብትጽፉል መልካም ነው። 23እኛም ለእናንተ ያለን መልእክት ይህ ነው። ከብቶቻችሁንና ንብረቶቻችሁ የእኛ ናቸው፤ የእኛዎቹም የእናንተ ናቸው፤ መልእክተኞቻችን ይህን እንዲገለጹላችሁ ልከናቸዋል”።
ናታን የሶርያ በቀል፤ ስምዖን በፍልስጥኤም
24የዲሜጥሮስ የጦር ሹማምንት ለመዋጋት ፈልገው ከቀድሞ ይበልጥ የበዙ ወታደሮች ይዘው እንደገና መምጣታቸውን ዮናታን ሰማ። 25ከኢየሩሳሌም ወጣና ሊገጥማቸው ወደ ሃማት አገር ሄደ፤ ምክንያቱም ወደ እርሱ አገር እንዲገቡ ጊዜ ሊሰጣቸው አልፈቀደም። 26ወደ ሠፈራቸው ሰላዮች ላከ፤ ሰላዮቹ ተመልሰው ጠላቶች በሌሊት ሊወሩን ይዘጋጃሉ ብለው ነገሩት። 27ፀሐይ ስትጠልቅ ዮናታን ሰዎቹን ነቅተውና የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው ሌሊቱን ሙሉ ለውጊያ ዝግጁዎች ሆነው እንዲገኙ አዘዛቸው። እንዲሁም በሠፈሩ ዙሪያ ጠባቂዎች አቆመ። 28ዮናታንና የእርሱ ሰዎች ለውጊያ ዝግጁዎች መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ ጠላቶቹ ፈሩ፤ ልባቸው በፍርሃት ተሞልቶ በሠፈራቸው እሳት አነደዱ። 29ነገር ግን ዮናታንና ሰዎቹ እሳቱን ያዩ ስለ ነበር መሄዳቸውን ያወቁት ጠዋት ሲነጋ ብቻ ነው። 30ዮታን ተከታተላቸው፤ ግን አልደረሰባቸውም፤ ምክንያቱም የኤለውጥሮስን ወንዝ ተሻግረው ነበር። 31ዮናታን ዘብዴያውያን ወደሚባሉ ዓረቦች ተመለስና ወጋቸው፤ ማረካቸው። 32ከዚያም ሠፈሩን ነቅሎ ወደ ደማስቆስ ሄደ፤ እዚያ አገሩን ሁሉ እየተዘዋወረ ተመለከተ። 33ስምዖንም ገሠገሠና እስከ አስቃሎንና በአጠገቡ እስካሉት ምሽጐች ድረስ ሄደ። ከዚህ በኋላ ወደ ኢዮጴ ተመለሰና ያዛት። 34ምክንያቱም የእዚያ አገር ሰዎች ምሽጉን ለዲመትሪዮስ ሰዎች ለመስጠት ፈልገው ስለ ነበር ነው። የሚጠብቋት ወታደሮችም በዚያ አቆመ።
የግንባታ ሥራ በኢየሩሳሌም
35ዮናታን ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ሰበሰበና ከእነርሱ ጋር ሆኖ በይሁዳ አገር ምሽጐች ለመሥራት ተማከረ፤ 36የኢየሩሳሌም ግንቦችን ለማጠናከርና በምሽጉና በከተማዋ መካከል መለያ የሚሆን ረዥም ግንብ ለመሥራት ፈለገ፤ ይህንንም ማድረግ ያሰበው የዲመትሪዮስ ሰዎች እየመጡ መግዛት ወይም መሸጥ እንዳይችሉ ነው። 37ከተማውን እንደገና የመሥራት ጥረት የጋራ ነበር፤ በምሥራቃዊው ሸለቆ ላይ የነበረው ግንብም በከፊል ተንዶ ነበር፤ ካፋነታ በመባል በምሥራቃዊው ሸለቆ ላይ የነበረው ግንብም በከፊል ተንዶ ነበር፤ ካፋነታ በመባል የሚታወቀውንም ክፍል ጠገነ። 38ስምዖን አዲዳን እንደገና ገነባት፥ አጠናከራት፥ ባለመቆለፊያ መዝጊያም አደረገባት።
