መዝሙር 104:1-17
መዝሙር 104:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙንም ጥሩ፥ ለአሕዛብም ሥራውን ንገሩ። ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፥ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ። በቅዱስ ስሙም ትከብራላችሁ። እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው፤ እግዚአብሔርን ፈልጉት፥ ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። የሠራውን ድንቅ ዐስቡ፥ ተአምራቱን፥ የአፉንም ፍርድ። ባሪያዎቹ የአብርሃም ዘር፥ ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱ በምድር ሁሉ ነው። ለዘለዓለም የሚኖር ቃል ኪዳኑን፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን ዐሰበ። ለአብርሃም የሠራለትን፥ ለይስሐቅም የማለውን፤ ለያዕቆብ ምስክርነትን አጸና። ለእስራኤልም ለዘለዓለም የሚኖር ኪዳኑን፤ እንዲህም አለው፥ “ለአንተ የከነዓንን ምድር፥ የርስታችሁ ገመድ ትሆናችሁ ዘንድ እሰጣለሁ፤” እነርሱ በቍጥር እጅግ ጥቂቶችና፥ በውስጧ ስደተኞች ሲሆኑ። ከሕዝብ ወደ ሕዝብ፥ ከነገሥታት ወደ ሌላ ሕዝብ አለፉ። ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልተወም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታቱን ገሠጸ። የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ። በምድር ላይ ራብን አመጣ፥ የእህልን ኀይል ሁሉ አጠፋ። በፊታቸው ሰውን ላከ፤ ዮሴፍ ተሸጠ፥ አገልጋይም ሆነ።
መዝሙር 104:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፤ ክብርንና ግርማን ለብሰሃል። ብርሃንን እንደ ሸማ ተጐናጽፈሃል፤ ሰማያትንም እንደ ድንኳን መጋረጃ ዘረጋህ፤ የእልፍኝህን አግዳሚ በውሆች ላይ አኖርህ፤ ደመናትን ሠረገላህ አደረግህ፤ በነፋስ ክንፍ ትሄዳለህ። መላእክትህን መንፈስ፣ አገልጋዮችህንም የእሳት ነበልባል ታደርጋለህ። ለዘላለም እንዳትናወጥ፣ ምድርን በመሠረቷ ላይ አጸናት። በጥልቁ እንደ ልብስ ሸፈንሃት፤ ውሆችም ከተራሮች በላይ ቆሙ። በገሠጽሃቸው ጊዜ ግን ፈጥነው ሄዱ፤ የነጐድጓድህንም ድምፅ በሰሙ ጊዜ ሸሹ። በተራሮች ላይ ፈሰሱ፤ ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራ፣ ወደ ሸለቆዎች ወረዱ። ተመልሰው ምድርን እንዳይሸፍኑ፣ ዐልፈውም እንዳይመጡ ድንበር አበጀህላቸው። ምንጮችን በሸለቆ ውስጥ እንዲሄዱ አደረግህ፤ በተራሮችም መካከል ይፈስሳሉ፤ የዱር እንስሳትም ከዚያ ይጠጣሉ፤ የሜዳ አህዮችም ጥማቸውን ይቈርጣሉ። የሰማይ ወፎች ጐጇቸውን በወንዞቹ ዳር ይሠራሉ፤ በቅርንጫፎችም መካከል ይዘምራሉ። ከላይ ከእልፍኝህ ተራሮችህን ታጠጣለህ፤ ምድርም በሥራህ ፍሬ ትረካለች። ከምድር ምግብን ታወጣ ዘንድ፣ ለእንስሳት ሣርን፣ ለሰው ልጆች ሥራ ዕፀዋትን ታበቅላለህ፤ የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኝ ወይን፣ ፊቱን የሚያወዛ ዘይት፣ ልቡን የሚያበረታ እህል በዚህ ይገኛል። ደግሞም የእግዚአብሔር ዛፎች፣ እርሱ የተከላቸውም የሊባኖስ ዝግባዎች ጠጥተው ይረካሉ፤ ወፎች ጐጇቸውን በዚያ ይሠራሉ፤ ሽመላ በጥዶቹ ውስጥ ማደሪያ ታገኛለች።
