YouVersion Logo
Search Icon

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 22

22
የዳዊት የድል መዝሙር
(መዝ. 18)
1እግዚአብሔር ዳዊትን ከሳኦልና ከሌሎቹም ጠላቶቹ እጅ በመታደግ ባዳነው ጊዜ ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር ክብር ዘመረ፦
2እግዚአብሔር አለቴ፥ አምባዬ
የደኅንነቴ ኀይል፥ ጠንካራ ምሽጌ ነው።
3አንተ የመዳን አለቴ ነህ፤ እንዲሁም ጋሻዬ፥ የጦር መሣሪያዬና ከለላዬ ነህ፤ ከኀያላን እጅ ታድነኛለህ።
4ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤
እርሱም ከጠላቶቼ ያድነኛል።
5የሞት ጣር ከበበኝ፤
የጥፋት ጐርፍም አጥለቀለቀኝ፤
6የሲኦል ገመድ ተበተበኝ፤
የሞት ወጥመድም ተጠመደብኝ፤
7መከራ በደረሰብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤
እንዲረዳኝም አምላኬን ለመንኩት።
በመቅደሱም ሆኖ ድምፄን ሰማ
ጩኸቴንም አደመጠ።
8እግዚአብሔር ስለ ተቈጣ
ምድር ተናወጠች፤ ተንቀጠቀጠችም፤
የአድማስ መሠረቶች ተናጉ፤ ተነቃነቁም።
9ከአፍንጫው የቊጣ ጢስ ወጣ፤
ከአፉም የሚባላ የእሳት ነበልባልና
የሚያቃጥል ፍም ወጣ።
10ሰማይን ሰንጥቆ ወደ ታች ወረደ፤
ከእግሩም በታች ጥቊር ደመና ነበረ፤
11በኪሩቤል ላይ ሆኖ በረረ፤
በነፋስም ክንፎች ላይ ሆኖ መጠቀ።
12ሁለንተናውን በጨለማ ሸፈነ።
በውሃ የተሞላ ጥቅጥቅ ያለ ደመና ከቦታል።
13በፊቱ ካለው ነጸብራቅ የተነሣ
ጥቅጥቅ ያለ ደመና፥ በረዶና
የሚነድ እሳት መጣ።
14እግዚአብሔር ከሰማይ አንጐዳጐደ፤
ልዑል እግዚአብሔር ድምፁን አሰማ።
15ፍላጻውን ከቀስቱ አስፈነጠረ፤
ጠላቶቹንም በተናቸው፤
በመብረቁም ብልጭታ አሳደዳቸው።
16እግዚአብሔርም ከአፍንጫው ከሚወጣው የእስትንፋስ ወላፈንና
በግሣጼው የባሕሩ ውስጥ ወለል ታየ፥
የምድሩም መሠረት ተገለጠ።
17እግዚአብሔር ከላይ ሆኖ እጁን በመዘርጋት ያዘኝ፤
ከጥልቅ ውሃም ስቦ አወጣኝ።
18በጣም በርትተውብኝ ከነበሩት
ከኀይለኞች ጠላቶቼና ከሚጠሉኝ ሰዎች ሁሉ እጅ እግዚአብሔር አዳነኝ።
19እኔ በተቸገርኩበት ጊዜ በጠላትነት ተነሡብኝ
በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤
እግዚአብሔር ግን ጠበቀኝ።
20ወደ ሰፊ ቦታ አወጣኝ፤
በእኔ ደስ ስለ ተሰኘም አዳነኝ።
21እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤
እንደ እጄ ንጽሕናም ይመልስልኛል።
22እኔ የእግዚአብሔርን መንገድ ተከትያለሁ፤
ፊቴን ከአምላኬ በመመለስ ክፉ ነገር አላደረግሁም።
23የእግዚአብሔርን ሕጎች ሁሉ እፈጽማለሁ፤
ሥርዓቱንም ከማክበር ወደ ኋላ አላልኩም።
24በእርሱ ዘንድ ንጹሕ ነበርኩ፥
ከኃጢአትም ራሴን ጠብቄአለሁ፤
25እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ፥
እንደ እጄም ንጽሕና ዋጋዬን ከፈለኝ።
26አምላክ ሆይ! ለአንተ ታማኞች ለሆኑት ታማኝ ነህ፤
እውነተኞች ለሆኑትም እውነተኛ ነህ።
27ለንጹሖች ንጹሕ ነህ፤
ለጠማሞች ግን ተገቢ ዋጋቸውን ትሰጣለህ።
28ትሑቶችን ታድናለህ፤
ትዕቢተኞችን ግን ታዋርዳለህ።
29እግዚአብሔር ሆይ! ለእኔ ብርሃኔ ነህ፤
አንተ አምላኬ ጨለማዬን ታበራለህ።
30በአንተ ርዳታ አንድ የጦር ጓድ አጠቃለሁ፤
አንተ አምላኬም ቅጥሩን ለመዝለል ትረዳኛለህ።
31የእግዚአብሔር መንገድ ፍጹም ነው፤
ቃሉ የጠራ ነው፤
እርሱን መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻቸው ነው።
32ከእግዚአብሔር በቀር ማን ነው አምላክ?