ዮናታን በጠላቶቹ እጅ ወደቀ
39ትሪፎን በእስያ ላይ ለመንገሥ፤ አክሊል ለመድፋት፥ በንጉሥ አንጥዮኩስ ላይ እጁን ለመዘርጋት ይፈልግ ነበር። 40ዮናታን ይህን ከማድረግ እንዳያግደውና እንዳይወጋው ፈርቶ እርሱን ለመያዝና ለመግደል ይሻ ነበር፤ ተነሥቶ ወደ ቤተሳን መጣ። 41ዮናታን ምርጥ የሆኑ አርባ ሺህ ሰዎች አስከትሎ ሊገጠመው ሄደ፤ ወደ ቤተሳንም ደረሰ፤ 42ዮናታን ከብዙ ወታደሮች ጋር መምጣቱን ትሪፎን ባየ ጊዜ በእርሱ ላይ እጁን ከመዘርጋት ተቆጠበ። 43እንዲያውም በክብር ተቀበለውና ወደ ወዳጆቹ ሁሉ አቀረበው፤ እጅ መንሻዎችም አቀረበለት፤ ለወዳጆቹ ሁሉና ለወታደሮቹም፥ “ልክ ለእኔ እንደምትታዘዙኝ እንዲሁም ለዮናታን ታዘዙ” ሲል ትእዛዝ ሰጣቸው። 44ዮናታንን እንዲህ አለው፦ “አሁን የሚያስፈራን ምንም ጦርነት ስለሌብን ስለምን ይህን ሁሉ ሕዝብ ታደክማለህ? 45ስለዚህ ወደየቤታቸው እንዲሄዱ አሰናብታቸውና እንሂድ፥ ያችን ከተማና ሌሎች ምሽጐች፥ የቀሩትን ወታደሮችና የጦር አለቆች ሁሉ እሰጥሃለሁ፤ ከዚህ በኋላ እኔ ወደ ሀገሬ እመለሳለሁ፤ አመጣጤም ለዚሁ ነበር።” 46ዮናታንም ስላመነው እርሱ እንዳለው አደረገ፤ ሠራዊቱን አሰናበተ፤ እነርሱም ወደ ይሁዳ ምድር ተመለሱ። 47ከእርሱ ጋር ሦስት ሺህ ሰዎች አስቀረ፤ ከእነርሱ ሁለቱን ሺህ ወደ ገሊላ ላከ፤ ሺህ ሰዎች ተከተሉት። 48ነገር ግን ዮናታን ወደ ጰጦሎማይዳ በገባ ጊዜ የዚያ አገር ነዋሪዎች በሩን ዘጉበትና ያዙት፤ ከእርሱ ጋር የገቡትንም ሰዎቹ ሁሉ በሰይፍ ገደሉዋቸው። 49ትሪፎን የዮናታንን ሰዎች ለመግደል ወደ ገሊላና ወደ ታላቁ ሜዳ እግረኛ ወታደሮችንና ፈረሰኛ ጦሩን ላከ። 50የዮናታን ሰዎች ዮናታን መያዙና እርሱም ሆነ ጓደኞቹ ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ገባቸው፤ ስለዚህ እርስ በርሳቸው ተማከሩ፤ ተሰብስበበውና ለውጊያ ዝግጁዎች ሆነው ወጡ። 51የሚከታተሏቸው ሰዎች እነርሱ ሕይወታቸውን ለማዳን የሚዋጉ መሆናቸውን አይተው ወደ ኋላ ተመለሱ። 52ሁሉም በሰላም ወደ ይሁዳ አገር ደረሱ፤ ስለዮናታንና ስለጓደኞቹ አለቀሱ፤ በጣምም ፈሩ። የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ታላቅ ኀዘን አደረገ። 53በአካባቢው ያሉ ሕዝቦች ሁሉ ሊደመስሱዋቸው ፈለጉ፤ “መሪም ሆነ ድጋፍ የላቸውም፤ ስለዚህ አሁን እንውጋቸው፤ መታሰቢያቸው ከሰዎች መካከል እንዲጠፋ እናድርግ” አሉ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in