YouVersion Logo
Search Icon

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 23

23
ዳዊት በመጨረሻ የተናገረው ቃል
1እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ያደረገው፥ በያዕቆብ አምላክ የተቀባው፥ በእስራኤልም ዘንድ መልካም ባለመዝሙር የሆነው፥ የእሴይ ልጅ የዳዊት የመጨረሻ ቃሉ ይህ ነው።
2የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ አማካይነት ይናገራል፤
ቃሉም በአንደበቴ ነው።
3የእስራኤል አምላክ ይህን ተናግሮአል፤
የእስራኤል ጠባቂ እንዲህ ብሎኛል፤
“እግዚአብሔርን በመፍራትና
በፍትሕ የሚያስተዳድር ንጉሥ፥
4ከዝናብ በኋላ ደመና እንደሌለው ንጋት፥
ምድርንም ሣር እንድታበቅል እንደሚያደርግ፥
እንደ ንጋት የፀሐይ ብርሃን ነው።”
5በሁሉም ነገር የተመቻቸና አስተማማኝ፥
ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ከእኔ ጋር ስለ ገባ፥
በውኑ ቤቴ ለእግዚአብሔር ታማኝ አይደለም?
ርዳታዬና ፍላጎቴስ ሁሉ እንዲሟላ አያደርግምን?
6ክፉዎች ግን እንደ ተጣለ እሾኽ ስለ ሆኑ
ማንም በእጁ ሊዳስሳቸው አይችልም።
7እነርሱን ለመዳሰስ የብረት ልብስ ወይም የጦር ዛቢያ ያስፈልጋል፤
በዚያን ጊዜ ባሉበት ፈጽመው ይቃጠላሉ።
ዝነኞች የሆኑ የዳዊት ወታደሮች
(1ዜ.መ. 11፥10-41)
8ዝነኞች የሆኑት የዳዊት ወታደሮች ስም ዝርዝር ከዚህ በታች እንደ ተመለከተው ነው፤ የመጀመሪያው የታሕክሞን ተወላጅ ዮሼብ ባሼቤት የተባለው ሲሆን እርሱም ከሦስቱ ኀያላን ብልጫ ያለው ተቀዳሚ ነው፤ ይህ ሰው በአንድ ውጊያ ላይ ጦሩን አንሥቶ ስምንት መቶ ኀያላን ሰዎችን ገደለ።
9ከሦስቱ ኀያላን ሁለተኛው ከአሖሕ ጐሣ የሆነው ዝነኛው የዶዶ ልጅ አልዓዛር ነበር፤ አንድ ቀን እርሱና ዳዊት ለጦርነት ተሰልፈው የነበሩትን ፍልስጥኤማውያን ተገዳደሩ፤ እስራኤላውያን ወደ ኋላቸው አፈገፈጉ፤ 10ይህ ሰው ግን ባለበት ጸንቶ በመቆም እጁ ዝሎ በሰይፉ ላይ እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን ወጋ፤ በዚያን ቀን እግዚአብሔር ታላቅ ድልን አደረገ፤ ጦርነቱም ከቆመ በኋላ እስራኤላውያን አልዓዛር ወደነበረበት ስፍራ ተመልሰው ከሞቱት ፍልስጥኤማውያን ብዙ የጦር ልብስ ማረኩ።
11ከሦስቱ ኀያላን ሦስተኛው ደግሞ የሃራር ተወላጅ የሆነው ዝነኛው የአጌ ልጅ ሻማ ነበር፤ አንድ ቀን ፍልስጥኤማውያን የምስር ማሳ ባለበት በሌሒ ተሰልፈው ነበር፤ እስራኤላውያንም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ 12ሻማ ግን በዚያው በማሳው ውስጥ ጸንቶ ቆመ፤ በመከላከልም ፍልስጥኤማውያንን ገደለ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ታላቅ ድልን አደረገ።
13በመከር ጊዜ መጀመሪያ ላይ ከሠላሳው ኀያላን በተለይ ሦስቱ ዳዊት ወዳለበት ወደ ዐዱላም ዋሻ ወረዱ፤ ከፍልስጥኤማውያን ሠራዊት ጥቂቱ ክፍል በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር፤ 14ዳዊት በዚያን ጊዜ በተመሸገ ኮረብታ ላይ ነበር፤ ከፍልስጥኤማውያን ሠራዊት አንድ ቡድን ቤተልሔምን በመውረር ያዘ፤ 15ዳዊትም አገሩን በመናፈቅ “በቤተልሔም ቅጽር በር አጠገብ ካለው የውሃ ጒድጓድ የምጠጣው ውሃ የሚያመጣልኝ ሰው ምነው ባገኘሁ!” አለ። 16ስለዚህ ዝነኞች የሆኑት ሦስቱ ኀያላን ወታደሮች የፍልስጥኤማውያንን ሰፈር በድፍረት ጥሰው በማለፍ ከጒድጓዱ ውሃ ቀድተው ለዳዊት ይዘውለት መጡ፤ ዳዊት ግን ሊጠጣ አልወደደም፤ ይህንንም በማድረግ ፈንታ ለእግዚአብሔር መባ አድርጎ ካፈሰሰው በኋላ፥ 17“እግዚአብሔር ሆይ! ይህን ውሃ ከቶ ልጠጣው አልችልም! እኔ እርሱን ብጠጣ፥ በነፍሳቸው ቈርጠው የሄዱትን የእነዚህን ኀያላን ሰዎች ደም እንደ ጠጣሁ ይቈጠራል!” አለ፤ ውሃውንም መጠጣት እምቢ አለ።
