YouVersion Logo
Search Icon

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 24

24
ዳዊት የሕዝብ ቈጠራ ማድረጉ
(1ዜ.መ. 21፥1-27)
1እግዚአብሔር እንደገና በእስራኤል ላይ ስለ ተቈጣ በዳዊት አማካይነት መከራ እንዲመጣባቸው አደረገ፤ እግዚአብሔር ዳዊትን “ሄደህ የእስራኤልንና የይሁዳን ሕዝብ ቊጠር!” አለው፤ 2ስለዚህም ዳዊት የጦሩ አዛዥ የሆነውን ኢዮአብን “የጦር መኰንኖችህን በማስከተል ከአገሪቱ ዳር እስከ ዳር ማለትም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ወዳሉት የእስራኤል ነገዶች ሁሉ ሄደህ ሕዝቡን ቊጠር፤ ምን ያኽል ሕዝብ እንዳለ ማወቅ እፈልጋለሁ” ሲል አዘዘው።
3ኢዮአብ ግን “ንጉሥ ሆይ! አምላክህ እግዚአብሔር የእስራኤል ሕዝብ አሁን ካሉት ይልቅ በመቶ እጅ ያብዛልህ፤ ይህንንም ሲያደርግ ለማየት እንድትበቃ ዕድሜህን ያርዝምልህ፤ ነገር ግን ንጉሥ ሆይ! ይህን ለማድረግ ስለምን ፈለግኽ?” አለው፤ 4ንጉሡ ግን ኢዮአብና የጦር መኰንኖቹ ትእዛዙን እንዲፈጽሙ ስላስገደዳቸው ከፊቱ ወጥተው የእስራኤልን ሕዝብ ለመቊጠር ሄዱ።
5ዮርዳኖስንም ተሻግረው በጋድ ውስጥ በሚገኘው ሸለቆ መካከል ባለችው በዓሮዔር ከተማ በስተ ደቡብ ሰፈሩ፤ ከዚያም ወደ ሰሜን አምርተው ወደ ያዕዜር ደረሱ፤ 6ቀጥለውም ወደ ገለዓድና በሒታውያን ግዛት ውስጥ ወዳለው ወደ ቃዴስ ዘለቁ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ዳን፥ ከዳንም ወደ ምዕራብ ታጥፈው ወደ ሲዶና ሄዱ፤ 7ቀጥሎም በደቡብ በኩል ወደተመሸገችው ወደ ጢሮስ ከተማና እንዲሁም ወደ ሒዋውያንና ወደ ከነዓናውያን ከተሞች ሁሉ ሄዱ፤ በመጨረሻም በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ቤርሳቤህ ዘለቁ፤ 8በዚህ ዐይነት በመላ ሀገሪቱ ሲዘዋወሩ ቈይተው ዘጠኝ ወር ከኻያ ቀን ከሆናቸው በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 9ኢዮአብም በእስራኤል ስምንት መቶ ሺህ፥ በይሁዳ አምስት መቶ ሺህ በውትድርና ለማገልገል ብቃት ያላቸው ሰዎች መኖራቸውንም ለንጉሡ አሳወቀ።
10ነገር ግን ዳዊት ሕዝቡን ከቈጠረ በኋላ የኅሊና ወቀሳ ስላስጨነቀው እግዚአብሔርን “እኔ ይህን በማድረጌ ታላቅ በደል ፈጽሜአለሁ፤ የሞኝነት ሥራ ስለ ሠራሁም እባክህ ይቅር በለኝ!” ሲል ለመነ።
11-12እግዚአብሔርም የዳዊትን ነቢይ ጋድን “ሄደህ ዳዊትን ‘እነሆ ሦስት ምርጫ ሰጥቼሃለሁ፤ እኔም አንተ የምትመርጠውን አደርግብሃለሁ’ ይላል” ብለህ ንገረው። በማግስቱ ጠዋት ዳዊት ከእንቅልፉ ከተነሣ በኋላ፥ 13ጋድ ወዶ እርሱ ቀርቦ እግዚአብሔር ስለ እርሱ ያለውን ነገረው፤ ቀጠል አድርጎም “በምድርህ ሦስት ዓመት ራብ ከሚሆን፥ ለሦስት ወር ጠላቶችህ ከሚያሳድዱህና በምድርህ ላይ ለሦስት ቀን የቸነፈር መቅሠፍት ከሚሆን የትኛውን ትመርጣለህ? እንግዲህ በብርቱ አስብበትና ወደ እግዚአብሔር የማቀርበውን መልስ ስጠኝ” ሲል ጠየቀው።
