YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ኢዮብ 15

15
ሁለተኛው ክርክር
(15፥1—21፥34)
ኤሊፋዝ
1ቴማናዊው ኤሊፋዝ እንዲህ ሲል መለሰ፦
2“በውኑ ብልኅ ሰው
እንደ ነፋስ የማይጨበጥ ነገር ይናገራልን?
በሆዱስ ጐጂ የሆነ ሐሳብ ሊኖረው ይገባልን?
3ለመሆኑ ብልኅ ሰው ምንም በማይጠቅሙ ቃላትና
ዋጋ በሌለው ንግግር ይከራከራልን?
4አንተ እግዚአብሔርን መፍራት ትተሃል፤
ለእግዚአብሔር የሚገባውንም አምልኮ ታደናቅፋለህ።
5በደለኛነትህ በአነጋገርህ ይታወቃል፤
ነገር ግን በብልጠት አነጋገር ልትሸፍነው ትሞክራለህ።
6የሚፈርድብህ የገዛ አንደበትህ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፤
አነጋገርህም ያጋልጥሃል።
7“ከሰው በፊት የተወለድክ አንተ ነህን?
ተራራዎችስ ከመፈጠራቸው በፊት ተወልደህ ነበርን?
8በውኑ የእግዚአብሔርን ምሥጢር ሰምተሃልን?
ሰብአዊ ጥበብን ሁሉ የምታውቅ
አንተ ብቻ የሆንክ ይመስልሃልን?
9እኛ ከምናውቀው የተለየ የምታውቀው ነገር ምንድን ነው?
ከእኛ ተሰውሮ ለአንተ የተገለጠልህ ምን ጥበብ አለ?
10በዕድሜ ከአባትህ የሚበልጡ
ጠጒራቸው የሸበተ ሽማግሌዎች
በሐሳብ ከእኛ ጋር ናቸው።
11“በእኛ አማካይነት የሚነግርህ
ከእግዚአብሔር የተሰጠህ መጽናናት አይበቃህምን?
12ልብህ ለምን ወደ ሌላ ይወስድሃል?
ስለምንስ በቊጣ ዐይኖችህን ታፈጣለህ?
13ይህንንም በማድረግህ
በእግዚአብሔር ላይ መንፈስህን አነሣሥተሃል።
እንዲህ ያለውን ሁሉ የወቀሳ ቃል እስከ መናገር ደርሰሃል።
14“ሰው ንጹሕ ሊሆን ይችላልን?
ሥጋ ለባሽስ ጻድቅ ሊሆን ይችላልን?
15እግዚአብሔር በመላእክቱ ላይ እምነት የለውም፤
ሰማያት እንኳ በእርሱ ፊት ንጹሓን አይደሉም፤
16የተበላሸና የረከሰ ኃጢአትንም
እንደ ውሃ የሚጠጣ ሰውማ
ምንኛ የባሰ ነው? #ኢዮብ 25፥4-6።
17-18“አባቶቻቸው ሳይደብቁ ያስተላልፉላቸውን፥ ጥበበኞች የገለጡትን፥ እኔም የመረመርኩትን አስረዳሃለሁና ስማኝ፤ ልንገርህ።
19ምድሪቱ ለእነርሱ ብቻ ተሰጥታ ነበር፤
መጻተኞችም በመካከላቸው አልተቀላቀሉባቸውም።
20“ሰዎችን ሲጨቊን የኖረ ክፉ ሰው ዕድሜ
ልኩን ሲሠቃይ ይኖራል።
21የሽብርን ድምፅ በጆሮው ይሰማል፤
ሁሉ ነገር ሰላም መስሎ በሚታይበት ጊዜ አጥፊው ይመጣበታል።
22ዕድል ፈንታው በሰይፍ መሞት ስለ ሆነ፥
ከጨለማ የማምለጥ ተስፋ የለውም፤
23ለአሞራ እንደሚጣል ምግብ ይጣላል፤
የሚጠፋበት ጨለማው ቀን እንደ ቀረበበት ያውቃል።
24የጨለማው ጊዜ አስፈራራው፤
አንድ ንጉሥ ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ዐይነት ሐዘንና ጭንቀት ይበረቱበታል።
25“ይህም የሚሆነው እጁን በእግዚአብሔር ላይ አነሣ፤
ሁሉን የሚችለውንም አምላክ ተዳፈረ።
26የተዳፈረውም በትከሻው ላይ ጠንካራና ሰፊ ጋሻውን አንግቦ
በትዕቢት ወደ እርሱ፥ እየገሠገሠ ነው።
27ፊቱ በስብ ተሸፍኖአል
ወገቡም በውፍረት ተድቦልብሎአል።
28“ይህ ሰው በወደሙ ከተሞች፥
ሰው በማይኖርባቸውና
ለመፍረስ በተቃረቡ ቤቶች ውስጥ ይኖራል።
29ባለጸጋ አይሆንም፥
ሀብቱም ለብዙ ጊዜ አይቈይም፤
በምድር ላይም አይስፋፋም።
30ከጨለማ ማምለጥ አይችልም፤
የእሳት ነበልባል ቅርንጫፎቹን እንዳደረቃቸውና
አበባዎቹም በነፋስ እንደ ረገፉበት ዛፍ ይሆናል።
31በከንቱ ነገር እየተማመነ ራሱን አያታል፤
በዚህም ዋጋ ቢስ ሆኖ ይቀራል።
32ጊዜው ሳይደርስ ግንዱ እንደሚደርቅና
ቅርንጫፎቹም እንደማይለመልሙ ዛፍ ይሆናል።
33ገና ሳይበስል ዘለላውን እንደሚያረግፍ የወይን ተክልና
አበባው እንደሚረግፍ የወይራ ዛፍ ይሆናል።
34“የእግዚአብሔርን ሕልውና የሚክዱ ሰዎች
ዘር አይወጣላቸውም፤
በጉቦ የተሠሩ ቤቶችም በእሳት ይጋያሉ።
35እንደዚህ ያሉ ሰዎች ተንኰልን ያቅዳሉ፤
ችግርንም ይወልዳሉ፤
ልባቸውም በአታላይነት የተሞላ ነው።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in