YouVersion Logo
Search Icon

መዝሙር 42

42
ሁለተኛ መጽሐፍ
ከመዝሙር 42–72
መዝሙር 42#42 በብዙ የዕብራይስጥ ቅጆች መዝሙር 42 እና 43 አንድ መዝሙር ነው።
ለመዘምራን አለቃ።
በስደት ላይ ያለ ሌዋዊ ልቅሶ
1ዋላ የምንጭ ውሃ እንደምትናፍቅ፣
አምላክ ሆይ፤ ነፍሴም እንዲሁ አንተን ትናፍቃለች።
2ነፍሴ አምላክን፣ ሕያው አምላክን ተጠማች፤
መቼ ደርሼ ነው የአምላክን ፊት የማየው?
3ሰዎች ቀኑን ሙሉ፣
“አምላክህ የት አለ?” ባሉኝ ቍጥር፣
እንባዬ ቀንና ሌሊት፣
ምግብ ሆነኝ።
4ነፍሴ በውስጤ እየፈሰሰች፣
እነዚህን ነገሮች አስታወስሁኝ፤
ታላቅ ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ቤት እየመራሁ፣
በእልልታና በምስጋና መዝሙር፣
በአእላፍ ሕዝብ መካከል፣
እንዴት ከሕዝቡ ጋር እሄድ እንደ ነበር ትዝ አለኝ።
5ነፍሴ ሆይ፤ ለምን ትተክዢያለሽ?
ለምንስ በውስጤ ትታወኪያለሽ?
ተስፋሽን በአምላክ ላይ አድርጊ፤
6አዳኜና አምላኬን፣ ገና አመሰግነዋለሁና።
ነፍሴ በውስጤ ተክዛለች፤
ስለዚህ በዮርዳኖስ ምድር፣
በአርሞንኤም ከፍታ፣ በሚዛር ተራራ ዐስብሃለሁ።
7በፏፏቴህ ማስገምገም፣
አንዱ ጥልቅ ሌላውን ጥልቅ ይጣራል፤
ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ፣
ሙሉ በሙሉ አጥለቀለቀኝ።
8 እግዚአብሔር ምሕረቱን በቀን ያዝዛል፤
ዝማሬውም በሌሊት በእኔ ዘንድ አለ፤
ይህም ለሕይወቴ አምላክ የማቀርበው ጸሎት ነው።
9እግዚአብሔር ዐለቴን፣
“ለምን ረሳኸኝ?
ጠላትስ እያስጨነቀኝ፣
ለምን በሐዘን እመላለሳለሁ?” እለዋለሁ።
10ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ፣
“አምላክህ የት አለ?” እያሉ፣
በነገር ጠዘጠዙኝ፣
ዐጥንቴም ደቀቀ።
11ነፍሴ ሆይ፤ ለምን ትተክዢያለሽ?
ለምንስ በውስጤ ትታወኪያለሽ?
ተስፋሽን በአምላክ ላይ አድርጊ፣
አዳኜና አምላኬን
ገና አመሰግነዋለሁና።

Currently Selected:

መዝሙር 42: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in