YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 13

13
ስምዖን የአይሁዶች መሪና ሊቀ ካህናት
ስምዖን መሪነቱን ያዘ
1ትሪፎን ወደ ይሁዳ አገር ለመሄድና አገሩን ለማጥፋት ከፍ ያለ የጦር ሠራዊት ማከማቸቱን ስምዖን ሰማ። 2ሕዝቡ በፍርሃት መንቀጥቀጡን ባዩ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣና ሕዝቡን አሰባሰበ፤ 3እንዲህ ሲል አረጋጋቸው፦ “እኔና ወንድሞቼ የአባቴም ቤት ስለ ሕግጋትና ስለ ቤተ መቅደስ ብለን ያደረግነውን ሁሉ ታውቃላችሁ። 4ስለዚህ ነው ወንድሞቼ ሁሉ ስለ እስራኤል የሞቱት እኔም ብቻዬን የቀረሁት። 5ይህ ጊዜ የመከራ ጊዜ ቢሆንም እኔ ሕይወቴን የማዳን ሐሳብ የለኝም፤ እኔ ከወንድሞቼ ይበልጥ የተሻልሁ አይደለሁም፤ 6ነገር ግን ሕዝቦቹ ሁሉ በጥላቻ ተነሣሥተው እኛን ለመደምሰስ ስለተባበሩብን እኔ ስለ ሕዝቤና ስለ ቤተ መቅደሱ ስለ ሚስቶቻችሁና ስለ ልጆቻችሁ እበቀላለሁ።” 7ይህን ቃል በመስማት የሕዝቡ መንፈስ ተነሣሣ፤ 8በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያሉ መለሱለት፤ “በወንድሞችህ በይሁዳና በዮናታን ፈንታ አንተ መሪያችን ነህ፤ 9ውጊያችንን ምራ፤ የምትለንን ሁሉ እንፈጽማለን”። 10እርሱም የጦር ሰዎችን በሙሉ ሰበሰበ፤ የኢየሩሳሌምን ግንብ ሠርቶ ለመጨረስ ተጣደፈ፤ በዙሪያውም አጠናከረው። 11የአቤሰሎም ልጅ ዮናታን በቂ ሠራዊት አስከትሎ ወደ ኢዮጴ እንዲሄድ አደረገው፤ ዮናታን ነዋሪዎቹን አባሮ እዚያው ተቀመጠ።
ስምዖን ትሪፎንን ከይሁዳ አስወጣው
12ትሪፎን ከብዙ ሠራዊት ጋር ሆኖ ወደ ይሁዳ አገር ለመግባት ከጰጦሎማይዳ ተነሣ፤ ከእርሱ ጋር ምርኮኛውን ዮናታንን ይዞ ሄደ። 13ስምዖን መጥቶ በሜዳው ፊት ለፊት በአዲዳ ሠፈረ። 14ስምዖን በወንድሙ በዮናታን እግር ተተክቶ ሊዋጋው መዘጋጀቱን ባወቀ ጊዜ ትሪፎን እንዲህ ሲል መልእክተኞችን ላከበት፥ 15“ወንድምህን ዮናታንን ይዘን ያቆየነው ለመንግሥት ሊከፍል በሚገባው ገንዘብ (ዕዳ) ምክንያት ነው፤ 16አሁን አንድ መቶ የብር መክሊትና መያዢያ የሚሆኑ ሁለቱ ልጆቹን ላክልን፤ ይህንንም የምንለው ከተለቀቀ በኋላ እንዳይሸፈትብን ብለን ነው፤ ይህ ከተደረገልን እንለቀዋልን”። 17ስምዖን ምንም እንኳ ይህ ቃል የአታላይነት ቃል መሆኑን ቢያውቅም ከሕዝቡ ታላቅ ጥላቻ እንዳይመጣበት በመፍራት ገንዘቡንና ልጆቹን አስመጣ፥ 18“ዮናታን የሞተው ገንዘቡንና ልጆቹን ስላልላከለት ነው። ይሉኛል”። በሚል ፍራቻ የተጠየቀውን ሁሉ ላከለት። 19ስለዚህ ነው ልጆቹንና መቶውን መክሊት የላከለት፤ ነገር ግን እንደገመተው አታለለው፤ ዮናታንንም አለቀቀውም። 