መዝሙረ ዳዊት 104:1-17

መዝሙረ ዳዊት 104:1-17 መቅካእኤ

ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፥ ክብርንና ግርማን ለበስህ። ብርሃንን እንደ ልብስ ለበስህ፥ ሰማይንም እንደ ድንኳን መጋረጃ ዘረጋህ፥ እልፍኙን በውኃ የሚሠራ፥ ሠረገላውን ደመና የሚያደርግ፥ በነፋስ ክንፍም የሚሄድ፥ ነፋሳትን መልእክተኞቹ የሚያደርግ፥ የእሳት ነበልባልም አገልጋዮቹ። ለዘለዓለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት። በጥልቅ እንደ ልብስ ከደንሃት፥ በተራሮችም ላይ ውኆች ይቆማሉ። ከቁጣህም ይሸሻሉ፥ ከነጐድጓድህም ድምፅ ይደነብራሉ፥ ወደ ተራሮች ይወጣሉ፥ ወደ ቈላዎች፥ ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራ ይወርዳሉ፥ እንዳያልፉትም ድንበር አደረግህላቸው ተመልሰው ምድርን እንዳይከድኑ። ምንጮችን ወደ ሸለቆዎች ይልካል፥ በተራሮችም መካከል ያልፋሉ፥ የዱር አራዊትን ሁሉ ያጠጣሉ፥ የበረሃ አህያዎችም ጥማቸውን ያረካሉ። የሰማይም ወፎች በእነርሱ ዘንድ ያድራሉ፥ በቅጠሎች መካከል ያዜማሉ ይጮኻሉ። ተራሮችን ከላይ የምታጠጣቸው፥ ከሥራህ ፍሬ ምድር ትጠግባለች። እንጀራን ከምድር ያወጣ ዘንድ ሣርን ለእንስሳ፥ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም ያበቅላል። ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ያበራል፥ እህልም የሰውን ጉልበት ያጠነክራል። የጌታ ዛፎች እርሱም የተከላቸው የሊባኖስ ዝግባዎች ይጠግባሉ። በዚያም ወፎች ጎጆአቸውን ይሠራሉ፥ ሽመላዎችም ከበላያቸው ቤታቸውን ያበጃሉ።