ዝነኞች የሆኑት ሦስቱ ኀያላን ወታደሮች የፈጸሙአቸው የጀግንነት ተግባሮች እነዚህ ናቸው።
18የጽሩያም ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ ዝነኞች የሆኑት የሠላሳዎቹ ወታደሮች አለቃ ነበር፤ እርሱም ጦሩን አንሥቶ ከሦስት መቶ ሰዎች ጋር በመዋጋት ሁሉንም ገደለ፤ ስለዚህም እንደ ሦስቱ ዝነኛ ሆነ። 19ከሠላሳዎቹ መካከል እጅግ ዝነኛ በመሆኑም የእነርሱ አለቃ ሆነ፤ ይሁን እንጂ የሦስቱን ጀግኖች ያኽል ዝነኛ አልነበረም።
20ሌላው ዝነኛ ወታደር የቃብጽኤል ተወላጅ የነበረው የዮዳሄ ልጅ በናያ ነበር፤ እርሱም ሁለት የታወቁ ሞአባውያን ወታደሮችን ከመግደሉም ሌላ ብዙ የጀግንነት ሥራ ፈጽሞአል፤ አንድ ጊዜ በምድር ላይ ዐመዳይ በወረደበት ቀን ወደ አንድ ዋሻ ወርዶ አንበሳ ገደለ፤ 21እንዲሁም ጦር ይዞ የነበረውን አንድ ኀያል ግብጻዊ ገድሎአል፤ ይኸውም በናያ በእጁ ከበትር በስተቀር ሌላ የጦር መሣሪያ ሳይዝ ወደ ግብጻዊው ቀርቦ የገዛ ጦሩን በመቀማት በዚያው ጦር ግብጻዊውን ገደለው። 22እንግዲህ እንደ ሦስቱ ኀያላን ዝነኛ የሆነው በናያ የፈጸማቸው የጀግንነት ሥራዎች እነዚህ ናቸው፤ 23ከሠላሳዎቹ መካከል እጅግ ታዋቂ ቢሆንም በዝነኛነቱ ከሦስቱ ኀያላን ደረጃ አልደረሰም፤ ዳዊትም በናያን የክብር ዘቡ አዛዥ አድርጎ ሾሞት ነበር።
24-39ከሠላሳዎቹ መካከል የሌሎቹ ሰዎች ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው፦
የኢዮአብ ወንድም ዐሣሄል፤
የቤተልሔሙ ተወላጅ የዶዶ ልጅ ኤልሐናን፤
የሐሮድ ተወላጆች የሆኑት ሻማና ኤሊቃ፤
የፌሌጥ ተወላጅ የሆነው ሔሌጽ፤
የተቆዓ ተወላጅ የሆነው የዒቄሽ ልጅ ዒራ፤
የዐናቶት ተወላጅ የሆነው አቢዔዜር፤
የሑሻ ተወላጅ የሆነው መቡናይ፤
የአሖሕ ተወላጅ የሆነው ጻልሞን፤
የነጦፋ ተወላጅ የሆነው ማህራይ፤
የነጦፋ ተወላጅ የሆነው የባዕና ልጅ ሔሌብ፤
በብንያም ግዛት የምትገኘው የጊብዓ ተወላጅ የሆነው የሪባይ ልጅ ኢታይ፤
የፒርዓቶን ተወላጅ የሆነው በናያ፤
በጋዓሽ ሸለቆ አጠገብ የተወለደው ሂዳይ፤
የዓርባ ተወላጅ የሆነው ኢቢዓልቦን፤
የባርሑም ተወላጅ የሆነው ዓዝማዌት፤
የሻዓልቦን ተወላጅ የሆነው ኤልያሕባ፤
የያሼን ልጆች፤
ዮናትን፤
የሐራር ተወላጅ የሆነው ሻማ፤
የሐራር ተወላጅ የሆነው የሻራር ልጅ አሒአም፤
የማዕካ ተወላጅ የሆነው የአሐሰባይ ልጅ ኤሊፌሌጥ፤
የጊሎ ተወላጅ የሆነው የአኪጦፌል ልጅ ኤሊዓም፤
የቀርሜሎስ ተወላጅ የሆነው ሔጽሮ፤
የዐረብ ተወላጅ የሆነው ፓዓራይ፤
የጾባ ልጅ የሆነው የናታን ልጅ ዪግአል
የጋድ ተወላጅ የሆነው ባኒ፤
የዐሞን ተወላጅ የሆነው ጼሌቅ፤
የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ የነበረውና የበኤሮት ተወላጅ የሆነው ናሕራይ፤
የያቲር ተወላጆች የሆኑት ዒራና ጋሬብ፤
ሒታዊው ኦርዮን።
ዝነኞች የሆኑት ኀያላን ወታደሮች ጠቅላላ ድምር ሠላሳ ሰባት ነበር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in