YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ኢዮብ 16

16
ኢዮብ
1ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፦
2“ይህን የመሰለ ንግግር ብዙ ጊዜ ሰምቼአለሁ፤
እናንተ አሰልቺ አጽናኞች ናችሁ።
3ይህ ከንቱ ንግግራችሁ መጨረሻ የለውምን?
ከእኔ ጋር ይህን ያኽል ለመከራከር
ያነሣሣችሁ ምክንያት ምንድን ነው?
4እናንተ በእኔ ቦታ ሆናችሁ
እኔ በእናንተ ቦታ ብሆን ኖሮ
በንቀት ራሴን እየነቀነቅሁ
አሁን እናንተ የምትሉትን ሁሉ
በእናንተ ላይ አሳምሬ መናገር በቻልኩ ነበር።
5እንዲሁም በአንደበቴ ባበረታታኋችሁና
እናንተንም ለማጽናናት ብዙ መናገር በቻልኩ ነበር።
6“ነገር ግን ብዙ ብናገርም ሕመሜ አይቀነስልኝም፤
ዝም ብዬ ብታገሠውም ሥቃዬ ከእኔ አይወገድም።
7አምላክ ሆይ! ከሰውነት ውጪ አደረግኸኝ፤
ቤተሰቤንም ሁሉ አጠፋህብኝ።
8የሰውነቴ መጨማደድ ማስረጃ ሆኖብኛል፤
ክሳቴም በእኔ ላይ ተነሥቶ ኃጢአተኛ ነህ ብሎ ይመሰክርብኛል።
9እግዚአብሔር ተቈጥቶ ሰውነቴን ቈራረጠ፤
በጥላቻም ጥርሱን አፋጨብኝ፤
ጠላቴም ዐይኑን አፈጠጠብኝ።
10ሰዎች በዙሪያዬ ተሰብስበው ተዘባበቱብኝ፤
እያፌዙም በጥፊ መቱኝ።
11እግዚአብሔር ለክፉ ሰዎች አሳልፎ ሰጠኝ፤
በዐመፀኞች እጅ ላይ ጣለኝ።
12በሰላም እኖር ነበር፤
ነገር ግን እግዚአብሔር በቊጣው ሰባበረኝ፤
አንገቴንም አንቆ ፈጠፈጠኝ፤
ለዒላማውም አደረገኝ።
13ቀስተኞቹ ከበቡኝ
ያለ ርኅራኄ ኲላሊቶቼን ቈራረጡ፤
ሐሞቴንም በምድር ላይ አፈሰሱ፤
14እየደጋገመ አቈሰለኝ፤
እንደ ብርቱ ጦረኛም ተንደርድሮ መታኝ።
15ስለ ሐዘኔም ማቅ ሰፍቼ ለበስኩ፤
በትቢያ ውስጥም ተደፋሁ።
16ፊቴ በልቅሶ ቀላ
ድቅድቅ ጨለማም ቅንድቦቼን ሸፈናቸው።
17ይህ ሁሉ ሲሆን የፈጸምኩት በደል የለም፤
ጸሎቴንም ወደ እግዚአብሔር የማቀርበው
በንጹሕ ልብ ነው።
18“ምድር ሆይ! የደረሰብኝን በደል አትሸፍኚ!
ስለ ፍትሕ የማቀርበው አቤቱታ ተሸፍኖ እንዲቀር አታድርጊ!
19እነሆ፥ ለእኔ የሚመሰክርልኝና
ጥብቅናም የሚቆምልኝ በሰማይ አለ። #ኢዮብ 19፥25።
20ወዳጆቼ በንቀት ይመለከቱኛል፤
እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር አለቅሳለሁ።
21ሰውና ሰውን አወቃቅሶ የሚያስታርቅ እንዳለ ሁሉ፥
ምነው ሰውንና እግዚአብሔርን
አወቃቅሶ የሚያስታርቅ በኖረ፤
22የዕድሜዬ ፍጻሜ እየተቃረበ ነው፤
ወደማልመለስበት መንገድ ለመሄድ
ጥቂት ዘመን ብቻ ይቀረኛል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in