መዝሙር 104:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ነፍሴ ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኚ! እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! እንዴት ታላቅ ነህ! ግርማንና ክብርን ለብሰሃል። ብርሃንንም እንደ ልብስ ተጐናጽፈሃል፤ ሰማይን እንደ ድንኳን ዘርግተሃል። በጠፈር ላይ ካለው ውሃ በላይ ቤትህን ሠርተሃል፤ ደመና ሠረገላህ ነው፤ በነፋስ ክንፎችም ትሄዳለህ። ነፋስ መልእክተኛህ ነው፤ የእሳት ነበልባልም አገልጋይህ ነው። ምድርን በመሠረትዋ ላይ አጽንተህ አቆምሃት፤ ከቶም አትናወጥም። ውቅያኖስን እንደ ልብስ አለበስካት፤ ውሃውም ተራራዎችን ሸፈነ። ውሃውን በገሠጽከው ጊዜ ከፊትህ ሸሸ፤ የትእዛዝህን ድምፅ በሰማ ጊዜ በፍጥነት ሮጠ። አንተ ወዳዘጋጀህለት ስፍራ፥ ወደ ተራራዎች ላይና ወደ ሸለቆዎች ውስጥ ፈሰሰ። ዳግመኛ ምድርን እንዳይሸፍንም የማይጥሰውን ወሰን አበጀህለት። ምንጮች በሸለቆ ውስጥ እንዲፈስሱ፥ ወንዞችም በተራራዎች መካከል እንዲወርዱ አደረግህ። በዚህ ዐይነት የዱር አውሬዎች የሚጠጡት ውሃ ያገኛሉ፤ የሜዳ አህዮችም ጠጥተው ጥማቸውን ያረካሉ። በነዚህም ምንጮችና ወንዞች አጠገብ ባሉት ዛፎች ላይ፥ ወፎች ጎጆአቸውን ሠርተው ያዜማሉ። ከሰማይ ዝናብን በተራሮች ላይ ታወርዳለህ፤ ምድርም በምትሰጣት በረከት ትሞላለች። ሣርን ለእንስሶች ታበቅላለህ፤ አትክልትንም ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲውል ታደርጋለህ፤ በዚህ ዐይነት ሰው ምግብ የሚሆነውን ዘርቶ ይሰበስባል። ስለዚህ ልቡን ደስ የሚያሰኝ የወይን ጠጅ፥ ፊቱን የሚያበራ ዘይትና ብርታት የሚሰጠውን ምግብ ያዘጋጃል። እግዚአብሔር የተከላቸው የሊባኖስ ዛፎች በቂ ዝናብ ያገኛሉ፤ በላያቸውም ወፎች ጎጆዎቻቸውን ይሠራሉ፤ ሸመላዎችም በእነዚያ ዛፎች ላይ መኖሪያቸውን ያበጃሉ።
መዝሙር 104:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፥ ክብርንና ግርማን ለበስህ። ብርሃንን እንደ ልብስ ለበስህ፥ ሰማይንም እንደ ድንኳን መጋረጃ ዘረጋህ፥ እልፍኙን በውኃ የሚሠራ፥ ሠረገላውን ደመና የሚያደርግ፥ በነፋስ ክንፍም የሚሄድ፥ ነፋሳትን መልእክተኞቹ የሚያደርግ፥ የእሳት ነበልባልም አገልጋዮቹ። ለዘለዓለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት። በጥልቅ እንደ ልብስ ከደንሃት፥ በተራሮችም ላይ ውኆች ይቆማሉ። ከቁጣህም ይሸሻሉ፥ ከነጐድጓድህም ድምፅ ይደነብራሉ፥ ወደ ተራሮች ይወጣሉ፥ ወደ ቈላዎች፥ ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራ ይወርዳሉ፥ እንዳያልፉትም ድንበር አደረግህላቸው ተመልሰው ምድርን እንዳይከድኑ። ምንጮችን ወደ ሸለቆዎች ይልካል፥ በተራሮችም መካከል ያልፋሉ፥ የዱር አራዊትን ሁሉ ያጠጣሉ፥ የበረሃ አህያዎችም ጥማቸውን ያረካሉ። የሰማይም ወፎች በእነርሱ ዘንድ ያድራሉ፥ በቅጠሎች መካከል ያዜማሉ ይጮኻሉ። ተራሮችን ከላይ የምታጠጣቸው፥ ከሥራህ ፍሬ ምድር ትጠግባለች። እንጀራን ከምድር ያወጣ ዘንድ ሣርን ለእንስሳ፥ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም ያበቅላል። ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ያበራል፥ እህልም የሰውን ጉልበት ያጠነክራል። የጌታ ዛፎች እርሱም የተከላቸው የሊባኖስ ዝግባዎች ይጠግባሉ። በዚያም ወፎች ጎጆአቸውን ይሠራሉ፥ ሽመላዎችም ከበላያቸው ቤታቸውን ያበጃሉ።