መጽሐፈ መዝሙር 104
104
ለፈጣሪ የቀረበ ምስጋና
1ነፍሴ ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኚ!
እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! እንዴት ታላቅ ነህ!
ግርማንና ክብርን ለብሰሃል።
2ብርሃንንም እንደ ልብስ ተጐናጽፈሃል፤
ሰማይን እንደ ድንኳን ዘርግተሃል።
3በጠፈር ላይ ካለው ውሃ በላይ ቤትህን ሠርተሃል፤
ደመና ሠረገላህ ነው፤
በነፋስ ክንፎችም ትሄዳለህ።
4ነፋስ መልእክተኛህ ነው፤
የእሳት ነበልባልም አገልጋይህ ነው። #ዕብ. 1፥7።
5ምድርን በመሠረትዋ ላይ አጽንተህ አቆምሃት፤
ከቶም አትናወጥም።
6ውቅያኖስን እንደ ልብስ አለበስካት፤
ውሃውም ተራራዎችን ሸፈነ።
7ውሃውን በገሠጽከው ጊዜ ከፊትህ ሸሸ፤
የትእዛዝህን ድምፅ በሰማ ጊዜ በፍጥነት ሮጠ።
8አንተ ወዳዘጋጀህለት ስፍራ፥
ወደ ተራራዎች ላይና ወደ ሸለቆዎች ውስጥ ፈሰሰ።
9ዳግመኛ ምድርን እንዳይሸፍንም
የማይጥሰውን ወሰን አበጀህለት።
10ምንጮች በሸለቆ ውስጥ እንዲፈስሱ፥
ወንዞችም በተራራዎች መካከል እንዲወርዱ አደረግህ።
11በዚህ ዐይነት የዱር አውሬዎች የሚጠጡት ውሃ ያገኛሉ፤
የሜዳ አህዮችም ጠጥተው ጥማቸውን ያረካሉ።
12በነዚህም ምንጮችና ወንዞች አጠገብ ባሉት ዛፎች ላይ፥
ወፎች ጎጆአቸውን ሠርተው ያዜማሉ።
13ከሰማይ ዝናብን በተራሮች ላይ ታወርዳለህ፤
ምድርም በምትሰጣት በረከት ትሞላለች።
14ሣርን ለእንስሶች ታበቅላለህ፤
አትክልትንም ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲውል ታደርጋለህ፤
በዚህ ዐይነት ሰው ምግብ የሚሆነውን ዘርቶ ይሰበስባል።
15ስለዚህ ልቡን ደስ የሚያሰኝ የወይን ጠጅ፥
ፊቱን የሚያበራ ዘይትና
ብርታት የሚሰጠውን ምግብ ያዘጋጃል።
16እግዚአብሔር የተከላቸው
የሊባኖስ ዛፎች በቂ ዝናብ ያገኛሉ፤
17በላያቸውም ወፎች ጎጆዎቻቸውን ይሠራሉ፤
ሸመላዎችም በእነዚያ ዛፎች ላይ መኖሪያቸውን ያበጃሉ።
18ዋልያዎች በከፍተኛ ተራራዎች ላይ ይገኛሉ፤
ሽኮኮዎችም በተሰነጠቁ አለቶች ውስጥ ይኖራሉ።
19ጨረቃን የወቅቶች ምልክት እንድትሆን፥
ፀሐይ የሚጠልቅበትን ጊዜ እንዲያውቅ አድርገሃል።
20አንተ ጨለማን ፈጠርክ፤ ሌሊትም ሆነ፤
በጨለማም የዱር አውሬዎች ሁሉ ይወጣሉ።
21እግዚአብሔር የሚያዘጋጀውን ምግብ ሲያድኑ
የአንበሳ ደቦሎች ያገሣሉ።
22ፀሐይ በሚወጣበት ጊዜ ሾልከው ይሄዳሉ፤
ተመልሰው በየመኖሪያቸው ውስጥ ይተኛሉ።
23ከዚህ በኋላ ሰዎች ለሥራ ይሰማራሉ፤
እስከሚመሽም ድረስ ሲሠሩ ይውላሉ።
24እግዚአብሔር ሆይ!
አንተ ብዙ ነገሮችን ፈጥረሃል፤
ሁሉንም በጥበብ አድርገሃል፤
ምድር አንተ በፈጠርካቸው ነገሮች ተሞልታለች።
25ከቊጥር በላይ በሆኑ ታላላቅና ታናናሽ ሕያዋን ፍጥረቶች
የተሞላው ትልቁና ሰፊው ባሕር እነሆ፥
26በላዩ መርከቦች ይመላለሳሉ፤
በውስጡም አንተ የፈጠርከው ሌዋታን የተባለ
ታላቅ ዘንዶ ይጫወታል። #ኢዮብ 41፥1፤ መዝ. 74፥14፤ ኢሳ. 27፥1።
27እነዚህ ሁሉ ምግባቸውን በየጊዜው
እንድትሰጣቸው ተስፋ የሚያደርጉት አንተን ነው።
28አንተ ምግብ ስትሰጣቸው እነርሱም ይመገባሉ፤
አንተ እጅህን ስትዘረጋ
እነርሱም መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ በልተው ይጠግባሉ።
29አንተ ስትለያቸው ሁሉም ይደነግጣሉ፤
እስትንፋሳቸውን ስትወስድባቸውም ይሞታሉ፤
ወደ ተገኙበትም ዐፈር ይመለሳሉ።
30እስትንፋስ ስትሰጣቸው ግን ይፈጠራሉ፤
ለምድርም አዲስ ሕይወት ትሰጣለህ።
31የእግዚአብሔር ክብር ለዘለዓለም ይኑር!
እግዚአብሔር በፈጠረው ነገር ሁሉ ደስ ይበለው።
32ምድርን ሲመለከት ትንቀጠቀጣለች፤
ተራራዎችን ሲነካ እነርሱም ይጤሳሉ።
33በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤
በሕይወትም እስካለሁ ድረስ
ለአምላኬ የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ።
34ደስታዬ በእርሱ ስለ ሆነ
እርሱም በማቀርብለት የተመስጦ ጸሎት ደስ ይበለው።
35ኃጢአተኞች ከምድር ላይ ይጥፉ!
ግፍ አድራጊዎችም ይደምሰሱ!
ነፍሴ ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኚ!
እግዚአብሔርን አመስግኚ!
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 104: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997