YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ኢዮብ 14

14
1“ሥጋ የለበሰ ሰው ዕድሜው አጭር ነው፤
ያውም ቢሆን በመከራ የተሞላ ነው።
2እንደ አበባ ታይቶ ወዲያውኑ ይረግፋል፤
እንደ ጥላም ብዙ ሳይቈይ ወዲያው ያልፋል።
3ታዲያ እንዲህ ዐይነቱን ሰብአዊ ፍጡር ትከታተላለህን?
በፊትህስ ለፍርድ ታቀርበዋለህን?
4ከርኩስ ነገር ንጹሕ ነገርን ማግኘት የሚችል ከቶ ማንም የለም።
5የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው፤
የሚኖርባቸውም ወራት በአንተ ዘንድ የተቈጠሩ ናቸው፤
አንተም ከወሰንክለት የዕድሜ ገደብ የሚያልፍ የለም።
6ቅጥረኛ የቀን ሥራውን ሲፈጽም እንደሚደሰት፥
ሰውም በድካም ዘመኑ እንዲደሰት ታገሠው።
7“ለተቈረጠ የዛፍ ጒቶ እንኳ ተስፋ አለው፤
እንደ ገና ሊያቈጠቊጥና ቅርንጫፎችም
ሊያበቅል ይችላል።
8ምንም እንኳ ሥሮቹ በመሬት ውስጥ ቢያረጁ
ግንዱም በዐፈር ውስጥ ቢበሰብስ፥
9የውሃ ጠል ካገኘ እንደ ገና ያቈጠቊጣል፤
እንደ አዲስ ተክልም ቅርንጫፎችን ያወጣል።
10ሰው ግን ሞቶ እንዳልነበረ ይሆናል፤
ከሞተ በኋላስ የት ይገኛል?
11“የሐይቅ ውሃ ተኖ እንደሚያልቅ፥
የወንዝም ፈሳሽ እንደሚደርቅ፥
12ሰውም እንዲሁ ከሞተ በኋላ አይመለስም፤
ሰማይ እስከሚያልፍ ድረስ አይነቃም፤
ከእንቅልፉም አይነሣም።
13“ምነው፥ በሙታን ዓለም ብትሰውረኝ!
ቊጣህም እስከሚያልፍ ብትሸሽገኝ!
የቀጠሮም ቀን ወስነህ ብታስበኝ!
14ሰው ከሞተ በኋላ
በሕይወተ ሥጋ ሊኖር ይችላልን?
ዕረፍቴ እስከምትመጣበት ጊዜ ድረስ፥
ይህን የትግል ዘመኔን ፍጻሜ
በትዕግሥት እጠባበቃለሁ።
15በዚያን ጊዜ አንተ ትጠራኛለህ፤
እኔም ‘አቤት’ እልሃለሁ፤
ፍጡርህ የሆንኩትን እኔን ለማየት ትናፍቃለህ።
16እነሆ አሁን እርምጃዬን ሁሉ ትከታተላለህ፤
ሆኖም ኃጢአቴን አታስብብኝም።
17በከረጢት ታሽጎ እንደሚወረወር ጒድፍ
በደሌን ሁሉ ታስወግድልኛለህ
ኃጢአቴንም ትደመስስልኛለህ።
18በዚህ ዓለም ግን
የተራራ ናዳ እንደሚፈልስ፥
ቋጥኝም ከቦታው እንደሚፈነቃቀል፥
19ውሃ ድንጋይን እየቦረቦረ እንደሚጨርስ፥
ኀይለኛ ዝናብም መሬትን እንደሚሸረሽር፥
አንተም እንዲሁ የደካማን ሰው ተስፋ ታጠፋለህ።
20ኀይልህ ለዘለዓለም በእርሱ ላይ ይበረታል፤
እርሱም እንዳልነበረ ይሆናል፤
መልኩንም ለውጠህ ከፊትህ ታስወግደዋለህ።
21ልጆቹ ክብር ቢያገኙ አያውቅም፤
ቢዋረዱም አያይም።
22እርሱ የገዛ ሰውነቱ ሥቃይ ይሰማዋል፤
ስለ ራሱም ችግር ብቻ ያለቅሳል።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in