14ዳዊትም “እነሆ እኔ ለምርጫ በሚያስቸግር ሁኔታ ላይ ነኝ! ይሁን እንጂ በሰው እጅ መውደቅ አልፈልግም፤ እግዚአብሔር መሐሪ ስለ ሆነ እርሱ ራሱ ይቅጣኝ!” አለ። 15ስለዚህ እግዚአብሔር ከዚያን ጠዋት ጀምሮ እስከ ወሰነው ቀን ድረስ በእስራኤል ላይ ቸነፈር አመጣ፤ በሀገሪቱ ዳር እስከ ዳር ማለትም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሰባ ሺህ እስራኤላውያን አለቁ። 16የእግዚአብሔር መልአክ ኢየሩሳሌምን ለመደምሰስ በሚዘጋጅበት ጊዜ እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለ መቅጣት ያለውን ውሳኔ ለውጦ ይቀሥፋቸው የነበረውን መልአክ “በቃህ! አቁም!” አለው፤ በዚህም ጊዜ መልአኩ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ላይ ቆሞ ነበር።
17ዳዊትም ሕዝቡን ይቀሥፍ የነበረውን መልአክ አይቶ እግዚአብሔርን “በደል የፈጸምኩት እኔ ነኝ፤ እኔም ራሴ ክፉ ነገርን አደረግሁ፤ ታዲያ ይህ ምስኪን ሕዝብ ምን በደለህ? ይህ መቅሠፍት በእርሱ ላይ ከሚወርድ ይልቅ በእኔና በቤተሰቤ ላይ ይሁን” ሲል ጠየቀ።
የዳዊት መሠዊያ መሥራት
18በዚያው ዕለት ነቢዩ ጋድ ወደ ዳዊት ሄዶ “ወደ ኦርና አውድማ ሄደህ ለእግዚአብሔር መሠዊያውን ሥራ!” አለው፤ 19ዳዊትም ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ጋድ እንደ ነገረው አደረገ፤ 20ኦርናም ወደ ታች ሲመለከት ንጉሥ ዳዊትና ባለሟሎቹ የሆኑት ባለሥልጣኖች ወደ እርሱ ሲመጡ አየ፤ እርሱም በዳዊት ፊት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ፤ 21“ንጉሥ ሆይ! ስለምን ወደዚህ መጣህ?” ሲል ጠየቀው።
ዳዊትም “እግዚአብሔር የቸነፈሩን መቅሠፍት እንዲመልስ የአንተን አውድማ ለመግዛትና በዚያውም ላይ መሠዊያ ለመሥራት ነው የመጣሁት” አለው።
22ኦርናም “ንጉሥ ሆይ! አውድማውን ወስደህ በፈቀድከው ዐይነት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቅርብበት፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ሆነው ይቀርቡ ዘንድ እነሆ እነዚህ በሬዎች አሉ፤ ስለ ማገዶም ጉዳይ እነርሱ የሚጠመዱበት ቀንበርና የእህል መውቂያው እንጨት ሁሉ አለ” አለው። 23ኦርናም “ይህን ሁሉ ለንጉሡ ሰጥቶ እግዚአብሔር መሥዋዕትህን ይቀበልልህ” አለው።
24ንጉሥ ዳዊት ግን “ይህስ አይሆንም፤ ዋጋውን መክፈል አለብኝ፤ እኔ ምንም ዋጋ ያላወጣሁበትን ነገር ለአምላኬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጌ ማቅረብ አይገባኝም” አለው፤ ከዚህም በኋላ ዳዊት አውድማውንና በሬዎቹን በኀምሳ ጥሬ ብር ገዛ፤ 25ለእግዚአብሔርም መሠዊያ ሠርቶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነት መሥዋዕት ሁሉ አቀረበ፤ እግዚአብሔርም የዳዊትን ጸሎት ሰማ፤ በእስራኤል ላይ የወረደውም የቸነፈር መቅሠፍት ከዚህ በኋላ ቆመ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in