20ከዚህ በኋላ ትሪፎን ሀገሪቱን ለመውረርና ለማጥፋት ገሠገሠ፤ ወደ አዶራ በሚወስደው መንገድ ዞሮ ሄደ፤ ግን ስምዖንና የእርሱ ሠራዊት እርሱ በሄደበት ሁሉ እየተከታተሉ ይቃወሙት ነበር። 21በዚያን ጊዜ በምሽጉ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ቶሎ በበረሃው በኩል እንዲመጣላቸው፥ ስንቅም እንዲልክላቸው ወደ ትሪፎን መልእክተኞች ላኩ። 22ትሪፎን ወደዚያ ለመሄድ ፈረሰኛ ጦሩን በሙሉ አዘጋጀ፤ ግን በዚያች ሌሊት ብዙ በረዶ ጣለ፤ ስለዚህ መሄድ አልቻለም፤ ከዚያ ተነሣና ወደ ገለዓድ አገር አመራ። 23ወደ ባስካማ ሲቃረብ ዮናታንን ገደለው፤ በዚያም ተቀበረ። 24ከዚህ በኋላ ትሪፎን ወደ አገሩ ተመለሰ።
ዮናታን ስምዖን በሞዲን ባዘጋጀው መቃብር ተቀበረ
25ስምዖን ሰው ልኮ የወንድሙን ዓፅም አስመጣና በአባቶቹ ከተማ በመዲን አስቀበረው። 26እስራኤል በመላው ታላቅ ኀዘን አደረጉለት፤ ለብዙ ቀናትም አለቀሱለት፤ 27ስምዖን የአባቱና የወንድሞቹ መቃብር በሩቅ እንዲታዩ ብሎ በስተ ኋላውም፥ በስተ ፊቱም በጥርብ ድንጋይ ከፍ አድርጐ ሠራው። 28ለአባቱ፥ ለእናቱ፥ ለአራቱ ወንድሞቹ ሰባት ሐውልቶችን አጠገብ ለአጠገብ አቆመ። 29በዙሪያቸው በኪነጥበብ የተሠሩ ረዣዥም ዓምዶቹ ላይ በባሕር ላይ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ የሚያዩዋቸውን የዘለዓለም ማስታወሻ የሚሆኑ የጦር መሣሪያዎችና መርከቦች ተቀርጸውባቸው ነበረ። 30በሞዲን የተሠራው እስከ ዛሬም የሚታየው መቃብር ይህ ነው።
ዳግማዊ ዲሜጥሮስ ለስምዖን የዋለው ውለታ
31ትሪፎን በወጣቱ ንጉሠ በአንጥዮኩስ ላይ የአታላይነት ሥራ ሠርቶ ገደለው፤ 32በምትኩ እርሱ ነገሠና የእስያን ዘውድ ተቀዳጀ፤ በአገሩ ላይም ታላቅ መከራ አወረደበት። 33ስምዖን የይሁዳን አገር ምሽጐች እንደገና ሠራቸው፤ በዙሪያቸው ረዣዥም የግንብ ምሽጐችን ሠራ፤ መዝጊያዎችና መቆለፊያዎች ያሏቸው ታላላቅ መካባቢያዎችንም ሠራ፤ በምሽጐቹ ውስጥ ስንቅ አስገብቶ አስቀመጠ። 34ከዚህ በኋላ ስምዖን ወደ ንጉሥ ዲሜጥሮስ ሰው ልኮ አገሩን ከግብር ነጻ እንዲያወጣ ጠየቀ ምክንያቱም ትሪፎን ከመዝረፍ በቀር ሌላ ያደረገው ነገር የለም። 35ንጉሥ ዴሜጥሮስ እንዲህ ሲል መልሱን ጻፈለት፤ 36“ንጉሥ ዲሜጥሮስ ለሊቀ ካህናትና ለነገሥታት ወዳጅ፤ ለስምዖን፥ ለሽማግሌዎችና ለአይሁድ ሕዝብ ሰላምታ ያቀርባል። 37የላካችሁለንን የወርቅ ዘውድና ዘንባባ ተቀብለናል፤ ከእናንተ ጋር ፍጹም የሰላምታ ውል ለመዋዋልና ቀረጥም እንዳያስከፍሏቸሁ ለሠራተኞቻችን ለመጻፍ ዝግጁዎች ነን፤ 38ልናደርግላችሁ የወሰንነው ነገር ሁሉ የጸና ይሆናል፤ የሠራችኋቸው ምሽጐችም የእናንተ ናቸው፤ 39በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እስከ ዛሬ የተደረገውን ስሕተትና በደል ይቅር ብላችኋል፤ መክፈል የሚገባችሁን የዘውድ ግብርና ከኢየሩሳሌም የሚከፈለውንም ሌላ ግብር ትተንላችኋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ አትገደዱም። 