ከእርሱስ በቀር መጠጊያ የሚሆን ማነው?
33ብርታትን የሚሰጠኝና
መንገዴን የሚያቃናልኝ እግዚአብሔር ነው።
34እርሱ እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች ያጠነክራል፤
በከፍታ ቦታዎችም ያለ ሥጋት ለመቆም ያስችለኛል። #ዕን. 3፥19። 35እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፤
የነሐስን ቀስት መሳብ እንዲችሉ ክንዶቼን ያበረታል።
36አምላኬ ሆይ!
የማዳን ጋሻህ ሰጠኸኝ፤
የአንተ ኀይልም ያጸናኛል።
37አረማመዴን አሰፋህ፤
እግሮቼም አልተንሸራተቱም።
38ጠላቶቼን አሳድጄ እደርስባቸዋለሁ፤
ሳላጠፋቸውም ወደ ኋላ አልመለስም፤
39ዳግመኛ እንዳይነሡ አድርጌ እመታቸዋለሁ፤
በእግሬም ሥር ይወድቃሉ።
40ለጦርነት ኀይልን ትሰጠኛለህ፤
በጠላቶቼም ላይ ድልን ታጐናጽፈኛለህ።
41ጠላቶቼ ከፊቴ ወደ ኋላ እንዲሸሹ አደረግህ፤
የሚጠሉኝንም ሁሉ አጠፋቸዋለሁ።
42የሚረዳቸውን በመፈለግ ይጮኻሉ፤
ነገር ግን ማንም አያድናቸውም፤
እግዚአብሔርንም ይጠሩታል፤
እርሱ ግን አይመልስላቸውም።
43ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ እስኪሆኑ ድረስ አደቀቅኋቸው፤
በመንገድ ላይ እንዳለ ጭቃም እረግጣቸዋለሁ።
44ከዐመፀኛ ሕዝብ አዳንከኝ፤
በአሕዛብም ላይ ሾምከኝ፤
የማላውቀውም ሕዝብ ይገዛልኛል።
45ባዕዳን ያጐነብሱልኛል፤
ዝናዬን እንደ ሰሙም ይገዙልኛል
46በፍርሃት ይጨነቃሉ፤
በመንቀጥቀጥም ከምሽጋቸው ወጥተው ወደ እኔ ይመጣሉ።
47እግዚአብሔር ሕያው ነው!
አምላኬ መጠጊያዬ ይመስገን!
ያዳነኝም ኀያል አምላክ ከፍ ከፍ ይበል!
48እርሱ ጠላቶቼን ይበቀልልኛል፤
ሕዝቦችንም ከበታቼ አድርጎ ያስገዛልኛል።
49ከጠላቶቼም ታድነኛለህ።
በጠላቶቼ ላይ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፤
ከግፈኞችም ታድነኛለህ።
50ጌታ ሆይ! ስለዚህ በሕዝቦች መካከል አመሰግንሃለሁ፤
ለስምህም እዘምራለሁ። #ሮም 15፥9።
51እርሱ ላነገሠው ንጉሥ ድልን ያጐናጽፈዋል፤
እርሱ ከቀባውም ዘለዓለማዊ ፍቅሩን ያሳየዋል፤
ለዳዊትና ለዘሩ፥ ለዘለዓለም ይህን ያደርጋል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in