YouVersion Logo
Search Icon

መዝሙር 7

7
መዝሙር 7
በስደት ጊዜ የጻድቁ ሰው ጸሎት
ዳዊት በብንያማዊው በኩዝ ምክንያት ለእግዚአብሔር የዘመረው መዝሙር።
1 እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፤
ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝ፤ ታደገኝም፤
2አለዚያ እንደ አንበሳ ይዘነጣጥሉኛል፤
የሚያድነኝ በሌለበትም ይቦጫጭቁኛል።
3 እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ይህን አድርጌ ከሆነ፣
በደልም በእጄ ከተገኘ፣
4በጎ ለዋለልኝ ክፉ መልሼ ብሆን፣
ጠላቴንም በከንቱ ዘርፌ ከሆነ፣
5ጠላቴ አሳድዶ ይያዘኝ፤
ሕይወቴን ከምድር ይቀላቅል፤
ክብሬንም ከዐፈር ይደባልቅ። ሴላ
6 እግዚአብሔር ሆይ፤ በመዓትህ ተነሥ፤
በቍጣ በተነሡብኝ ላይ ተነሥ፤
አምላኬ ሆይ፤ ንቃ፤ ትእዛዝም አስተላልፍ!
7የሕዝቦች ጉባኤ ይክበብህ፤
አንተም ከላይ ሆነህ ግዛቸው፤
8 እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ ይፈርዳል።
እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ጽድቄ ፍረድልኝ፤
ልዑል ሆይ፤ እንደ ቅን አካሄዴ መልስልኝ።
9ልብንና ኵላሊትን የምትመረምር፣
ጻድቅ አምላክ ሆይ፤
የክፉዎችን ዐመፅ አጥፋ፤
ጻድቁን ግን አጽና።
10ጋሻዬ#7፥10 ወይም የእኔ ልዑል ልዑል አምላክ ነው፤
እርሱ ልበ ቅኖችን ያድናቸዋል።
11እግዚአብሔር ጻድቅ ዳኛ ነው፤
ቍጣውንም በየዕለቱ የሚገልጥ አምላክ ነው።
12ሰው በንስሓ የማይመለስ ከሆነ ግን፣
ሰይፉን#7፥12 ወይም ሰው ንስሓ ካልገባ፣ እግዚአብሔር ሰይፉን ይስላል፤
ቀስቱን ይገትራል።
13የሚገድሉ ጦር ዕቃዎቹን አሰናድቷል፤
የሚንበለበሉትን ፍላጻዎቹንም አዘጋጅቷል።
14ክፋትን እያማጠ ያለ ሰው፣
ቅጥፈትን አርግዞ፣ ሐሰትን ይወልዳል።
15ጕድጓድ ምሶ ዐፈሩን የሚያወጣ፣
በአዘጋጀው ጕድጓድ ራሱ ይገባበታል።
16ተንኰሉ ወደ ራሱ ይመለሳል፤
ዐመፃውም በገዛ ዐናቱ ላይ ይወርዳል።
17ስለ ጽድቁ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀርባለሁ፤
የልዑል እግዚአብሔርን ስም በመዝሙር አወድሳለሁ።

Currently Selected:

መዝሙር 7: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in