40ከእናንተ መካከል አንዳንዶች ከወታደሮቻችን ጋር ተቀጥረው መሥራት የሚችሉ ካሉ ይመዝገቡ በመካከላችን ሰላም ይሁን”። 41በመቶ ሰባ (27 ግንቦት 142) ዓመተ ዓለም የአረማውያን ቀንበር ከእስራኤል ተነሣ፤ 42ሕዝቡም በጽሑፎቻቸውና በውሎቻቸው ላይ፥ “የአይሁድ ሕዝብ የጦር መሪና አለቃ፥ የሊቀ ካህናት ስምዖን መጀመሪያ ዓመት” እያሉ መጻፍ ጀመሩ።
ስምዖን ጌዘርን ያዘ
43በእነዚያ ቀናት ስምዖን ጌዘርን ለመውጋት በሁሉም ቦታ በወታደሮቹ አስከበባት ተንቀሳቃሽ ማማ ሠራና ወደ ከተማው አስጠጋው፤ ከምሽጐቹ አንዱን መትቶ አፈራረሰና ያዘው። 44በተንቀሳቃሽ ማማ ውስጥ የነበሩት ሰዎች እየዘለሉ ወደ ከተማው ገቡ፤ ትልቅ ሁከትም ተፈጠረ። 45የከተማው ነዋሪዎች ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው በበመካበቢያው ግንብ ላይ ወጡ፤ ልብስሳቸውን ቀደዱ፤ ስምዖን ሰላምን እንዲፈጥርና እንዲሰጣቸው ለመኑት። 46እንደክፋታችን አታድርግብን፥ እንደ ምሕረትህ አድርግልን አሉት። 47ስምዖን ከእነርሱ ጋር አንድ ስምምነት አደረገና ጦርነቱን አቆመ፤ ነገር ግን ከከተማዋ አባረራቸው፤ ጣዖቶች የነበሩባቸውን ቤቶች አጸዳ፤ ከዚህ በኋላ በዜማና በምስጋና ገባ፤ 48እርኩሱን ነገር ሁሉ አስወገደ፤ ሕግን ያከብሩ የነበሩትን ሰዎች እዚያ አስቀመጠ፤ ከተማዋን አጠናከረ፤ መኖሪያ ቤቱንም እዚያ ሠራ።
በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ምሽግ ስምዖን ተቆጣጠረ
49በኢየሩሳሌም ምሽግ ውስጥ ያሉት ሰዎች ለመግዛትም ሆነ ለመሸጥ ወደ አገሩ ውስጥ መሄድና መምጣት ስላልቻሉ በረሃብ እጅግ ተሠቃዩ፤ በረሃብ ብዙ ሰዎች ሞቱ። 50ሰላም እንዲያደርግና እንዲቀበላቸው ስምዖንን ለመኑት። እርሱም እሺ አላቸው፤ ቢሆነም ከቦታው አስወጣቸውና ምሽጉን ከእርኩስ ነገር አፀዳ። 51ከሃያ ሦስተኛው ቀን በሁለተኛው ወር በመቶ ሰባ አንድ (ሰኔ 4 ቀን 141) ዓመተ ዓለም በእልልታና በዘንባባ፥ በመሰንቆና በጸናጽል፥ በክራር፥ በዝማሬና በማሕሌት ገቡ፤ ምክንያቱም አንድ ትልቅ ጠላት ከእስራኤል ተነቅሎ ስለወደቀ ነው። 52ስምዖን ይህ ቀን በየዓመቱ በደስታ ይንዲከበር አዘዘ። በምሽጉ ጐን የሚገኘውን የቤተ መቅደሱን ኮረብታ አጠናከረ፤ እርሱም ከእርሱ ሰዎች ጋር እዚያው ተቀመጠ፤ 53ስምዓን የእርሱ ልጅ ዮሐንስ ለሙሉ ሰውነት የደረሰ መሆኑን ባየ ጊዜ የጦሩ አዛዥ የሠራዊቱ ሁሉ አለቃ አድርጐ ሾመው፥ ተቀማጭነቱም በጌዜር ሆነ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in